Connect with us

በቴሌ ዘመናዊ ቁማር እየተራቆትን ይሆን?

በቴሌ ዘመናዊ ቁማር እየተራቆትን ይሆን?
Photo: Social media

ሳይንስና ቴክኖሎጂ

በቴሌ ዘመናዊ ቁማር እየተራቆትን ይሆን?

በቴሌ ዘመናዊ ቁማር እየተራቆትን ይሆን?
(ጫሊ በላይነህ)

ኘሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ “አጭሬ” የሚሏት ግጥም አለቻቸው። ብዙ ጊዜ በሁለት መስመር እምቅ ሀሳብ የሚገለፅባቸው ናቸው። ኢትዮ ቴሌኮምም አጭሬ ቁጥሮች አሉት፤ ልክ ለአባይ ግድብ ድጋፍ እንደሚሰባሰብበት “8100” አይነት።

እነዚህ አጭር ቁጥሮች የትልቅ ቢዝነስ ምንጭ ናቸው። ትዳር አገናኛለሁ ከሚለው ደላላ ጀምሮ አስተያየታችንን እንደሚናፍቅ በየደቂቃው ከሚናዘዝ የራዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያ አዘጋጆች ድረስ ያለው ውትወታው ለጉድ ነው። ደግሞም ከሚያስገኘው የዳጎሰ ገቢ አንፃር ሲመዘን ጉትጎታው ሲያንስ ያሰኛል። ያው በቀላሉ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የሚካሄድ የገንዘብ ፈለጣ በለው።

ለአንድ መልዕክት በትንሹ ሶስት ብር የሚቆረጥ ቢሆን ቴሌ የራሱን ኮምሽን ወስዶ ለባለቤቶቹ የሚሰጠው ገንዘብ ወፍራም መሆን ቢዝነሱ የብዙዎችን ትኩረት እንዲስብ ያደረገው ይመስለኛል። እስቲ አስበው?!.. በአንድ መልእክት አንድ ብር ተገኘ ቢባል እና መልእክቱ በጣም በትንሹ ለአንድ ሚልየን ስልኮች ተላልፎ ቢሆን አጫዋቹ በቀላሉ ሚልየነር ሆነ ማለት አይደለምን?

መነሻዬ የአጭር መልእክት በስልካችን መንጋጋት፣ አልፎ አልፎም ሳንስማማ ገንዘባችን መቆረጥ አሳሳቢነቱን ለማንሳት ነው። ይኸቺን አጭር መልእክት እየፃፍኩኝ ወደስልኬ የተላኩ ልዩ ልዩ መልእክቶችን እየቃኘሁ ነበር።

“ የማሰብ ክህሎቶን ለማዳበር የሚጠቅሙ የጠቅላላ ዕውቀት መረጃዎችን ማወቅ ከፈለጉ OK ፊደሎችን ወደ 6901 በነፃ ይላኩ” ይላል አንደኛው።

ሌላኛው 6165 “ድንቃድንቅ እና አስገራሚ መረጃዎችን ለማግኘት ok ብለው ይላኩ” ይላል።
ልብ በል!..ይኸን በመላኬ ስንት ብር ቻርጅ እንደሚያደርገኝ በመልእክቱ አልተነገረኝም። ምናልባት በአንድ አጭር መልእክት ሶስት ብር ሊሆን ይችላል። አምስት ወይም አስር ብር ሊሆን ይችላል።እናም ግልፅነት አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከፍዬም የማገኘው መረጃ ጥራት የቱን ያህል ነው የሚለው የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ያሳስባል።
እነዚህን ለአብነት ያህል አነሳሁ እንጂ ስልካችን የተሸከመው ጉድ እጅግ ብዙ ነው።

በጣም በቅርብ አንድ ያሰለቸኝን አጭር ቁጥር መልእክቱ እንዲቆምልኝ “STOP” የሚለውን ተጭኜ መልእክት ሰደድኩኝ።ቴሌ በ900 ቁጥር በጥያቄዬ መሰረት መቆሙን የሚያበስርና ይህንን ጥያቄ በማቅረቤ አንድ ብር መክፈሌን የሚገልፅ አጭር መልእክት ሰደደልኝ። ሳልፈልግ የተላከልኝን መልእክት ለማስቆም እንደገና በመክፈሌ እየተብሰለሰልኩኝ ውሎ ሳያድር ያው መልእክት ተመልሶ መምጣቱን ስመለከት ደንግጫለሁ፣ አዝኛለሁም። ይኸን ክስተት እንደተራ ገጠመኝ ልወስደው አልቻልኩም። ገጠመኙ ቴሌ ያለፍላጎቴ እየነገደብኝ ነው ወደሚል ድምዳሜ ወስዶኛል።

ከምንም በላይ ያሳሰበኝ ሳልፈቅድ አስተዋፅኦ ማድረጌን የሚገልፅ መልእክት በተደጋጋሚ ወደስልኬ እየመጣ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ቁጥሩ ለጊዜው ይቆየኝና በተደጋጋሚ “…እናመሰግናለን” የሚል መልእክት ይላካል። ግን መቼ ልኬ ነው? የሚለው መልስ ላገኝለት አልቻልኩም። እንዲያውም ቢቸግረኝ ባለቤቴን “ሳትነግሪኝ በስልኬ የላከሽው መልእክት አለ እንዴ?” ብዬ እስከመጠየቅ አድርሶኛል። እናም በአጭሩ ኢትዮ ቴሌኮም ለበላተኛ አሳልፎ ሰጥቶኝ ይሆን? የሚል ጥርጣሬዬ አይሏል። ውድ አንባቢ ሆይ፤ ስለጉዳዩ ብንወያይበት ምናልባት ኢትዮ ቴሌኮም ጠቃሚ ግብአት እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል እላለሁ።
ደህና ሰንብቱልኝማ!!

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ሳይንስና ቴክኖሎጂ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top