Connect with us

ወላጆቻቸውን ማንገላታቱ ስለምን ነው?

ወላጆቻቸውን ማንገላታቱ ማለቱ ስለምን ነው?
Photo Facebook

ህግና ስርዓት

ወላጆቻቸውን ማንገላታቱ ስለምን ነው?

መንግሥት ተማሪዎቹ በተጨባጭ ከታገቱ ወንጀለኞቹን፣ ድራማ ከሆነ ደግሞ ተዋናዮቹን ይፋ ማድረግ ሲገባው… ወላጆቻቸውን ማንገላታቱ ማለቱ ስለምን ነው?
(አሳዬ ደርቤ በድሬ ቲዩብ)

ከ12 ዓመታት የትምህርት ቆይታ በኋላ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው፣ ሻንጣቸውን ሸክፈው፣ በወላጆቻቸው ‹‹ሰላም ተመለሱ›› ተብለው ወደ ደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ያመሩ 17? ተማሪዎች ባልታወቀ ጠላፊ ታፍነው ከተወሰዱ ወራቶች ተቆጠሩ፡፡

ይሄንንም የእገታ ዜና ከመንግሥት አንደበት ልንሰማው ሲገባ ከእገታው ማምለጥ በቻለች አንዲት ተማሪ አማካኝት በሶሻል ሚዲያ ይፋ ሆኖ ‹‹ልጆቻችን ይመለሱ›› የሚል ዘመቻና ሰላማዊ ሰልፍ ሲጀመር መንግሥት በቃለ-አቀባዩ አማካኝነት የተምታታ ሪፖርት አቅርቦ የተወሰኑ ተማሪዎችን ማስለቀቁን ተናገረ፡፡ ሆኖም ግን ‹‹ተለቀቁ›› የተባሉትን ተማሪዎች ከወሬ በዘለለ ማንም በአካል ያያቸውም ሆነ ያገኛቸው አልነበረም፡፡

እርግጥ ከጸጥታ አስከባሪዎች በላይ ጸጥታ አደፍራሾች በበዙበትና መረጋጋት በሌለበት አገር ብዙ አስቀያሚ የወንጀል ድርጊቶች ይፈጸማሉና ‹‹ለምን ይህ ነገር ተከሰተ›› ብሎ ማለት ይከብዳል፡፡ ለምሳሌ ያህል ባንድ ወቅት ቦኮሃራም የተባለ አሸባሪ ቡድን 276 የናይጀሪያ ሴት ተማሪዎችን አግቶ መውሰዱ የዓለም ሚዲያዎችን ሲያነጋግር ነበር፡፡

የእኛው እገታ ግን ለየት የሚያደርገው በዓለም ደረጃ ይቅርና እንደ አገርም ቢሆን ከሶሻል ሚዲያ ባለፈ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች፣ የሴቶች መብት ተሟጋቾችና የሴት ሚኒስቴሮች ርዕስ መሆን አለመቻሉ ነው፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እገታው በተግባር የተፈጸመ ሳይሆን ፖለቲካዊ ቁማር እንዲመስል ተደርጎ መቅረቡ ነው፡፡ ‹‹ተማሪዎቹን አግቷል›› ተብሎ የሚጠረጠረው ታጣቂ ቡድን በጃል መሮ አማካኝነት ‹‹አላገትኩም›› ማለቱ፣ ወደ ሥፍራው የሄደው አጣሪ ቡድን ‹‹የልጆቹን ዳና ላገኝ አልቻልኩም›› የሚል መግለጫ መስጠቱ፣ ብሎም ለትምህርት የላኳቸው ተማሪዎች ታግተውብኛል ከሚለው ክልል ውስጥ ‹‹የተወሰኑት ተማሪዎች ተደብቀው ተገኙ›› የሚል የውሸት መረጃ መውጣቱ ዋና ዋናወቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈም መንግሥት የታገቱትን ተማሪዎች ያስለቅቃል ተብሎ ሲታሰብ ከእገታው አመለጥኩ ብላ አብረዋት ስለታገቱት ተማሪዎች መረጃ ያወጣችው ተማሪ በሀሰት መረጃ ሽብር በመፍጠር ተጠርጥራ መታሰሯ በገሃድ የተፈጸመውን ጠለፋ ድራማ እንዲመስል አድርጎታል፡፡

ምንም እንኳን በወቅቱ የታጋች ወላጆች የፌደራል መንግሥት ባቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ስለ ልጆቻቸው መጥፋት ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ መንግሥት የተቻለውን እንደሚያደርግ ቃል የገባላቸው ቢሆንም በተግባር ግን የተጠለፉትን ማስለቀቅ ቀርቶ ጠላፊዎቹንም ማወቅ አልቻለም፡፡ ወይም ደግሞ ማወቅ አልፈለገም፡፡

የሆነው ሆኖ ግን ከጊዜ ብዛት ይህ የጠለፋ ወንጀል እየተረሳሳ ቢመጣም፣ የተማሪዎቹ ወላጆች ግን ልጆቻቸውን ማግኘት ቀርቶ አስከሬናቸውን ተረክበው እርማቸውን ማውጣት አልቻሉም፡፡ አሁን አሁንማ መንግሥት የአጋቹን ማንነት ለይቶ በልጆቻቸው ላይ የደረሰውን ጥቃት ሊነግራቸው ይቅርና አቤቱታቸውንም የመስማት ፍላጎት የለውም፡፡ ልጅ የጠፋቸውን ወላጆች በግ የጠፋቸው ይመስል እረስተዋቸው እንዲቀሩ ሳይፈልግ አይቀርም፡፡

ይሄንንም የተረዳው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እገታውን በራሱ መንገድ ለማጣራት መዘጋጀቱ የሚበረታታ ቢሆንም በመንግሥት በኩል የታየው ቸልታ ግን አስገራሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ጠለፋው በተጨባጭ ከተደረገ እስከ መጨረሻው ድረስ አጣርቶ አጋቾቹንም ሆነ ታጋቾቹን ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ድራማና ፖለቲካዊ ቁማር ከሆነ ደግሞ የዚህ ዓይነቱ ተውኔት ከጠለፋ ድርጊት የማይተናነስ ወንጀል ስለሆነ ተዋናዮቹንና ሴራቸውን መርምሮ ማሳወቅ ብሎም ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ግድ ይለዋል፡፡ ጧት ማታ ‹‹ልጆቻችንን የት አሉ?›› እያሉ የሚያነቡት ወላጆች ተዋናዮች ናቸው ብሎ ካመነ በሕግ ሊጠይቃቸው፣ ካልሆነ ደግሞ ልጆቻቸውን በሕይወት ማስመለስ ባይችል እንኳን ሙት አካላቸውን ሰጥቶ፣ ወንጀለኞቹን ቀጥቶ እንባቸውን ማበስ ይኖርበታል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ‹‹የወንጀሉ ተሳታፊዎችንም ሆነ የድራማውን ተዋናዮች ልደርስባቸው አልቻልኩም›› የሚለው አካሄድ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top