Connect with us

ይድረስ ለተከበሩ የትግራይ ፓርላማ አባላት

ይድረስ ለተከበሩ የትግራይ ፓርላማ አባላት

ፓለቲካ

ይድረስ ለተከበሩ የትግራይ ፓርላማ አባላት

ይድረስ ለተከበሩ የትግራይ ፓርላማ አባላት
==

ጉዳዩ፦ ሕገ መንግስት ስለመተርጎም!

(አብርሀ ደስታ)

በመጀመርያ ከናንተ የተለየ የፖለቲካ አመላካከት ቢኖረኝም ለናንተ ያለኝን አክብሮት መግለፅ እፈልጋለሁ። በሁለት ምክንያቶች፦

(1) በፓርላማ ስብሰባ ማንንም ሳትፈሩ ያመናችሁበትን የፈለጋችሁትን ሐሳብ በድፍረት መናገር በመቻላችሁ አድናቆት አለኝ። በሐሳባችሁ ባልስማማ እንኳን በድፍረት የመሰላችሁትን ነገር እየገለፃችሁ ለብዙ ዓመታት ዶርማንት የነበረውን ፓርላማ ህይወት ዘርታችሁበታልና ክብር ይገባችኋል።

(2) የፈለጋችሁትን ሐሳብ የመናገር መብት ስላላችሁ በፈለጋችሁት መንገድ ብትገልፁት ሐሳባችሁ ባይጥመኝም የመቀበልና የማክበር ግዴታ አለብኝ። የፖለቲካ አመለካከታችሁ ባልደግፈውም የራሳችሁን እምነት የመናገር መብታችሁ አከብራለሁና ቀጥሉበት። እምነታችሁ ባልቀበልም የመናገር መብታችሁ ግን እቀበላለሁ።

ወደ ገደለው ስገባ (የዚህ ፅሑፍ ይዘት ፖለቲካዊ ሳይሆን ትምህርታዊ መሆኑ ይታወቅ)

የሕገ መንግስት ትርጓሜ ጉዳይ ሰሞነኛ አጀንዳ ሆኗል። አሁን ላጋጠመን ችግር መፍትሔ “የሕገ መንግስት ትርጉም መጠየቅ ነው” ሲል እናንተ ያላችሁበት የተከበረው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ወስኗል። ተቃውማችሁታል። መብታችሁ ነው። ውሳኔያችሁም አከብራለሁ።

ግን የተቃወማችሁበት ምክንያት (አሁን በትግ ቲቪ እንደሰማሁት)

“ምርጫን ለማራዘም የተወሰነው ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ውሳኔ ሕገ ወጥ ነው። ሕገ መንግስቱ ለትርጉም የተጋለጠ አይደለም። ትርጉም ሚያስፈልገው አሻሚ ቃል ወይ አንቀፅ የለም። ተተርጉሞ ያደረ ነው። ሕገ መንግስቱ ግልፅ ነው ወዘተ”

ብላችኋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ልስጥ። እናንተን ለመቃወም ሳይሆን አድማጭ እንዳይደናገር ለመርዳት ብዬ ነው።

መንደርደርያ

ምርጫን ለማራዘም ታስቦ አይደለም የሕገ መንግስት ትርጉም የተጠየቀው። ምርጫ የተራዘመው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስለወሰነ ሳይሆን ምርጫን የማስፈፀም ሕጋዊ ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሀገራዊው ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በመገንዘቡ እና ውሳኔው ለሚመለከተው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በማቅረቡ ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትም የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተቀብሎ አፀደቀ። ምርጫ የማይደረግ ከሆነ ለሚፈጠረው የመንግስት ስልጣን ክፍተት ለመሙላት ምን ቢደረግ ይሻላል ካለ በኋላ “የህገ መንግስትን ትርጉም መጠየቅ” ተገቢ ሆኖ አገኘው።

የሕገ መንግስት ትርጉም

አንድ

ግልፅ ያልሆኑና አሻሚ ቃላት ወይ አንቀፆች ሲኖሩ

በመጀመርያ ማንኛውም (ዘመናዊ) ሕገ መንግስት ሲወጣ በተቻለ መጠን ሙሉ፣ ግልፅና የማያሻሙ ቃላትና አንቀፆች የያዘ ነው ወይም የያዘ መሆን አለበት። ግልፅ ነው፡ የጎደለ ቃልም አንቀፅም የለውም።

ሕገ መንግስት ሙሉና ግልፅ ሆኖ አንዴ ከወጣ በኋላ በግዜ ሂደት አዲዳስ ሁኔታዎች ይፈጠሩና ግልፅ የነበሩም አሻሚ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሙሉ የነበረውም ጎደሎ ይሆናል። በዚሁ ግዜ አሻሚ የሆኑ አንቀፆች ይተረጎማሉ፤ የጎደለ አንቀፅም ይተረጎማል ወይም ማሻሻያ ይደረጋል።

በአንድ ወቅት ግልፅና ሙሉ ሆኖ የረቀቀውን ሕገ መንግስት በግዜ ሂደት (አዳድስ ክስተቶች) አሻሚነቱም ጎደሎነቱም እየተጋለጠ ስለሚሄድ በመተርጎም ወይም በማሻሻል እየታደሰ ከግዜው ጋር እየዘመነ ህያው ሰነድ (Living Document) ሆኖ ለዘመናት ያገለግላል።

ሁለት

የስልጣን ክፍፍል

በፌደራል ስርዓት አወቃቀር ሕገ መንግስቱ ለፌደራል መንግስትና ለክልሎች ስልጣን ያከፋፍላል። (1) የተወሰነ ስልጣን ለፌደራል መንግስት (2) የተወሰነ ለክልሎች (3) የተወሰነ የጋራ (4) የተወሰነ በሕገ መንግስቱ ያልተካተተ (Residual Power) ስልጣን ደግሞ ላንዱ ይሰጣል። በግልፅ ቋንቋ ያከፋፍላል። ሁሉም የየራሱ ስልጣን ይጠቀማል።

በግዜ ሂደት ግን አዳዲስ ሁኔታዎች ስለሚፈጠሩ አዳዲስ የስልጣን ምንጮች ስለሚኖሩ በክልሎችና በፌደራል መንግስት መካከል የስልጣን ይገባኛል የሕገ መንግስት ክርክሮች ይነሳሉ። የሕገ መንግስት ትርጉም ይጠየቃል። አዳዲስ ክስተቶች የሕገ መንግስቱ ቃላት ወይም አንቀፆችን ለትርጉም ያጋልጣሉ።

ሦስት

ሌሎች ሕጎችና አዋጆች

ሕገ መንግስት የሁሉም ሌሎች ሕጎችና አዋጆች የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም የሚወጣ ሌላ ሕግ ወይ አዋጅ ከሕገ መንግስቱ መርሆዎች ወይ አንቀፆች ጋር የሚፃረር መሆን የለበትም። ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን አንቀፅ የያዘ ሕግ ወይ አዋጅ ከወጣ ሕጉ ወይም አዋጁ ውድቅ ይሆናል። አንድን ሕግ ወይ አዋጅ ከሕገ መንግስቱ ጋር ይቃረናል ወይ አይቃረንም የሚለው ክርክር በሕገ መንግስት ትርጉም ይፈታል።

አራት

የሕገ መንግስት ዝምታ ክፍተት

መጀመርያ ሕገ መንግስት ሲረቀቅ ሙሉ እንደሆነ ታስቦ ነው ብለናል። በግዜ ሂደት ግን አዳዲስ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ እናስታውስ። ለምሳሌ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ሙሉ ነው (ሁሉንም ጉዳዮች ይዳስሳል) ተብሎ ግልፅ በሆነ ቋንቋ ተቀምጧል። ግን አሁን ስላጋጠመን ችግር ምን ይላል?

በኢፌድሪ ሕገ መንግስት መሠረት የመንግስት ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ነው። የሚመረጡ የህዝብ ተወካይ አባላት የስልጣን ዘመን አምስት ዓመት ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል።

ከዓቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ በተያዘለት ቀነ-ገደብ ባይካሄድና ቢራዘም የነባሮቹ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት የስራ ዘመን ካለቀ ግዜ ጀምሮ የተራዘመውን ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ባለው የሽግግር ግዜ የመንግስትን ስልጣን በማን እጅ እንደሚቆይ ሕገ መንግስቱ ምንም አይልም። ሕገ መንግስቱ መጀመርያ ሲያረቁ ስለዚህ ጉዳይ አላሰቡበትምና ይህንን ክፍተት የሚሞላ አንቀፅ አላካተቱም።

አሁን ላጋጠመን ችግር መፍትሔ የሚሆን አንቀፅ የለም። በሌላ አባባል ሕገ መንግስቱ ለዚሁ ጥያቄ መልስ የለውም። ሕገ መንግስቱ ዝም ብሏል። በዚህ ምክንያት የሕገ መንግስት ዝምታ ክፍተት አጋጥሟል። ድሮ ሙሉ የነበረውን ሕገ መንግስት በግዜ አጋጣሚ በተፈጠረ አዲስ ክስተት ምክንያት ጎደሎ መሆኑ ተጋልጧል።

(የየትኛውም ሀገር ሕገ መንግስት በግዜ ሂደት ጎደሎነቱ ይጋለጣል። በማሻሻልና በትርጉም ይሞላል)

አሁን ጎደሎውን አንቀፅ (የሕገ መንግስቱ ዝምታ ክፍተት) በምን ይሞላ? ትርጉም በመጠየቅ? ይቻላል! እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም የሕገ መንግስት ትርጉም መጠየቅ ሕገ መንግስታዊ ነው!

ስለዚህ የሕገ መንግስት ትርጉም የሚጠየቀው የሕገ መንግስቱ አንቀፆች ወይ ቃላት አሻሚ ወይም ግልፅ ሳይሆኑ ሲቀሩ ብቻ ሳይሆን በአዳዲስ ክስተቶች ምክንያት የሕገ መንግስት ዝምታ ክፍተት ሲፈጠርም ነው። ሕገ መንግስቱ የሚተረጎም ለመናድም አይደለም፤ ህያው ለማድረግ እንጂ።

በልዩ ሁኔታ ምክንያት ባሉ የሕገ መንግስቱ አንቀፆች የማይመለስ ችግር ሲያጋጥም ግልፅ የሆኑ አሻሚ ያልሆኑ የነበሩ የሕገ መንግስቱ አንቀፆች በሙሉ ለሕገ መንግስት ትርጓሜ ይጋለጣሉ!

የተከበራችሁ የትግራይ የፓርላማ አባላት ሆይ! በዚሁ እንድትረዱት ሙያዊ ምክሬን ለግሻለሁ።

አክባሪያችሁ!

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top