Connect with us

ኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ህሙማንን የመጨረሻ ኑዛዜ የምትቀበለው ነርስ

ኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ህሙማንን የመጨረሻ ኑዛዜ የምትቀበለው ነርስ
Photo: Facebook

ጤና

ኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ህሙማንን የመጨረሻ ኑዛዜ የምትቀበለው ነርስ

 

በኮቪድ-19 በጠና ለታመሙ ህሙማን የኦክስጅን መተንፈሻ ማሽን (ቬንትሌተር) ድጋፍ በህይወት እንዲቆዩ ለማድረግ ይረዳል።

ምንም እንኳን ቬንትሌተር በህይወት እንዲቆዩ ቢያግዝም፣ በጠና በታመሙት ዘንድ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ቢያመጣም ህይወትን መቀጠል አያስችለውም።

እናም የመጨረሻዋ ደቂቃ ስትቃረብ፣ በማሽንም መተንፈስ ሲያዳግት፣ ማሽኑ ሊነቀል ግድ ይላል። ወደ ሞት እየሄዱ ላሉ ህሙማን ምን አይነት ስሜት ይኖረው ይሆን? ማሽኑን ለሚነቅሉት የጤና ባለሙያዎችስ?

በለንደን ሮያል ፍሪ ሆስፒታል በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ለምትሰራው ዋና ነርስ ጁዋኒታ ኒትላ በአብዛኛው መተንፈሻ ማሽኖችን መንቀል የሥራዋ አንድ አካል ነው።

በብሔራዊ የጤና አገልግሎት በፅኑ ህሙማን ልዩ ነርስ በመሆንም ለአስራ ስድስት ዓመታት ያህል አገልግላለች።

ነገር ግን ጊዜው ሥራውንም ሆነ የሚሰማትን ስሜት አላቀለለውም።

“ልብ የሚሰብር ነው፣ ህመሙም ጠልቆ ይሰማኛል” የምትለው የ42 ዓመቷ ጁዋኒታ “አንዳንድ ጊዜም ለእነዚህ ሰዎች ሞት ተጠያቂ ነኝ ብዬ አስባለሁ” ትላለች።

ኮሮናቫይረስ ሳንባን ከጥቅም ውጭ በሚያደርግበት ጊዜ ቬንትለተሮች የሰውነትን የመተንፈስ ሥርዓት በመቆጣጠጠር እንዲተነፍሱ ይረዳሉ።

ህሙማኑም በሽታውን እንዲታገሉና እንዲያገግሙም ያግዛቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህ ሁሉ በቂ የማይሆንበት ሰዓት አለ።

ህሙማኑም ሳይሻላቸው ሲቀር፣ ከቀን ወደ ቀን ሁኔታቸው ሲብስ የጤና ባለሙያዎችም ምን እንደሚወስኑ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ይገባሉ።

የሞትና የህይወት ጉዳይም ስለሆነ ማሽኖችን ለመንቀል የህሙማኑን የተለያዩ መረጃዎች ከግምት ውስጥ ያስገባሉ። የህሙማኑ እድሜ፣ ተደራራቢ ህመም ካለባቸው፣ ቫይረሱን መቋቋምና ማገገም መቻል አለመቻላቸውን በተመለከተ ያሉ መረጃዎች ያጤናሉ።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የጠዋት ፈረቃዋን ልትጀምር ባለችበት ወቅት በሃምሳዎቹ እድሜ ላይ ለምትገኝ የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ ነርስ ህክምና ማቆም እንዳለባት ተነገራት።

ካለው የኮሮናቫይረስ ስጋትም ጋር ተያይዞ የነርሷ ልጅ ሆስፒታል ባለመገኘቷ ጁዋኒታ ማድረግ የቻለችው ደውላ ህክምናውን ሊያቆሙ እንደሆነና እንደምትሞትም ነገረቻት።

“እናቷ ህመም ላይ እንዳልሆነችና፣ ፊቷም ላይ ሰላም ይነበብባታል ብዬ አረጋገጥኩላት” የምትለው ጁዋኒታ “እናቷ ከእምነቷ ጋር ተያያይዞ እንዲፈፀም የምትፈልጋቸው ጉዳዮችም ካሉ ጠየቅኳት” ትላለች

ህመምተኛዋ የተኛችበት ክፍል ስምንት አልጋዎች ያሉት ሲሆን፤ ሁሉም ራሳቸውን የማያውቁና በጠና የታመሙ ሰዎች ናቸው።

“ህመምተኛዋ ያለችበትን መጋረጃ ዘጋሁ፣ የመጥሪያ ደወሎቹንም አጠፋሁ” ትላለች።

የጤና ባለሙያዎቹም በዝምታ ተዋጡ፤ ክፍሉም ፀጥ፣ ረጭ አለ።

“ወደ ህመምተኛዋ ጆሮም ስልኩን አስጠጋሁና ልጇን እንድትናገር ጠየቅኳት።”

ከዚያም በልጇና በቤተሰቦቿ ጥያቄ መሰረት የመረጡትን ሙዚቃ እያጫወትን የመተንፈሻ ማሽኑን ከህመምተኛዋ ላይ አላቀቅነው።

“በመቆጣጠሪያው ላይ ብርሃን ብልጭ፣ ብልጭ ይላል፤ ከዚያም የልብ ምቷ ዜሮ፣ በሰሌዳው ላይም ቀጥ ያለ መስመር ሆነ።”

“ከዚያም አጠገቧ ሆንኩና እጆቿን ጨብጬ እስክትሞት ጠበቅኳት” ትላለች ሃዘን በተሞላ ድምፅ።

ህመምተኛዋም ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ህይወቷ አለፈ፤ ጁዋኒታ ከህመምተኛዋ ጋር የተገናኙ ቱቦዎችን ነቃቀለች።

ይህ ሁሉ ሲከናወን የህመምተኛዋ ልጅ በስልክ እያወራች ነበር፤ ከዚያም ሁሉ ነገር እንደተፈፀመ አረዳኋት።

“ከአንድ የሥራ ባልደረባዬም ጋር በመተባበር ገላዋን አጠብናት። በጨርቅ ጠቀለልናትና ለአስከሬን በተቀመጠው ሳጥን ውስጥ አድርጌ ከመዝጋቴ በፊት ግንባሯ ላይ የመስቀል ምልክት አደረግኩ” ትላለች።

የማያቋርጥ ቅዠት

የሚሞቱ ህሙማንን መንከባከብ የኮሮናቫይረስን ቀውስ በተሻለ መልኩ እንድትጋፈጠው አድርጓታል።

ሆስፒታሎች ከሚችሉት ቁጥር በላይ በሚመጡ ህሙማን እየተጨናነቁ ነው። እሷ በምትሰራበት ሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ክፍል ከ34 ወደ 60 አልጋዎች ጨምሯል።

“ከዚህ ቀደም በፅኑ ህሙማን ክፍል አንድ ነርስ ለአንድ ህመምተኛ ነበር እንክብካቤ የሚሰጠው። አሁን ግን አንድ ነርስ ለሦስት ህሙማን ለመመደብ ተገደናል” ትላለች።

“ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉና ከተባባሱ አንድ ነርስ ለስድስት ህሙማን ይሆናል፤ ይህም መቆጣጠር ከምንችለው በላይ ይሆናል” በማለትም ታስረዳለች።

ይባስ ብሎ አንዳንድ ነርሶች የኮሮናቫይረስ ምልክት በማሳየታቸውም ራሳቸውን ለማግለል ተገደዋል።

በዚህም ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትም የሆስፒታል ድጋፍ ሰጪ ነርሶችን በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንዲሰሩም ትምህርት እየሰጠ ነው።

“ሁሌም ሥራ ከመጀመራችን በፊት ተሰባስበን እጅ ለእጅ እንያያዛለን። በህይወት ለመቆየት ተጠንቀቁ እንባባላለን። ከዚያም በሥራ ላይ ስንሆንም አንዳችን የአንዳችንን ጥንቃቄ እንከታተላለን። የፊት ጭምብል፣ ጓንት እንዲሁም ሌሎች የራስ መከላከያዎችን በትክክል ማድረጋችንን በየጊዜው እንቆጣጠራለን” ትላለች

የፅኑ ህሙማን ክፍሉ በቀን አንድ ሞት ይመዘግባል፤ ከወረርሽኙ በፊት ይሄ ተሰምቶ የማይታወቅ ነው።

“በጣም ዘግናኝ ሁኔታ ነው” የምትለው ጁዋኒታ በሆስፒታሉም ዋና ነርስም በመሆኗ ፍርሃቷን ደበቅ ማድረግ አለባት።

“መተኛት ይከብደኛል። ሁልጊዜም እቃዣለሁ። በቫይረሱ እያዛለሁ ብዬ እጨነቃለሁ። ሁሉም ሰው በፍርሃት ላይ ነው ያለው” በማለትም ታስረዳለች።

በባለፈው ዓመት በሳንባ ህመም ምክንያት ለወራት ሥራ አቋርጣ ነበር። ከዚያ በኋላ የሳንባዋ አቅም እንደ ድሮውም እንዳልሆነ ታውቃለች።

“ብዙዎች መስራት እንደሌለብኝ ይነግሩኛል። ግን በዚህ ወረርሽኝ ወቅት እንዴት አድርጌ አቆማለሁ። ሁሉንም ወደጎን ትቼ ሥራዬ ላይ ነው የማተኩረውም።”

“ልክ ፈረቃዬ ሲያልቅ ስለሞቱ ህመምተኞቼ እያሰብኩ ልቤ ስብር ይላል። ከሆስፒታል ስወጣ ደግሞ ስለሌሎች ጉዳዮች ለማሰብ እሞክራለሁ” ትላለች ነርስ ጁዋኒታ።

ነርስ ጁዋኒታ ከቢቢሲ ጋር ቃለመጠይቅ ካደረገች በኋላ ባለባት የጤና ሁኔታ ሆስፒታሉ ቤት እንድትቀመጥ ጠይቋታል። ቢሆንም ቤት ሆ ና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በመሰራትም ድጋፏን ለመቸር አቅዳለች::(BBC)

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top