Connect with us

የእነ በረከት ቅጣት ከጓዶቻቸው ነጻነት ጋር ሲወዳደር

የእነ በረከት ቅጣት ከጓዶቻቸው ነጻነት ጋር ሲወዳደር

ፓለቲካ

የእነ በረከት ቅጣት ከጓዶቻቸው ነጻነት ጋር ሲወዳደር

የእነ በረከት ቅጣት ከጓዶቻቸው ነጻነት ጋር ሲወዳደር
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

እነ በረከት ስምኦንና ካሳ ጥንቅሹ ሲያስሩበት በኖሩት እሥር ቤት ታስረው ከቆዩ በኋላ ሲያስፈርዱበት በኖሩት ፍርድ ቤት ስድስት እና ሥምንት ዓመት እንደተፈረደባቸው ሰማን፡፡ ከፍርዱ በፊት እነ አቶ በረከት የእሥረኞች አያያዙ ጥሩ አለመሆኑን፣ ኢንተርኔት አለመኖሩን ወዘተረፈ በቅሬታ መልክ እያቀረቡ ችግሩ እንዲፈታላቸው ሲጠይቁ ነበር፡፡ አቶ አብዲ ኢሌ ደግሞ የወህኒ ቤቱ አያያዝ ከመኖሪያ ቤቱ በላይ ሆኖ እንዳገኘውና ይሄም ሁኔታ ለመደመር እንዳነሳሳው ሲናዘዝ ነበር፡፡

የሆነው ሆኖ ግን ከእነ በረከት ቅሬታ ይልቅ የአብዲ ኢሌ እርካታ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም በአሳሪነት ዘመን ያላስተካከሉትን ወህኒ-ቤት እና የፍርድ ሂደት በታሳሪነት ዘመን ቢያብጠለጥሉት ዋጋ የለውም፡፡ በቆፈሩት ጉድጓድ እንደሚባለው ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘ የቀድሞ የሃገራችን ፕሬዝዴንት መንግሥቱ ሐይለማሪያም ላይ የተቀለደች አንዲት ቀልድ አለች፡፡

ከእለታት ባንዱ ቀን መንጌ ሁለት ነገሮችን ለመጎብኘት አቅዶ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲሄድ ለመጽሐፍት ቤት ማስፋፊያ የሚውል የ50 ሺህ ብር በጀት በተጠየቀው መሠረት ልዩ ረዳቱን ማስተዋሻ እንዲይዝ ይነግረዋል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በማምራት አንዳንድ ነገሮችን ከጎበኘ በኋላ ለማረሚያ ቤቱ ማስፋፊያ የሚውል የ50 ሺህ ብር የበጀት ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡

በሌላ ጊዜ ታዲያ ልዩ ረዳቱ የያዘውን ማስተዋሻ በማቅረብ ‹‹ማረሚያ ቤቱ እና ዩኒቨርስቲው የጠየቁትን የ50 ሺህ ብር በጀት እንዴት እናድርገው?›› በማለት ሲጠይቅ መንጌ ‹‹ለዩኒቨርስቲው 50 ሺህ ብር፣ ለማረሚያ ቤቱ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር በጀት እንዲሠጣቸው ለፋይናንስ ጻፍላቸው›› ይለዋል፡፡

በዚህን ጊዜም ልዩ ረዳቱ ‹‹50 ሺህ ብር ለጠየቀ ማረሚያ ቤት አንድ ሚሊዮን የሚሰጠው ስለምን ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ መንጌ የሠጠው አጭር መልስ ‹‹ምን ነካህ! ከዚህ ቤተ-መንግሥት ስንወጣ እኮ የምንገባው ቃሊቲ እንጂ ዩኒቨርስቲ አይደለም›› የሚል ነበር፡፡

ምን ለማለት ነው?
በአመራርነት ዘመናቸው ፒንሳ የያዘ መርማሪ ሲያስገቡበት ከኖሩት ወህኒ-ቤት ታሳሪ ሆነው ሲገቡ ኢንተርኔትም ሆነ ምቾት መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡

ይሄን ብለን ከእሥራቱ ወደ ቅጣቱ ስንመጣ በእነ አቶ በረከት ላይ የተላለፈውን ፍርድ ከወንጀላቸውና ከጓዶቻቸው አንጻር መመልከት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

በመሆኑም የእነ አቶ በረከት ቅጣት ሲፈጽሙት በኖሩት ጥፋት ሲመዘን ምህረት ተደረገላቸው እንጂ ተፈረደባቸው ማለት አይቻልም፡፡ በእነ በረከት ዘመን እነታምራት ላይኔ እና ሥዬ አብርሐ የተላለፈባቸውን ውሳኔ ስናስበው ሰዎቹ በጭካኔያቸው ልክ ተጨክኖባቸዋል ማለት ይከብዳል፡፡ ያም ሆኖ ግን በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ አስተያየት ለመስጠት የተከሰሱበትን የክስ አይነት ማወቅና የሕግ ችሎታንም የሚጠይቅ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ብዙ ማለት አይቻልም፡፡

የእነ በረከትን ቅጣት ከሥልጣን ጓዶቻቸው አንጻር ካየነው ግን ፍርዱ አነሰ ተብሎ ቅሬታ የሚቀርብበት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ከእነ አቶ በረከት ባልተናነሰ መልኩ በሙሰኝነታቸውም ሆነ በግፋቸው የሚታወቁ ስንትና ስንት አመራሮች ሊከሰሱ ሲገባቸው ከሳሽ ሆነው፣ ሊፈረድባቸው ሲገባ ፈራጅ ሆነው አሁንም ድረስ አገሪቱን እያወኩ ነውና…

ሌላው ቀርቶ አቶ በረከት በመጽሐፋቸው የጠቃቀሷቸው ሙሰኞችና ማፊያዎች….ያለምንም ተጠያቂነት በጡረታ መሰናበታቸው ለክብራቸው የማይመጥን ሆኖባቸው ነጻ ያደረጓቸው አመራሮች አስወግደው ወደ ቤተ-መንግሥት ለመመለስ ሲያስቡ እየታዘብን ነውና…

በመሆኑም አሁን ከተፈረደባቸው አመራሮች ባልተናነሰ መልኩ…. ፕሮጀክቱን ትተው በጀቱን ሲከፋፈሉ፣ አጥፊውን ትተው ንጹሐንን ሲበድሉ፣ ብልት ሲሰልቡና ጥፍር ሲነቅሉ፣ ወጣቶችን ሲገድሉና አገር ሲከፋፍሉ የኖሩ እልፍ አዕላፍ ማፊያዎች የእጃቸውን ሳያገኙ በነጻነት በሚፎክሩባት አገር ላይ ‹‹የእነ አቶ በረከት ቅጣት አነሰ›› እያሉ መቆላጨት የወደቀ ግንድ ላይ ምሣር እንደ ማብዛት ነው፡፡

ምክንያቱም በርካታ ጓዶቻቸው ወደ እሥር ቤት ቀርቶ ከአመራርነት አልወረዱም፡፡ የሚቀጣቸው ይቅርና ከጥፋታቸው የሚያስቆማቸው ዳኛ አላገኙም፡፡ ሲፈጽሙት በኖሩት ግፍ ወደ ወህኒ መውረድ ሲገባቸው እስካሁን ድረስ ከሕግም ሆነ ከኅሊና ቅጣት ነጻ ሆነው መድረክ ላይ እየፈነጩ ናቸው፡፡ ሕግ የሚያስከብር መንግሥት ቢኖር ኖሮ ወደ ከርቸሌ የሚወረወሩት ሁሉ ‹‹አሁን ያለው መንግሥት ሕግን ማስከበር የሚችል አይደለምና ሥልጣኑን ያስረክብ›› እያሉ ናቸው፡፡

በመሆኑም የእነ በረከትን ቅጣት ከጓዶቻቸው ነጻነት ጋር ስናወዳድረው ይበልጥ የሚያናድደው የወደቁት ዛፎች ሳይሆን አሁንም የጥፋት ፍሬዎችን እያፈራ ያለው ግዙፍ ጫካ ነው፡፡

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top