Connect with us

ወይ ጀዋር!… ደግሞ በመዝናኛ ድራማችን መጣኸ?!

ወይ ጀዋር!... ደግሞ በመዝናኛ ድራማችን መጣኸ?!
Photo: Social Media

መዝናኛ

ወይ ጀዋር!… ደግሞ በመዝናኛ ድራማችን መጣኸ?!

ወይ ጀዋር!… ደግሞ በመዝናኛ ድራማችን መጣኸ?!
(ጫሊ በላይነህ)

የኦፌኮው ፓለቲከኛ ጀዋር መሐመድ ከትላንት በስቲያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የለጠፋት አጭር አስተያየት ቀልቤን ሳበው። አስተያየቱ “ቤቶች” በመባል የሚታወቀውና በእነጥላሁን ጉግሳ በኢቲቪ ዘወትር ቅዳሜ የሚተላለፈውን የመዝናኛ ድራማ የሚመለከት ነው።ባልሳሳት ባሳለፍነው ቅዳሜ በተላለፈው የቤቶች ድራማ አንድ ነጠላ መልእክት ጀዋርን አስፈንድቋል። እናም በፌስቡክ ገፁ የፓለቲካ ሳታየር (ስላቅ) ለዴሞክራሲ ማበብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ውዳሴ ያቀረበው ደስታውን መደበቅ ባለመቻሉ ይመስለኛል። ያው በእሱ አረዳድ በድራማው ተቀንጭቦ በቀረበው ንግግር የብልፅግና ፓርቲ ሰዎችን ልክ ልካቸውን ነገረልኝ አይነት ስሜት ውስጥ ዶሎታል። ጀዋር በአጭር መልእክቱ ኢቲቪ በቀረበው ስላቅ ምክንያት አንዳች እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚል መላምቱንም አስቀምጧል።

እውነት ለመናገር በዕለቱ የተላለፈውን የቤቶች ድራማ አላየሁትም ነበር። እናም ወደ የቪዲዮ ክምችት በማምራት ከዩቲዩብ ላይ ክፍል 303 “ወንድ ልጅ ቆረጠ” በሚል ርዕስ የተቀመጠውን ቪድዮ ያየሁት የጀዋርን ሙገሳ ካነበብኩኝ በኃላ ነው። ሙሉውን ድራማ ካየሁኝ በኃላ ተመልሼ ጀዋር መሐመድ ለእሱ ገረሜታ የፈጠረበትን፣ ከድራማው ክፍል ቀንጭቦ ያስቀመጠውን የቪዲዮ ሊንክ ከፍቼ ተመለከትኩት።

የጀዋርን ትኩረት የሳበው የድራማው ክፍል እንዲህ ይላል።” ስብሰባውን በሥርአት ለመምራት የምቸገር ከሆነ የሀይል እርምጃ ለመውሰድ እገደዳለሁ”
ሌላኛው ገፀባህርይ “…ገና ስብሰባው ሲጀመር የሀይል እርምጃን ምን አመጣው? ተነጋግሮ መግባባት አላቃተን…ገና ለገና የቤቱ አባወራ ነኝ ብለህ ነው..” የሚል መልስ ይሰጣል።

ጀዋር በቤቶች ድራማ በተደጋጋሚ ስላቅ እያቀረበ ስለመሆኑ ያስረዳልኛል ያለውን ሌላኛ የድራማ ክፍል ቀንጭቦ ሊንኩን አያይዟል። “…ኮሎኔሉ የወረዳው ሊቀመንበር ወጣቶችን አስተባብሮ ሥልጣን አለቅም አለ” ይላል።

ሌላኛው ገፀባህርይ መልስ ሲሰጥ “…እሱ አይደለም እንዴ ከእኔ የተሻለ ብቁ ሰው ከመጣ ሥልጣኔን እለቃለሁ ሲል የነበረው…” የሚል ምላሽ ይሰጣል።

እናም ጀዋር መሐመድ ድራማው ለምን የፓለቲካ ሳታየር ሆኖ ሊታየው ቻለ የሚል ክርክር ማቅረብ አልፈልግም። ነገር ግን ጥቃቅን ሀሳቦችን በመገጣጠም ድራማው ሊያስተላልፈው የፈለገውን መልእክት አንሻፎ ለራስ የፓለቲካ አላማ ወደማቅረብ መሸጋገሩ የድራማውን አዘጋጆችና ተከታታዮች ከማሳዘን ያለፈ ውጤት ያለው አይደለም።

ምናልባት በጀዋር እሳቤ የቤቶች ድራማ የተቆነፀለ መልእክት እነጠ/ሚ አብይ አህመድን ሸንቆጥ ያደርጋል በሚል ትርጓሜ ያገኘ መስሎ ታይቶኛል። ብልፅግናዎችን በመሸንቆጥ ድራማው የፓለቲካ አላማ ማራመጃ አድርጎ በማቅረብ ጠልፎ ለመጣል የሄደበት ርቀት ግን በግሌ አሳዝኖኛል።

እንደሚታወቀው ቤቶች ድራማ ከአምስት አመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረ የቤተሰብ ድራማ ነው። ቤተሰብ ብዙውን ጊዜ የአገር ተምሳሌትም ነው።በየራሳችን ቤት ስለውሏችን፣ ስለገጠመኛችን፣ ስለደስታችን፣ ስለሐዘናችን፣ ስለኑሮአችን፣ ስለፓለቲካችን… ሀሳብ መለዋወጣችን የተለመደ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ነው። በቤቶች ድራማም የዚሁ አጠቃላይ እውነታ ነፀብራቅ ነው። የእለት ተእለት ህይወታችንን አዝናኝ በሆነ መልኩ አጣፍጦ ማቅረብ።

ባለፈው ቅዳሜ የተላለፈው ወደ34 ደቂቃ ገደማ የሚወስደውን የቤቶች ድራማ ሙሉውን ለተመለከተ የጀዋር አረዳድ የተሳሳተና ከጭብጡ የወጣ መሆኑን ይገነዘባል። እንዲያውም በድራማው አንድን ወጥ (ምግብ) ለመስራት የተለያዩ የቤተሰቡ አባላት ተሰብስቦ በቡድን እንዲደራጅ መደረጉን ያሳይና መደራጀታቸው እና የደቦ ወጥ ወደመስራት መሸጋገራቸው የቱን ያህል ቀውስ እንደፈጠረ ያሳያል። የተሰራው ወጥ በበርበሬ ፈንታ ሚጥሚጣ ተሞጅሮበታል፤ ሁሉም ቡድን የጨመረው ጨው ከልክ በላይ በመሆኑ የተመገቡት የቤተሰብ አባላት መታመማቸውን ያሳያል። ይኸ ለእኔ የታመመው ፓለቲካችን ነፀብራቅ ወይንም አብነት ነው። በአጭሩ መልእክቱ በግርግር፣ በጨረባ ተዝካር ውጤት ማግኘት እንደማይቻል ጠቋሚ ነው። ውድ አንባቢዬ ሆይ ይኸም ትርጉም የእኔ የአንድ ተመልካቹ እንጂ ድራማው ሊያስተላልፈው የፈለገው ጭብጥ አድርጎ መውሰድ እንደማይቻል እንዳትዘነጋብኝ እፈልጋለሁ።

በመጨረሻም፤ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የለውጥ ማኔጅመንትም በጀዋር የተንኮል መልእክት መደናገጥ ውስጥ ገብቶ አንድ ለእናቱ የሆነውን የቤተሰብ ድራማ ያሰናክላል ብዬ አላምንም።እንዲያውም በተቃራኒው ሕገመንግሥታዊውን የሀሳብ ነፃነትን በማክበር አዘጋጆቹ ሥራቸውን አጠንክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ የእነጀዋርን ሴራ ያከሽፋል ብዬ እየጠበኩኝ ነው።

ደህና ሰንብቱልኝ!

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top