Connect with us

ለእስክንድር ነጋ ግልጽ ደብዳቤ

ለእስክንድር ነጋ ግልጽ ደብዳቤ
Photo: Social media

ፓለቲካ

ለእስክንድር ነጋ ግልጽ ደብዳቤ

ለእስክንድር ነጋ ግልጽ ደብዳቤ
(ሙክታሮቪች)

ይድረስ ለእስክንድር

ከትናንት በስቲያ ቤታቸው ለፈረሰባቸው በቪዲዮ ያደረክላቸውን ንግግር ካየሁ በኋለ፣ በእውነት በመታሰርህ መቀለዴ አግባብ ባለመሆኑ ይህን ረጅም ደብዳቤ ልጽፍልህ ተነሳሁ፡፡

በዚህ ጽሁፍ ያንተ የፖለቲካ አካሄድ ስላልገባኝ፣ ወይ ነገረ ስራህ ከፓርቲ ፖለቲካ አካሄድ ጋር ሊጣጣምልኝ ስላልቻለ፣ ምንም አንተ የምታውቀው ቢሆንም ለሚደግፉህ ሰዎችም ይበጃል በማለት

ስለፖለቲካ
ስለፓለቲከኛ
እና
ስለፖለቲካ ፓርቲ….. ዘርዘር ያለ ነገር ጽፌልሃለው እና በትእግስት እንድታነበው ከአደራ ጭምር እለምንሃለው፡፡

,

ጊዜ ወስጄ ረጅም ደብዳቤ የምጽፍልህ፣ በርካታ ደጋፊ ስላለህ፣ ይህን ደጋፊ በአግባቡ ብትጠቀምበት ለሀገራችን ይጠቅማል ከሚል ቅን መንፈስ ነው፡፡ ይህ የአንድ የሀገርህ ልጅ እንደአቅሚቲ የተወረወረ ምክር እንጂ እኔ አውቃለሁ፣ አንተ አታውቅም በሚል መታበይ በመነሳሳት የተጻፈ በፍጹም አይደለም፡፡

ፖለቲካ ምንድነው …….. በዚህ ጥያቄ ልጀምር…..

አንድ ማህበረሰብ የሚተዳደርበት ስርዓት፣ ህግ እና አመራር ያስፍልገዋል፡፡ እዚህ ላይ አመራር ለመስጠት ስልጣን ለመያዝ የመወዳደረያ መድረክ ነው ፖለቲካ ማለት፡፡ በመሰረቱ የፖለቲካ መነሻም መድረሻም ህዝብ ነው፡፡ ፖለቲካ የሚጀምረው ከሰው ልጆች እኩልነት፣ በአንድ ሀገር ያሉ ዜጎች እኩልነታቸው በአዋጅ ተረጋግጦላቸው፣ ሰርተው የመኖር፣ ወልደው የመሳም፣ በነጻነትና በሰላም ወጥቶ የመግባትና ኑሮኣቸውን የማሻሻል፣ ጤናቸውን የመጠበቅ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ለራሳቸውና ለሀገራቸው ልማት በጋራ የሚያደርጉትን ርብርብና ስራን ወግ ባለው ስርዓትና መርህ ለማካሄድ ነው፡፡

ፖለቲካ በመሰረቱ ከላይ የተገለጹትን የማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ፍላጎቶች ሁሉ ዜጋ አንድ አይነት አመለካከትና አንድ አይነት ሀሳብ ስለማይኖረው፣ ስለሀገር ልማትና ስለህዝብ ኑሮ መሻሻል ተደጋግፎ በአንድነት ለመራመድና ለዚህም ዘዴ በዜጎች መካከል የሚከሰትን የሀሳብ ልዩነትን ስርዓት ባለው መንገድ አስታርቆ ወይም አመቻምቾ የማስኬድ ስራ ነው፡፡

,

ለዚህም ስራ የተለያዩ ግለሰቦች እንደ ቡድን ተደራጅተው በተለያዩ ሀሳቦች ዙሪያ በመነጋገር ልዩነትን በማጥበብና የስምምነቱን አድማስ በማስፋት ወደ የጋራ እድገትና ብልጽግና የማያቋርጥ ጎዳና ውስጥ የሚገቡበት ዘዴ ነው ፖለቲካ፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ ማለት በሰላማዊ መንገድ በህጋዊ ስርዓት፤ በንግግር፣ ውይይትና ክርክር ሀሳቦች የህዝብ ቀልብ እንዲስቡና ተቀባይነት እንዲያገኙ ከዚያም ወደ ህዝባዊ አላማ ተለውጠው ወደ መሬት እንዲወርዱ የሚያስችል ስልጣን ለማግኘት በብዱኖች መካከል የሚደረግ ሰላማዊ የስልጣን ፉክክር ነው፡፡

ባጠቃላይ፣ ፖለቲካ ‹የመመቻመች ጥበብ› ማለት ነው፡፡
The Art of Compromise ይሉታል ፈረንጆቹ፡፡ ፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ ጨዋታው ሁልጊዜ በልክነት አይመዘንም፣ በአግባብነት እንጂ፡፡ ፖለቲካ ሁልጊዜ ማሸነፍ አይደለም፣ ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን የማጣጣምና የማስታረቅ ጥበብ እንጂ!

,

የማከብርህ እስክንድር ሆይ!

ብዙ ጊዜ ያንተ የፖለቲካ አካሄድ ግትርነት ይበዛዋል፡፡ ጫወታህን ከተቀናቃኝህ አንጻር እየቃኘህ አትጫወትም፡፡ አክቲቭ እና የፖለቲካውን ከባቢ ቃኝተህ፣ መንፈሱን ቀድመህ ተረድተህ እስተራቴጂህን አታወጣም ወይንም አትከልስም፡፡ የተቀናቃኝህ ስታራቲጂና ታክቲክን እየተከተልክ ነው ፖለቲካን የምትተገብረው፡፡ ይህ ሪአክቲቭ ያደርግሃል፡፡ ከግብና አላማህ ያስትሃል፡፡ ህዝብ አጋር በሚፈልግበት ወቅት ድምጽን ማሰማት ተገቢ ቢሆንም የንተ ግን በትንሹም በትልቁም የግለሰብ ስም እያነሳህ ትቃወማለህ፣ ትዝታለህ፡፡

ሲበዛ ግትር ነህ!

ፖለቲካ እጥፍ ዘርጋ ይፈልጋል፡፡ አላማህን እና ፕሮግራምህን እስካልተቃረነ ድረስ ለትልቁ ምስል ስትል የማትሻውን ጥቃቅን ነገር ማድረግ ካለብህ ታደርጋለህ፣ ማድረግ እያለብህ ታግሰህ ታልፈዋለህ፡፡

__በፖለቲካ ግትርነት አይሰራም፡፡

ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንዲሁም የተለያዩ ኃይሎችን አሰላለፍና ሚዛን በቅጡ መፈተሸና መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካ የስልትና ስትራቴጂ ጨዋታ ነው፡፡ የጨዋታው አካሄድ የሚወስነው ካርድ በማን እጅ ውስጥ እንዳለ ማወቅ ስልትና እስትራጂን ለመከለስ ይጠቅማል፡፡

,
ፖለቲካ የአንድ ወገን ቅኝትና ዳንስ ብቻ የሚታይበት ሌሎች ዳር ቆመው የሚቆዝሙበት የአግላይ-ተገላይ ክስና ዛቻ የሚሰማበት የአምባጋሮ መድረክ ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተጻራሪ ጥቅሞች እርስበርስ ተቻችለው እንዲኖሩ ለማድረግ በተቃራኒ ወገኖች የጋራ ሀላፊነት የሚመራ ሰፊ የጥበብ መንገድ ነው፡፡

እርግጥ ነው፣ ይህ የሁሉ ሀላፊነት ነው፡፡ እንዳንተ የተማረ፣ ያነበበ እና የሰለጠነውን አለም ካየ ብዙ ይጠበቃል፡፡

በሀገራችን እንዲህ ያለ ፖለቲካ እንዲመጣ የሰከነ ስራ ይፈልጋል፡፡ ፍሬው በአመታት የሚጎመራ መኮትኮት የሚፈልግ ነው፡፡ ለዚህ በቀስታ ነገር ግን በጽናት ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ እያደገ የሚሄድ የፖለቲካ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

,

ውድ እስክንድር፣

ያንተን ፖለቲካ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ሊወክል በሚችል መንገድ መቃኘት አለብህ፡፡ የሚቃወምህ ሰው ለምን ይቃወምሃል? አይወክለኝም የሚልህ አካል ለምንድነው የሚጠራጠርህ፡፡ በተለያየ መንገድ ማጥናት፣ በተለይም በገለልተኛ በባለሞያዎች ማስጠናት አለብህ፡፡ ባገኘኸው ውጤት ላይ ተመስርተህ ፕሮግራምህን፣ እስትራቴጂና ታክቲክህን መቃኘት ካለብህ፣ መከለስ ካለብህ ትከልሰዋለህ፣ የጎደለ ነገር ካለ ጨምረህ ታዳብረዋለህ፡፡
,

ለምን መሰለህ?

ፖለቲካ የዜጎችን ዥንጉርጉር መልክና ፍላጎት ከግምት ያስገባ መሆን አለበት

ከገባህበት አይቀር ከልብ ፖለቲከኛ ሁን!

,

ፖለቲከኛ ማለት…….

ዜጎች ስለ ሀገር ልማትና ብልጽግና እንዲሁም ስለየራሳቸው የጋራ እና የተናጥል ጥቅሞች የተለያዩ አመለካከትና ሀሳብ ስለሚኖራቸው ፖለቲከኛ እነዚህን አመለካከቶች ሰብስቦ በመቀመር፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለየጋራ ጥቅሞቻቸውና ሌሎች አንገብጋቢ አጀንዳዎች ከህዝቡ በተለያዩ መንገዶች በመሰብሰብ አቀናብሮ አንድ ላይ በማንጠር የዚያን ማህበረሰብ አመለካከቶች በተለያዩ የህዝብ ውይይቶች፣ ክርክሮች እና በፖለቲካ መወዳደርያ መድረኮች ላይ ለህዝቡ መልሶ የሚያቀርብ ግለሰብ ነው፡፡

ፖለቲከኛ ማለት ……..

የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ብሶቶች፣ አቤቱታዎች፣ መከፋቶች፣ ንጭንጮች እና ደግሞ ሊከበርላቸው የሚፈልጉትን ጥቅሞችና ህልውናቸውን የሚፈታተኑ ወቅታዊ አስጨናቂ የኑሮ ውጣ ውረዶች መፍትሄ እንዲያገኙ አንድ ላይ በማሰባሰብ በአማረና አሳማኝ በሆነ መንገድ ‹አርቲኩሌት› በማድረግ አሽሞንሙኖ ለህዝብ መልሶ በንግግር፣ በጽሁፍና በተለያዩ መንገዶች የሚያቀርብ ሰው ማለት ነው፡፡

እንዲህ አይነት ፖለቲከኛ ሆነህ አላገኘውህም!

አንተ በኮሮና ምክንያት የተጨነቀውን ህዝብ አልኝታ ለማግኘት በተጠና እቅድ ትልቁ ምስልን ይዘህ እንደመንቀሳቀስ የቤተመንግስቷ ፒኮክ ላይ ፊርማ ለማሰባሰብ ዘመቻ ትላለህ፡፡ (አቅልዬው ሳይሆን ፕራይሮቲ አይደለም፣ የሚደግፍህ ህዝብ በዚህ ጉዳይ ይከፋፈልብሃል)

ሀገሪቱን ማወቅ አለብህ፡፡ በህዝብ ፊርማ የተቀየረ ነገር ሀገራችን የለም፡፡ ኖሮም አያውቅም፡፡ ወንበር እና ስልጣን የህዝብ እምነትን መርታት አለበት፡፡ የህዝብ ትልቁ አንገብጋቢ ችግርን መለየት እና ህዝብን እያደራጁ መታገል ያስፈልጋል፡፡

ለፌስቡክ አጀንዳ ሳይሆን ምላሽህ ለትልቁ አላማህ መሆን አለበት፡፡

,

በተጨማሪ ፖለቲከኛ ……..

የሚወክለውን ህዝብ ጥቅሙን እንደሚያስከብርለት ቃል በመግባት የተደራጀና የተጠናከረ ድጋፍ እንዲሰጠው በማግባባት ከዚያም በፖለቲካ ምህዳር ውስጥ በጽሁፍና በንግግር በፖለቲካ ነክ መድረኮቸና ውይይቶች ላይ አሳማኝ በሆኑ ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎች የሚወክለው የማህበረሰብ ክፍል ጥቅሞች ለምን ህጋዊ ተቀባይነት እንደሚሹ፣ ለምን ሊደገፉ እንደሚገባ፣ ለችግሮቹ ምን መፍትሄ ከማን መቼ ሊያገኙ እንደሚገባ በተፎካካሪ ወይም ታዛቢ በሆኑ ብዱኖች ባሉበት የፖለቲካ ጠረጴዛ ላይ በማቅረብ የዚያን ማህበረሰብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ሰው ማለት ነው፡፡

,

ለምሳሌ የአዲሳባ ህዝብ ጉራማይሌ ነው፡፡ በብሄር፣ በሃይማኖትና በመደብ ይለያየል፡፡ ሁሉንም ልታቅፍ የሚያችል የበሰለ ፖለቲካ መጫወት አለብህ፡፡

ካንተ የማይጠበቅ ስህተት ትሰራለህ፡፡

ለምሳሌ የሞጣ መስጊዶች ሲቃጠሉ እንደ ፖለቲከኛ ማለት ያለብህ እና መናገር ያለብህን መለየት እና በጥንቃቄ መናገር አለብህ፡፡ አንተ ግን ያቃጠሉ ሰዎች በንዴት ተገፋፍተው ነው አይነት በሙስሊሙ የሀገሪቱ ህዝብ ነጥብ የሚያስጥል ፋውል ሰራህ፡፡

መሳሳት ያለ ነው፡፡ ሆኖም ይቅርታ መጠየቅ ደግሞ ያጣኸውን ድጋፍ ይመልስልሃል፡፡

አዲስ አበባ በኦሮሞ ህዝብ የተከበበች ከተማ ናት፡፡ ቁጥሩ የበዛ ኦሮሞ ይኖርባታል፡፡ አንተ ይህን ሰፊ ህዝብ ቀልብ ማሸነፍ አለብህ፡፡ ቄሮን በአሸባሪነት በአለማቀፍ እከሳለሁ ብለህ ስታበቃ፣ አማራ ክልል ከፋኖ ጋር በጥይት ታጅበህ ፎቶ ትነሳለህ፡፡ ሰላማዊው፣ አራዳው እና በጥይት የማያምነው የሸገር ልጅ በዚህ ደብል ስታንዳርድ አካሂድህ ይታዘብሃል፡፡ ኦሮሞውም እንዲሁ ሁሉን ቄሮ በአንድ ስትፈርጅበት አይቀበልህም፡፡

ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ የተብራራ ነገር ከቻልክ ጻፍ፡፡ ጊዜ ከሌለህ ተወው፡፡
Rebels without cause እያልክ ገና ከጅምሩ ከብዙዎች ጋር ትጋጫለህ፡፡ ለመፈታትህ ከፍተኛ ትግል ያደረጉትን ቄሮዎች ጨፍልቀህ ለብዙ ትርጓሜ የሚያጋልጥ ቁንጥር ቁንጥር ያለች ጽሁፍ መልቀቅ ትግል አይደለም፡፡ ከቄሮ ውስጥ ጭቆና አንገፍግፎት የታገለ አለ፡፡ ትግሉን ወደ ሌላ አቅጣጫ የመራም አለ፡፡ ሰውን እያሳመንክ ደጋፊ ታደርጋለህ እንጂ መግፋት የለብህም፡፡ ፖለቲካ እንዲህ አይሰራም፡፡

,

በኣጠቃላይ ፖለቲከኛ ……

የጋራ ጥቅሞች ነጋዴ በመሆን እነዚህን የጋራ ጥቅሞች (collective interest) የሚያንጸባርቁ ሀሳቦችን አበጃጅቶ፣ አሳምሮና አሽሞንሙኖ፣ በተስፋ ቃል አጅቦ ለፖለቲካው ምህዳር የጋራ ማዕከላዊ ገበያ ያቀርባል፡፡ ህዝብ ድምጹን በእሱና በአስተሳሰብ አንድነት ለተግባቡ የቡድን አባላቱ (ለፓርቲው) እንዲሰጥ በማግባባት ለስልጣን የሚሰራ ሰው ነው፡፡

ብዙ ጊዜ እንደማይብህ የመብት ታጋይነትህ እስካሁን ስላለቀቀህ፣ ፖለቲከኛነቱን ይጋርድብሃል፡፡

አውቃለሁ መንግስት እቀባ ያርግብሃል፡፡ ሆኖም በብልጠት አንተም መጓዝ አለብህ፡፡ በሀገራችን የተከፈተውን የፖለቲካ መንገድ አሟጠህ ለመጠቀም በሳል መሆን አለብህ፡፡ ህዝቡን ከስር፣ ከመንደር ጀምሮ ማደራጀት አለብህ፡፡ ማንቃት አለብህ፡፡ ለነገ ፍሬ ያዘለ ስራ ዛሬን በተጠና እርምጃ መጓዝ አለብህ፡፡

ከመጥፎ ስርዓት የወረስነው የታሪክ ሸክም አለ፡፡ እንደ ሀገር የሚያኮራም ታሪክ አለን፡፡

በምንኮራው ኮርተን….ከዚያ ባሻገር….

ለጥንት በደል እውቅና ሰጥቶ፣ እንዳይደገም ተስማምቶ፣ ከዚያም አልፎ ተራምዶና ተሻግሮ ዛሬ የሚገጥሙን ህልውናችንን የሚፈታተኑና የኑሮ አስጨናቂ ጉዳዮችን በመፍታት ለነገ የልጅ ልጆቻችን የምትበጅ ሀገርን በጋራ እንድንገነባ የሚሰሩ ፖለቲከኞች እጅግ በጣም ጥቂት ስለሆኑ አንተ በዚህ ረገድ ሁሉን ሊያቅፍ የሚችል የፖለቲካ ጥበብ ይፈለግብሃል፡፡

ሰው እንደታጋይነትህ፣ በብእርህ ስለሚያውቅህ ይህን ብራንድህን የሚመጥን ፖለቲካ ያስፈልጋል፡፡

ውድ እስክንድር ሆይ!

አሁን ፓርቲ አለህ፣ ፖለቲካን በማህበር እየተገበርህ ነው ማለት ነው፡፡
ማኅበር ማለት የጋራ ዓላማ ያላቸውን ሰዎች ተሰብስበው የሚፈጥሩት ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ የጠራ አላማ እና መድረሻ ግብ አለው፡፡ ማኅበር አለቃ አለው፣ ደንብና ሥርዓት አለው፣ አባሎቹ ለማኅበሩ ግልጽና የተወሰነ ግዴታ አለባቸው፣ ማኅበሩም ለአባሎቹ የተወሰኑ መብቶችን ያጎናጽፋል፣ በተጨማሪም አባሎቹ በማኅበሩ ዓላማ የተሳሰሩና የተዛመዱ ይሆናሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አላማ ስልጣን ይዞ ለህዝብ ፋይዳ ያለው ነገር ለማበርከት እስከሆነ ድረስ በከፍተኛ ስርዓት መመራት ስላለበት፣ የማህበሩ አባላት በየለት ድርጊታቸው ዲሲፕሊን ያስፈልጋቸዋል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ህግ ወጥቶ በስርዓት መተግበር አለበት፡፡

ጠንካራ እና ግልጽና የጠራ አላማህን ማስቀመጥ አለብህ፡፡ የተደራጀ ድረገጽ ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብ አቅምህን ለመጨመር ሰው የሚተማመንበት ፓርቲ ለመሆን ከፍኛ የሞብላይዜሽን ስራ ያስፈልጋል፡፡

ሰዎች የጠራ ዓላማ ሲያገኙ ይሰባሰባሉ፤ ተመሳሳይ ዓላማ ያቀራርባል፤ መቀራረቡ ዓላማውን ለማራመድ ብልሃትን ይፈጥራል፡፡ ይህ ወሳኝ ነው፡፡

እስክንድር ሆይ!

ወረድ ብለህ ሰው ላይ ስራ! ሸገር የነቃ ማህበረሰብ ስለሆነ ያለህን መልካም እድል እወቀው!
ዓላማ ሰውን ያሰባስባል፡፡ የፖለቲከኛ ስራ በአላማ ስር ሰውን ማሰባሰብ ነውና!

ዓላማውን ለማራመድ መደረጀት ግድ ነው፤ ለመደራጀት ማንቃት ያስልጋል፡፡ በዓላማው የሚያምኑ ሰዎች ይሰባሰባሉ፣ ይበረታሉ፣ ወንድማዊና እህታዊ ስሜት ያስተሳስራቸዋል፡፡ ግዴታቸውን ይመዘግባሉ፤ ጉልበታቸውን ያስተባብራሉ፤ ለተፈላጊው ነገር ሁሉ የማኅበሩ ኃይል የሚሆን መዋጮ ያዋጣሉ፣ ሀብት ካላቸው ገንዘብ ያሰባስባሉ፡፡

ለማኅበሩ ህልውና፣ መስፋፋትና ጥንካሬ፣ እድገትም ደንብና ሥርዓት ይቀረጻል፣ በአላማ ጽናት፣ ስነስርዓትና እውቀት እየታየ በየቦታው ጠንካራ ሰው ይሰየማሉ፡፡
የበለጠ እድገት የሚገኘው ማኅበሩ ባመጣው ውጤት መጠን ነው፡፡ ውጤት ካጣብህ ሰው ከልቡ ያስወጣሃል፡፡

ዓላማን ተከትሎ የሚመጣው የአባሎች መሰባሰሰብና ድርጅት መመሥረት ውጤቱ በነጠላው ዓላማውን ማራመድ ብቻ አይደለም፤ አባሎቹን ያቀራርባል፤ ያዛምዳል፤ ዝምድና ከማኅበረተኛነት የአላማ ፍቅር ይወለዳል፡፡

ያንተ አላማ ምንድነው? ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ላንተና ለጓዶችህ ብቻ አይደለም፣ ለሚከተልህ፣ ለሚወድህም ለሚጠላህም፡፡ የሚወድህን ትይዛለህ፡፡ ጠላት/ተቀናቃኝህን እየቀነስክ እየደረጀህ ትሄዳለህ፡:

አሁን እየሄድክ ባለው መንገድ ለስኬት መብቃትህን እጠራጠራለሁ፡፡

በመጨረሻም……

ይህን ሁሉ የጻፍኩልህ! ከብሽቀት የተነሳ አላግባብ፣ ቤት ለፈረሰባቸው ስትቆም በሳታይር መልኩ ስለቀለድኩብህ፣ ወንድማዊ ምክሬን በመለገስ ልክስህ ስለፈለኩ ነው፡፡
ይቅናህ፡፡

አክባሪህ ሙክታሮቪች

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top