Connect with us

“የሰራተኞችን ደመወዝ የመቀነስም ሆነ የማባረር እቅድ የለኝም” – የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የሰራተኞችን ደመወዝ የመቀነስም ሆነ የማባረር እቅድ የለኝም… የኢትዮጵያ አየር መንገድ
ፎቶግራፍ በሳሞ አሊ

ኢኮኖሚ

“የሰራተኞችን ደመወዝ የመቀነስም ሆነ የማባረር እቅድ የለኝም” – የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) እያሳደረ ባለው ጫና የሰራተኞችን ደመወዝ የመቀነስም ሆነ ሰራተኛ የማባረር እቅድ የለኝም አለ።

አየር መንገዱ በወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴውና በሰራተኛ አያያዝ ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተሰራጩ ባለው ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የአየር መንገዱ ኮርፖሬት የሰው ሃብት አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ዋሲሁን አስረስ እንዳሉት፤ በአለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አየር መንገዱ ጫና ደርሶበታል።

በዚህም ከነበሩት 127 መዳረሻዎች 90 በመቶ በረራ ለማቆም በመገደዱ ገቢውም በዛው ልክ ቀንሷል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተወዳዳሪ የነበሩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ ኤምሬትስ፣ ኳታርና ሌሎች አየር መንገዶች በወረርሽኙ ጫና ምክንያት ሰራተኞቻቸውን እየቀነሱ እንዲሁም ደመወዝ እየቀነሱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚከተለው ስትራተጂ የተለያዩ አማራጮችን በማየት ህልውናውን ለማስቀጠል እንዳስቻለው ያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በካርጎ፣ በአውሮፕላን ጥገና እንዲሁም በቻርተርና በሌሎች የገቢ አማራጮችን በማየት እየሰራ በመሆኑ ለሰራተኛው ደመወዝ መክፈል አለማቆሙን ጠቁመዋል።

ትርፋማና ተወዳዳሪ የሚባሉ የአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያ፣ አፍሪካ አየር መንገዶች ወረርሽኙ ባሳደረባቸው ጫና ምክንያት ሰራተኞቻቸውን እየቀነሱና እያሰናበቱ መሆኑን አውስተዋል።

ለአብነትም የአሜሪካ አየር መንገድ አንድ ሶስተኛ የአውሮፕናን አብራሪዎቻቸውን ቀንሰዋል፤ የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ የአብራሪዎቻቸውን ደመወዝ 45 በመቶ ለመቀነስ መወሰናቸውን ጠቅሰዋል።

የእንግሊዙ ብሪቲሽ ኤርዌይስ 12 ሺህ ሰራተኞችን ሊቀንስ መሆኑንም የገለጹት አቶ ዋሲሁን፤ ”የኢትዮጵያ አየር መንገድ አማራጮችን ያያል እንጂ ሰራተኞችን የመቀነስ እቅድ የለውም” ብለዋል።

አየር መንገዱ ሰራተኞቹን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እያቀረበ ሲሆን ሰራተኞች ስለበሽታው ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተለያዩ ዘዴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ እንደሆነም ተነግሯል።

ከስራ ባህሪያቸው አንጻር ራሳቸውን ለይተው ማቆየት ለሚፈልጉ ሰራተኞችም ለይቶ ማቆያ መዘጋጀቱን አቶ ዋሲሁን ጨምረው ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ የቀዳማዊ ሰራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ተድላ ደሬሳ በወረርሽኙ ምክንያት የሰራተኞች ጥቅም እንዳይነካ ከተቋሙ ሃላፊዎች ጋር እየሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአየር መንገዱ ከ7 ወር በፊት የተመሰረተው ማህበር ‘ለሰራተኛው የቆሙኩ ህጋዊ ማህበር እኔ ነኝ” በሚል በመገናኛ ብዙሃን በሰራተኞች ላይ በደል እየተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ እያሰራጨ ያለው መረጃ ከእውነት የራቀ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

”በመሆኑም ማህበሩ የሰራተኞችን መብት በመጠበቅና ከወረርሽኙ ተጽእኖ በመውጣት በአለም ደረጃ ያለውን ስም እናስቀጥላለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉት 16 ሺህ ሰራተኞች የተወሰኑ ስራ ላይ ሲሆኑ የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የተወሰኑ እረፍት ላይ ሆነው ደመወዘ እየተከፈላቸው መሆኑም ተገልጿል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአየር መንገዶች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ በዚሁ ከቀጠለ በመላው ዓለም በኢንዱስትሪው ላይ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ሊደርስ እንደሚችል የአለም አቀፍ አየር መንገዶች ማህበር ትንበያ ያሳያል።

ምንጭ :- ኢዜአ

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top