Connect with us

ኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝኀነትን እንደጦር የሚፈራ አገዛዝ …

ኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝኀነትን እንደጦር የሚፈራ አገዛዝ ለመሸከም ዝግጁ አይደለችም!!

ፓለቲካ

ኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝኀነትን እንደጦር የሚፈራ አገዛዝ …

ኢትዮጵያ የሀሳብ ብዝኀነትን እንደጦር የሚፈራ አገዛዝ ለመሸከም ዝግጁ አይደለችም!!
ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

ድርጅታችን አብሮነት የኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ቸግሮች መፍትሄ የሚያገኙት ከሃገራዊ የምክክር ሂደት (National dialogue) በሚመነጭ የእርቅ እና የአንድነት የሽግግር መንግስት በማቋቋም እንደሆነ አጥብቆ ያምናል። ይህንን ሐሳብ ለአለፉት ሁለት አመታት በፅናት ስናራምደው የነበረ ቢሆንም በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ራሱ ‹‹እመራበታለሁ!›› በሚለው ሕገ-መንግስት መሰረት የስልጣን ዘመኑ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ቢሆንም ገዢው ፓርቲ ‹‹እመራበታለሁ!›› ከሚለው ሕገ-መንግስት ድንጋጌ ባፈነገጠ ሁኔታ በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት በማሳየቱ ምክንያት አብሮነት የሚያራምደው የእርቅና የአንድነት የሽግግር መንግስት አጀንዳ በሃገራችን ፖለቲካ መድረክ ትልቅ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።

ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ከአራት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የምንገኝበትን አገራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ፣ የመድብለ-ፓርቲ ዴሞክራሲ አስተሳሰብን የሚቃረንና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚጋፋ በጥሞና እንድንመለከተው የሚያስገድድ ንግግር አድርገዋል፡፡ ለምሣሌ ያህል ለመጥቀስ በንግግራቸው ፦

1፡ ታዋቂ የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያቀረቡት ያለውን የሃገራዊ ምክክር (National dialogue) ጥያቄ “የፓርቲወች ንትርክ” በማለት አጣጥለውታል።

2፡ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሣቸው “የደም ዋጋ የተከፈለበት” የሚሉትንና የሚምሉበትን ሕገ-መንግስት አና ሕገ-መንግስታዊነት በመጣስ ፓርቲያቸው ብልፅግና ከመስከረም 25 በኋላም በስልጣን እንደሚቀጥል በግላጭ አውጀዋል። ይህ ንግግራቸው የሚያሳየን ነገር ቢኖር የተለየ ሀሳብን እንደጦር የመፍራትና ተፎካካሪን በጠላትነት ፈርጆ ማጥፋት መገለጫው የሆነው “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ” አስተሳሰብ የእርሳቸውና የድርጅታቸው መገለጫ ባህሪ ሆኖ መቀጠሉን ነወ።

የሁለት አመቱ “የእኔ አሻግራችኋለሁ” የብልፅግና ፓርቲ ስልጣን ላይ ቆይታ አሁን ላይ ውሉን ስቶ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚወራው ስለስርአታዊ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሳይሆን ስለ ሃገር ሉዓላዊነትና የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ሆኗል። ከዚህ ሁኔታ በግልፅ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር የሁለት ዓመቱ “የእኔ አሻግራችኋለሁ” ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ መሆኑን ነወ፡። የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ የሚያሳየው ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ አንደሌለው ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከምትገኝበት ውስብስብ የማህበራዊ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር አኳያ አሁን የተያዘውን አካሄድ ማስተናገድ የሚትችልበት ትክሻ የላትም። ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የሰከነ አመራር የተረጋጋና ሰላማዊ ትብብርና አንድነት የምትሻበት የታሪክ መድረክ ላይ ትገኛለች። በመሆኑም ለእኛ በዚህ ዘመን ለምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ሃገራዊ ምክክር (Na”tional dialogue) ምርጫችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም መሆኑን አብሮነት በፅኑ ያምናል። ድርጅታችን አብሮነት ለእርቅ የአንድነት እና የሽግግር መንግስት ጥያቄ ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ የክቡር ጠቅላይ ምንስትሩ የተለየ ሀሳብን ለማዳመጥ ያለመፈለግ፣ የፍረጃ ንግግር፣ እንዲሁም ህዝብን የማደናገርና ጠላት የመፍጠር በአጠቃላይ ‹‹እኔ አውቅላችኋለሁ!›› የሚሉ አመለካከቶችን እንደከዚህ ቀደሙ አጥብቀን የምንታገላቸውና የምንፀየፋቸውም መሆኑን አናረጋግጣለን፡፡

በመጨረሻም ሃቀኛ የፖለቲካ ሐይሎች በኢትዮጵያ ከወጭም ሆነ ከውስጥ ሊመጣ የሚቸለውን አደጋ ከስሜትና ከጊዜያዊ ፍላጎት በመራቅ ገምግመን በድፍረት ወቅቱን የሚመጥን አቋም ካልያዝን እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ነገሮች በራሳቸው ጊዜ ‹‹ይስተካከላሉ!›› ከሚል ምኞትና ያልተጨበጠ ተስፋ በመራቅ የነገሮችን ዕድገት በምክንያትና ውጤት ለክቶ ካልተንቀሳቀሰ መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ በጣም አሳሳቢ ነው። በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሃገር የምንገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪያችንን አናስተላልፋለን ።

ግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top