Connect with us

ከመድሃኒት ፍለጋው ጎን በጎን ….

ከመድሃኒት ፍለጋው ጎን በጎን እስካሁን ያልታመምንበት ምክንያትም ምርምር ያስፈልገዋል

ጥበብና ባህል

ከመድሃኒት ፍለጋው ጎን በጎን ….

ከመድሃኒት ፍለጋው ጎን በጎን እስካሁን ያልታመምንበት ምክንያትም ምርምር ያስፈልገዋል
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

ጋሽ ስብሀት ‹‹አምሥት ሥድስት ሰባት›› በሚል ሥያሜ ባሳተመው ተወዳጅ መጽሐፉ… የሳምንት ስንቃቸው አሰንቀው፣ ድንኳናቸውን ሸክፈው፣ ሰጋር በቅሏቸውን አስጭነው ሞትን ሲሸሹ ስለኖሩ አንድ ሽማግሌ ጽፎልን ነበር፡፡
ስለ አጋፋሪ እንደሻው…

እናም የ66 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አጋፋሪ ሰጋር በቅሏቸውን አስጭነው ወደ አንዱ ስፍራ ይሄዱና በሰፈሩ የታመመ ወይንም ደግሞ የሞተ ሰው መኖርና አለመኖሩን ሲጠይቁ… ‹‹የለም›› የሚል መልስ ከተሰጣቸው ድንኳናቸውን አስተክለው ያድራሉ፤ የታመመ/ የሞተ ሰው ካለ ደግሞ በቅሏቸውን በአለንጋ እያጣደፉ ወደ ሌላ አካባቢ ይሸሻሉ፡፡

የሚያሳዝነው ነገር ታዲያ አጋፋሪ ሞትን ሲሸሹት የነበረው በቅሏቸው ላይ አፈናጥጠውት፣ በጋቢያቸው ተከናንበውት፣ በትከሻቸው ተሸክመውት፣ ከኦክስጅን ጋር እየሳቡት፣ በውሃ መልክ እየጠጡት ነበር፡፡ ሽሽታቸው ከመሞቻ ስፍራቸው እና ቀናቸው ለመድረስ ነበር፡፡ ሸሸሁት ያሉትን መልዓከ-ሞት እየፈለጉት ነበር፡፡

ምክንያቱም ሞት የሌለበት ስፍራ የለማ! ጠላትን እንጂ ሞትን መሸወድ አይቻልማ!
አሁን ላይ ታዲያ ኮሮና የሚባል ገዳይ በሽታ በመምጣቱ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ እንደ አጋፋሪ እንደሻው ለመሆን ተገደዋል፡፡ ልዩነት በእሳቸው ዘመን የነበረው ሞት ከአገር አገር በመራወጥ የሚመለጥ ሲሆን፣ የእኛው ደግሞ ቤት ውስጥ አርፎ በመቀመጥ መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ እኛ የምንሸሸው በሽታውን ሲሆን፣ እሳቸው ግን እንደ አጠቃላይ ሞትን ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ ቫይረስ ይጠቁ ዘንድ የተፈረደባቸው አገሮችና ‹‹ሙቱ›› የተባሉ ሰዎች ከዚህ በሽታ መምለጥ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም በሥልጣኔውም ሆነ በጥንቃቄው የተካኑት ምዕራባውያኑ በዚህ በሽታ ሲያልቁ፣ በግድ-የለሽነታችን እና በኋላቀርነታችን የምንታወቀው አፍሪካውያን ግን እስካሁን ድረስ የከፋ ጉዳት አላስተናገድንም፡፡

በሽታው ቻይና ላይ ሲከሰት ቀድመው የአየርና ወሰናቸውና የየብስ ድንበራቸውን የዘጉት አገራት በበሽታው ሲወረሩ እንዲሁም ቤታቸውን ዘግተው የተቀመጡ ዜጎቻቸው ለሆነች ጉዳይ ወጣ ባሉበት ኮሮናን በመዳፋቸው ተሸክመውትና በፌስታል አንጠልጥለውት ወደ ቤታቸው በመግባት ታምመው ሲሞቱ፣ አየር መንገዷንም ሆነ ሕዝቦቿን በከፊል እንዲንቀሳቀሱ የፈቀደች አገራችን ግን ለበሽታው ተጠቂዎች ያዘጋጀቻቸው አልጋዎቿ እስካሁን ድረስ ባዷቸውን ናቸው፡፡

ማለትም እነሱ እንደ አጋፋሪ ሸሽተው ያላመለጡትን ሞት፣ እኛ እስከዚህች ቀን ድረስ ፈልገን አጥተነዋል፡፡ በመሆኑም ምዕራባውያን ከእውቀታቸው በላይ ሆኖ ከፍተኛ ጉዳት ላደረሰባቸው በሽታ መድሃኒት ለማግኘት ላብራቶሪያቸውን ዘግተው ምርምራቸውን ሲያጧጡፉ… እኛ ዘንድ ምርምር የሚያስፈልገው የኮሮና መድሃኒት ብቻ ሳይሆን እስካሁን ያልታመምንበት ምክንያትም ጭምር ሆኗል፡፡

ያም ሆኖ ግን የኮሮናን አስከፊነትና የመንግሥትን መመሪያ ችላ ብለው የተለመደ የህይወት ዘይቤያቸውን ያስቀጠሉ ዜጎች በርካቶች ቢሆኑም፣ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ግን እጁን በሳኒታይዘርና በሳሙና እያጸዳ ቤቱን ዘግቶ ሰንብቷል፡፡

እኔም ከእነዚህ ዜጎች መሃከል አንዱ ስሆን የቤቴን በር ዘግቼና ቴሌቪዥኔን ከፍቼ በጣሊያን፣ በስፔን፣ በአሜሪካ በየእለቱ የሚታመመውንና የሚሞተውን ሰው እየተከታተልኩ ስጨነቅ ሰንብቻለሁ፡፡ ‹‹ሞትን ሽሽት ከቦታ ቦታ በመራወጥ የሚታወቁት አጋፋሪ እንደሻው በዚህ ዘመን ቢኖሩ ኖሮ ቤታቸውን ዘግተው ከመቀመጥ ይልቅ ሰጋር በቅሏቸውን ጭነው ወደ አንታርቲካ መፈርጠጥ ሳይመርጡ አይቀሩም›› እያል ስፈላሰፍ ነበር፡፡

የሞት መላዕክ ወደ ቤቱ እንዳይገባ ለሰባት ዓመታት ያህል በግዝት አስቁሞ ደጅ ላይ ሲያንገላታው እንደኖረው ‹‹ሊቁ ተዋናይ›› እኔም ቤቴን ጥርቅም አድርጌ በመዝጋት በር ላይ ገትሬው ሰንብቻለሁ፡፡

ያም ሆኖ ግን እራስ ምታት ቢጤ ሲሰማኝ፣ ሰውነቴ ሞቅ ሲለኝ፣ አልፎ አልፎ ሲያስነጥሰኝ ‹‹ይሄ በሽታ ያዘኝ እንዴ?›› እያልኩ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ‹‹ፍርሃትና ናፍቆት›› በሚል ርዕስ የጻፏትን ግጥም ከጊዜው ጋር በምትጣጣም መልኩ ትንሽ ማስተካከያ አድርጌ እንዲህ እያልኩ ሳንጎራጉር ነበር፡፡

‹‹ሊመጣ ነው›› ሲሉኝ
የመቅሰፍት ጊዜ- የመከራ ጊዜ
‹‹የት ደርሷል?›› ስላቸው ‹‹ቀርቧል›› ብቻ እያሉኝ
‹‹መች ይመጣል’ም? ስል ‹‹ደርሷል›› ብቻ እያሉኝ
ይሄው ስንት ቀኔ በፍርሃት አለሁኝ
ወይ በሽታው መጥቶ- ደቁሶ አልደቆሰኝ
ፍርሃቱ፣ ፍርሃቱ፣ ፍርሃቱ ገደለኝ፤
‹‹ሊመጣ ነው›› ሲሉኝ
የሰላም፣ የደስታ- የነጻነት ዘመን
‹‹የት ደርሷል?›› ስላቸው ‹‹ቀርቧል›› ብቻ እያሉኝ
ናፍቆቱ፣ ናፍቆቱ፣ ናፍቆቱ ገደለኝ››

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top