Connect with us

በሰዎች ከመፈራት ተከታይ ወደ ማፍራት የተሸጋገረው እብደታችን

በሰዎች ከመፈራት ተከታይ ወደ ማፍራት የተሸጋገረው እብደታችን
Photo: Social media

መዝናኛ

በሰዎች ከመፈራት ተከታይ ወደ ማፍራት የተሸጋገረው እብደታችን

በሰዎች ከመፈራት ተከታይ ወደ ማፍራት የተሸጋገረው እብደታችን | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

በልጅነታችን የምናውቃቸውን እብዶች ከዛሬ የአእምሮ ሕመም ተጠቂዎች ጋር ስናወዳድራቸው እንደ አገራችን ሁሉ እብደታችንም በሁለት አሃዝ አድጎ እናገኘዋለን፡፡ ብሎም ‹‹እብድ ድሮ ቀረ›› እንዲንል ያደርገናል፡፡ ከዚህ አንጻር አንዳንድ መሥፈርቶችን በማስቀመጥ የበፊቶቹንና የአሁኖቹን እስኪ እናወዳድራቸው፡፡

1. አለባበስ
በልጅነታችን የምናውቃቸው እብዶች ልብሳቸውንና እራሳቸውን ጥለው የሚሄዱ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹እከሌ እኮ አበደ›› ለማለት ‹‹እከሌ እኮ ልብሱን ጣለ›› ወይንም ደግሞ ‹‹ጨለለ›› እንል ነበር፡፡ የአሁኖቹ ግን በባሕል ልብስ ሽክ ብለው፣ ሱፋቸውን ገድግደው፣ ከረባታቸውን አስረው እብደትን የሚጀምሩ በመሆናቸው ዝንጥ የሚሉ እንጂ ልብሳቸውን የሚጥሉ አይደሉም፡፡

2. ሰይጣን
በፊት በፊት የምናውቃቸው እብዶች ሰው የሚደባደቡ፣ ቆሻሻ የሚመገቡ፣ ብቻቸውን የሚያነበንቡ ሲሆኑ በዚህም ባሕሪያቸው ሰይጣን እንዳለባቸው ታምኖ ሰው ይሸሻቸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ፈውስ ፍለጋ ጸበል ይዘዋቸው ይሄዱና አንዳንዶቹ ሲፈወሱ፣ አንዳንዶቹ ግን እንደ ቀወሱ ይቀራሉ፡፡

የአሁኖቹ ግን ፈውስ የሚፈልጉ ሳይሆን ፈዋሽ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ እንደ ቀድሞዎቹ ‹‹ሰይጣን አለባቸው›› ተብለው የሚፈሩ ሳይሆኑ ሰይጣን የሚያባርሩ በመሆናቸው በርካታ ምዕመን ፈውስ ፍለጋ ካሉበት እየሄደ ቀውስ ሆኖ ይመለሳል፡፡

መደባደብን በተመለከተ ደግሞ የድሮዎቹ ግብዳ ድንጋይ አንስተው ሰው የሚፈረክሱ ሲሆኑ የአሁኖቹ ግን ሰዎችን ሳይሆን አጋንንትን በጫማ ጥፊ እያጠናገሩ የሚፈውሱ ናቸው፡፡

3. ሥም እና ሕመም
ከዓመታት በፊት የነበረው የእብደት አይነት ከሰው የሚነጥል፣ ከቆሻሻ ስፍራ የሚያውልና ለብቻ የሚያስወራ ነበር፡፡ እኒህም ሰዎች እብዶች ወይንም ደግሞ ቀውሶች እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡

አሁን ግን ሥሙም ሕመሙም ተቀይሯል፡፡ የዘመናችን እብደት ከሰው የሚቀላቅል፣ መድረክ ላይ የሚያውል፣ ተከታይ ለማፍራት የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም አንዳንዶቹ መስቀሉንና ባንድራውን አንጥልጥለው ‹‹ንጉሳችሁና ንግሥታችሁ እኔ ነኝ›› እያሉ ሲያወሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ መሃረብና ማይክ ይዘው መድረክ ላይ እየተንጎባለሉ ‹‹የጌታ መልዓክ በአካውንታችሁ ብር ሲያስገባ ይታየኛል›› በማለት ሲናገሩ… ተከታዮቻቸው ‹‹አሜን›› ይሏቸዋል፡፡ እኒህንም ሰዎች የዘርፉ ባለሙያዎች ‹‹የአዕምሮ ሕመም ተጠቂዎች›› ሲሏቸው ተከታዮቻቸው ግን ‹‹ነቢያቶችና ነገስታቶች›› ብለው ነው የሚጠሯቸው፡፡ ብቻቸውን ሲያወሩ ቢታዩ እንኳን ከመላዕክት ጋር እየተንሾካሾኩ እንጂ ብቻቸውን እያወሩ ነው አይባሉም፡፡

4. በመኪና መገጨትና እራስን ማጥፋት
የዚያን ዘመን እብዶች እራሳቸው የማያውቁ በመሆናቸው መኪና ሲመጣ ግራና ቀኙን ሳያዩ ተንደርድረው እየገቡ እራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡ ነበር፡፡የአሁኖቹ ግን ቢገቡም የሊሞዚን እና የV-8 መኪናቸውን ጋቢና ከፍተው ነው፡፡ ሞትን በተመለከተ ደግሞ በፊት በፊት ‹‹እከሌ እኮ ጭንቅላቱን ነካ አድርጎት እራሱን አጠፋ›› ሲባል እንሰማ ነበር፡፡ ያሁኖቹ ግን እራሳቸውን ከማጥፋት ይልቅ ጤነኛውን ሕዝብ መቃብር አስቆፍረው አስከሬን ማስነሳት የሚመርጡ ናቸው፡፡

5. እሥራት
የድሮዎቹ አዕምሯቸውን ነካ ባደረጋቸው ቅጽበት ሰው ስለሚፈረክሱ ቤተሰቦቻቸው በገመድና በሰንሰለት እያሰሩ ያሰቃዮቸው ነበር፡፡ የዘመናችን ወፈፌዎች ግን ከሰው ቤት ገብተው ግንባር የሚፈረክሱ ሳይሆኑ ቤተ-መንግሥት ገብተው የሚነግሱ በመሆናቸው ፖሊስ ነው የሚያስራቸው፡፡

ትዝብታችንን ጠቅለል ስናደርገው… ካህሊል ጂብራል ባንድ መጣጥፉ ልክ እንደ እኛ ታማሚውና ጤነኛው ስለተምታታባት አንዲት አገር እንዲህ በማለት ይተርካል፡፡

‹‹ከአንድ ጉድጓድ የሚወጣ ውሃ እየጠጡ አድበው የተቀመጡ ሕዝቦች የሚጠጡት ውሃ ለእብደት በዳረጋቸው ጊዜ አድመው ወደ ቤተ-መንግሥት ያመራሉ፡፡ ንጉሱና አገልጋዮቻቸው ግን የራሳቸው የውሃ ጉድጓድ ስለነበራቸው ሳያብዱ ይቀራሉ፡፡

በጅምላ ያበዱት ሕዝቦች ግን የቤተ- መንግሥቱን ቅጽር ከብበውና መፎክር ይዘው እንዲህ እያሉ ቁጣቸውን ይገልጹ ጀመር፡፡

‹‹ቀውስ ንጉሥ አይመራንም››
‹‹አይመራንም››
‹‹ይሄ እብድ ንጉሥ ከስልጣኑ ይወገድ››
‹‹ይወገድ››

ንጉሱም ይሄንን ሲሰማ ካባውን ደርቦና ዘውዱን ጭኖ ወደ ደጅ ያመራና እርቃናቸውን ተሰባስበው ‹‹አንት ልብስ-ለባሽ ጠሽ›› እያሉ የሚሰድቡትን ሕዝቦች በግርምት እያየ ‹‹ምክንያቱ ምንድን ነው?›› በማለት አገልጋዮቹን ሲጠይቅ ‹‹ውሃው ነው ያሳበዳቸው›› በማለት ይመሉስለታል፡፡

ንጉሡ ‹‹በእብዶች መሃከል ጤነኛ ሆኖ ከመገኘት የሚበልጥ እብደት›› አለመኖሩን ያውቅ ነበር፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ የጠጣው ውሃ እንዲመጣለት ካደረገ በኋላ አገልጋዮቹንና ቤተሰቡን ‹‹ቺርስ›› ሲላቸው ‹‹እንደ ሕዝብ ለመቀወስ›› በማለት ይመልሱለታል፡፡

ከዚያም ውሃውን ተጎንጭተው እብድነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ንጉሡ ካባቸውን፣ አገልጋዮቹ ኮታቸውን መጣል ሲጀምሩ… ሕዝቡ ደግሞ ተቃውሞውን ትቶ ‹‹ቀዉሱ ንጉሣችን ተፈወሱ›› እያለ እልልታውን ያቀልጠው ጀመር፡፡

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top