Connect with us

በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረግ?

በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረግ?
Photo: Social media

ፓለቲካ

በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረግ?

በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረግ?
(አብርሀ ደስታ)

አንዳንድ የትግራይ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች (እንዲሁም ህወሓት) የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና ከዘጠኙ ስምንቱ ክልሎች እየመራ ያለው የብልፅግና ፓርቲ በሀገር ደረጃ ምርጫ የማያካሂድ ከሆነ የትግራይ ክልል (ሀገር?) ለብቻው ክልላዊ (ሀገራዊ) ምርጫ ማካሄድ አለበት እያሉ ነው።

ምክንያት ደግሞ (1) በህወሓት በኩል ፦ በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት መሠረት አንድ አካል ስልጣን መያዝ የሚችለው ወይም በስልጣን የሚቆየው በህዝብ ሲመረጥ ነው። ከመስከረም በኋላ በህዝብ የተመረጠ ሕገ መንግስታዊ ይሁን ቅቡልነት ያለው መንግስት ስለማይኖር የክልሉ መንግስት የቅቡልነት ቀውስ (Legitimacy Crisis) ያጋጥመኛል ከሚል የስልጣን ማጣት ስጋት የመነጨ ነው።

(2) ምርጫ ካልተካሄደ በሌላ የተለየ ሕገ መንግስታዊ ያልሆነ አሰራር ሰበብ የትግራይ ክልል ራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሊጨፈለቅ ይችላል ከሚል የትግራይ አክቲቪስቶች መልካም እሳቤ ነው።

ሁለቱም ተገቢ ስጋቶች ናቸው። ግን ምርጫ ማካሄድ ብንችል ጥሩ ነበር። ከዐቅም በላይ በሆነ ምክንያት አልተቻለም። እናም ምርጫ ተራዝሟል!

አሁን ህወሓት የቅቡልነት ቀውስ እንዳያጋጥማት ብለን ምርጫ ይደረግ ብለን እንጩህ? ምን አገባን? (ህወሓት ውጭ ያለን ሰዎች ማለቴ ነው)። የቅቡልነት ቀውስ ሲያጋጥም የክልላችን እና ህዝባችን ደሕንነት እና መብቶች እንዲከበሩ መጠበቅ ግን የሁላችን ሓላፊነት ነው።

ስለዚህ በክልል ደረጃ ምርጫ ይካሄድ ነው ምትሉ? የመንግስት ስልጣን ሕጋዊነትና ቅቡልነት የሚመነጨው ከምርጫ ነው ነው ምትሉ? አዎ ልክ ነው ከምርጫ ነው ሚመነጨው።

ግን ኮ ምርጫ በሀገር ደረጃ ተራዝሟል!? ምርጫ መራዘሙ ሕገወጥ ነው ነው ምትሉ? የምርጫ መራዘም በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ከፀደቀ ኮ ሕጋዊ ሆነ ማለት ነው!? ሕገ መንግስቱ ኮ በተለያዩ የሕግና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሕጋዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ስልጣን ሰጥቶታል። ስለዚህ በሕገ መንግስቱ መሠረት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የፀደቀ ውሳኔ ሕጋዊ ተፈፃሚነት አለው። ስለዚህ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ አካል እስከሆነች ድረስ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሚወጡ ሕጎች ወይም ውሳኔዎች የማክበርና የማስከበር ሕገ መንግስታዊ ግዴታ አለባት።

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምርጫን ለማራዘም የወሰነውን ውሳኔ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ነው ምትሉኝ? ውሳኔው ከሕገ መንግስት አንቀፅ ጋር ይጋጫል የሚል የሕግ ክርክር ተነስቶ በመጨረሻ ሕገ መንግስትን የመተርጎም ስልጣን ያለው የፌደሬሽን ምክርቤት “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” ነው ብሎ ውሳኔ እስካላሰለፈ ድረስ ምርጫን የማራዘሙ ውሳኔ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ሊባል አይችልም።

ምርጫ ካልተደረገ የሚባለው ሕገ መንግስቱ እንዳይጣስ አይደል? የትኛው ሕገ መንግስት? የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አይደል?

የኢፌዲሪን ሕገ መንግስት እንዳይጣስ በትግራይ ምርጫ ይደረግ ከተባለ ስለ ሕገ መንግስቱ መከበርም መጠንቀቅ አለብን። በሕገ መንግስቱ መሠረት ምርጫ የሚካሄደው በሀገር ደረጃ በተቋቋመው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ አዘጋጅነት ነው። ሕጋዊው ምርጫ ቦርድ ደግሞ አሁን በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ማስተናገድ አልችልም ብሏል።

ስለዚህ የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ እንዲካሄድ ከፈለገ ሀገራዊውንና ሕጋዊውን የምርጫ ቦርድን ማሳመን ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ምርጫው ሕጋዊ እንዲሆን በሕጋዊ አካል መዳኘት ይኖርበታል። በሌላ ሕጋዊ ያልሆነ ቦርድ ተዘጋጅቶና ተዳኝቶ ሕጋዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም! የሲዳማ ሪፈረንደም፣ የአዲስ አበባና የሱማሌ ክልል ወዘተ ምርጫዎች የተከናወኑ በዚሁ ሀገራዊ ቦርድ አማካኝነት ነው።

ሕጋዊው የምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልልን ምርጫ ለማከናወን ፍቃደኛ ባይሆንስ? (ማድረግ አልችልም ብሏል)።

የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ (ወይ ሀገራዊ) ምርጫ ቦርድን አቋቁማለሁ እያለ ነው። ለብቻ ይቻላል እንዴ? የክልል ምርጫ ቦርድ? በየትኛው የሕገ መንግስት አንቀፅ? ሕገ መንግስቱ እንዳይጣስ ብለህ ሕገ መንግስቱን ጥሰህ የራስህ ህገወጥ ምርጫ ቦርድ አቋቁመህ ምርጫ ልታካሂድ? ሕገ ወጥ ድርጊት ነው። ሕገ መንግስቱ ክልሎች የራሳቸው ክልላዊ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም ምርጫ ማካሄድ ይችላሉ አይልም። ሕገ መንግስት በመጣስ ሕገ መንግስት አይከበርም!

የኢፌድሪ ሕገ መንግስት አይመለከተኝም በማለት ራሱ እንቻለ ወይ እንደተገጠለ ሀገር (በነሱ ቋንቋ ዲ ፋክቶ ስቴት) በማሰብ የራስን ምርጫ ቦርድ አቋቁሞ የክልል ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ታስቦ ከሆነ… የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የማይመለከትህ ከሆነ ታድያ የትኛው ሕገ መንግስት እንዳይጣስ ነው ምርጫ ካላደረግን ሚባለው? እንደተለየ ሀገር ማሰቡ በራሱ ኮ ፀረ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ነው። በራስህ ፍቃድ ፀረ ሕገ መንግስት ስትሆን ኮ ቅጣት እየጋበዝክ ነው። ቅጣቱ ደግሞ የትግራይ ህዝብ መስዋእትነት የከፈለለት የራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶች አደጋ ላይ ትጥላለህ።

በሆነ መንገድ ራስህ ቻልክና፣ ምርጫው በተያዘለት ቀነ ገደብ (ነሐሴ 23, 2012 ዓም) ለማካሄድ ቆርጠህ ተነስተሃል እንበል።

በክልል (ሀገር) ደረጃ የመንግስትን ስልጣን የሚገድብ፣ የዜጎች መብት የሚጠብቅ፣ የስልጣን ምንጭ የሚጠቁም ወዘተ ሕገ መንግስት አዘጋጅተህ ማስፀደቅ ይኖርብሃል። በፀደቀው ሕገ መንግስት መሠረት የምርጫ ቦርድን ማቋቋም ይኖርብሃል። የምርጫ ሕግ አዋጅ አዘጋጅተህ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መመዝገብ አለብህ። የምርጫ ቁሳቁስ ከውጭ ሀገር አስገባ (14 ቀናት Quarantine ሆነው ይገባሉ)። መራጭ ህዝብ መዝግብ። የምርጫ ፈፃሚዎች ስልጠና ስጥ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብ እየሰበሰቡ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያካሂዱ ……. ሁሉም በጥቂት ወራት ውስጥ!

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለሦስት ወራት አስቸኳይ ግዜ አውጀሃል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። መሰብሰብ አይፈቀድም። እንዴት ተደርጎ ነው ምርጫ ሚካሄደው?

በማይሆነው ነገር አንድከም!

የተፈጠረ ይፈጠር ግን የህዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት (Right to Self Rule) እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት (Right to Self Determination) እደግፋለሁ፣ ለተፈፃሚነቱም እታገላለሁ!

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top