Connect with us

የጥቁር አንበሳ – ጥቁር አበሳ

የጥቁር አንበሳ ~ ጥቁር አበሳ

ጤና

የጥቁር አንበሳ – ጥቁር አበሳ

የጥቁር አንበሳ ~ ጥቁር አበሳ
#ጥቆማ ለአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት!!

ጉዳዩ:- የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኮሮናን በመከላከል ረገድ ያሳየውን ልግምተኝነት ላይ ፈጣን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ስለመጠየቅ፤

በእውነቱ ደንግጫለሁ። ምን እንደምል አላውቅም። የትልቁ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነገር ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ የሚያሰኝ ነው። ሰሞኑን በሆስፒታሉ ከ48 ሰዓት በላይ የምቆይበት ጉዳይ ነበረኝ። የሆስፒታሉ ኮሪደሮች በኮሮና ወረርሽኝ መልዕክቶች ተጨናንቀዋል። በየኮሪደሩ የተሰቀሉ ቴሌቭዥኖች በሆስፒታሉ የታወቁ ሐኪሞች ስለኮሮና ቫይረስ የሰጡት መልዕክት እየተደጋገመ ይሰማል። በመውጫና በመግቢያ በሮች ላይ በአስታማሚና በመሳሰሉት ሰዎች በብዛት እንዳይገቡ ብርቱ ጥንቃቄ ይደረጋል። ወደውስጥ የሚዘልቁ ሰዎችም እጃቸውን እንዲታጠቡ ውሀ እና ሳሙና ተዘጋጅቷል። እንዲሁም የሰውነት ሙቀት የሚለኩ ባለሙያዎችም በየበሩ ላይ ተሰይመው ሥራቸውን ያከናውናሉ።

በቅጥር ግቢ ውስጥ የሚታዩ ብዙ ባለሙያዎች አፋቸው ላይ ማስክ አይጠፋም። አንዳንዶችም ለእጃቸው ጓንት ያደርጋሉ። ሆስፒታሉም ሆነ ባለሙያዎቹ እዚህ ድረስ ያደረጉት ነገር የሚመሰገን ነው።

ነገርግን 3ኛ ፎቅ በሚገኘው የወላዶች ማረፊያ በአንድ ክፍል (በግምት 40 ካሬ ሜትር በሚሆን ክፍል) ሰባት አልጋዎችን ተዘርግቷል። እንደታዘብኩት በክፍሉ ውስጥ አንዲት እናት ከወለደችው ልጇ ጋር እና ከአንድ አስታማሚ ጋር በትንሹ 21 ሰዎች ውለው ያድሩበታል። እንዲሁም ለሥራ ወጣ ገባ የሚሉ ሐኪሞች፣ የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪዎች፣ የምግብ አቅራቢ እና የፅዳት ባለሙያዎች… ቁጥር ሲጨመር የሰው ብዛት ያሻቅባል። በዚህ ላይ ክፍሉ ለአየር ማስተላለፊያ በቂና የሚሰሩ መስኮቶች የሌሉት መሆኑ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል። ከምንም በላይ የወለዱ እናቶች የቆይታ ጊዜ ከአንድ እስከ ሶስት ቀናት ሲሆን በክፍል ውስጥ በየቀኑ የሚኖረው የሰዎች መለዋወጥ ከፍተኛ መሆኑ ለኮሮና ቫይረስ የመጋለጥ እድልን የሚያሰፋ ነው።

ዛሬ መንግስታችን በባቡር፣ በታክሲና በአውቶቡስ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲቀንሱ ያደረገው የቫይረሱን ስርጭት ስጋት ለመቀነስ ነው።

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማኔጅመንት ግን ተኝቷል። የሰራው ነገርም ከፈንድ ቅፈላ ጋር የተነካካ የጥቅም ጉዳይ ብቻ መሆኑን መገመት ይቻላል። በሆስፒታሉ አስተኝቶ በማከም ክፍሎች ውስጥ ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ፣ ክፍሎቹም በቂ አየር እንዲያስገቡ መስኮቶችን የመጠገን ስራዎች ላይ ዳተኛ ሆኗል። በማኔጅመንቱ ቸልተኝነት የጤና ባለሙያዎችን፣ የህክምና ፈላጊዎችን ህይወት ሪስክ ውስጥ መውደቁ አሳዛኝ ነው። ያነጋገርኳቸው ሐኪሞች ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ነግረውኛል። ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማኔጅመንት ኮቪድ 19 መከላከል ማለት ወረቀት በየግድግዳው ላይ መለጠፍ፣ በየኮሪደሩ በተሰቀሉ ስክሪኖች ስኮቪድ 19 ማወራት፣ ባለሙያዎች ማስክ እንዲያደርጉ መወትወት ብቻ ነው። በተግባር፣ መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ለኮሮና ቫይረስ ምቹ ጫካ ነው።

ይኸ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድርጊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን የጣሰ ነው።ርቀትን ከመጠበቅ አንፃር፣ በቅርብ ርቀት ከአራት ሰዎች በላይ አለመሰብሰብ እና የመሳሰሉ ድንጋጌዎች ተጥሰዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፈፃሚ አካል ወይንም ኮማንድ ፖስት ሆስፒታሉን ከጤና ሚኒስቴር እና መሰል አካላት ጋር ሆኖ በመገምገም ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ጥቆማዬን አቀርባለሁ።

ጫሊ በላይነህ ነኝ።

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top