የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጥበብ ዕይታና የቅጥራቸውን ሞገስ የማይመጥን የኪነ ጥበብ ኩነት፤
ብልጽግና ከኢህአዴግ የወረሳቸው አርቲስቶችና ህወሃት በሀብት ክፍፍሉ የምትረከባቸው ከያኒያን፤
****
ከስናፍቅሽ አዲስ
ኮሮናን ለማስተማር በሚል የተዘጋጀው ያልተማረ ሰው ብቻ ሳይሆን ጥበብ አልባ ኩነት ብዙዎች ስሜታቸውን ገልጸውበታል፡፡ ትናንት ብስራት ኤፍ ኤም ላይ ኪነ ብስራትን ስሰማ ግን እኔም የተሰማኝን ብዬ ባልፍ ቢያንስ ስህተት በየዓመቱ የማይደገስባት ሀገር አንፈጥርም፡፡
ብልጽግና ኢህአዴግን የመሰለበት ክስተት የአንድነት ፓርኩ የኪነት ድግስ ይመስለኛል፡፡ አሁን በደረስኩበት ድምዳሜ ብልጽግና እንደ ማህተሙና እንደ አባላቱ ሁሉ ከኢህአዴግ እነኚህን የጥበብ ሰው ነን ባይ ቡድኖችም አብራ ተረክባለች፡፡ ግንቦት ሃያን የሚመስለው የኮሮና ድግስ ጥበብም ውቃቢም የራቀው እንደሆነ ታይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኪነ ጥበብ እውቀታቸው የሚታሙ አይደሉም፤ ያማ ቢሆን ዳንኤል ክብረትን ሳይሆን የደራሲያን ማህበሩን ጸሐፊ አማካሪ ባደረጉ ነበር፡፡ የሰላ ንባብ፣ የኪነ አውዱ እውቀትና የጥበብ ዕይታ ያላቸው መሪ ናቸው፡፡ አንድነት ፓርክ በዚህ አግባብ ካየነው እንዲህ ያለው እውቀት ሰርቶ ማሳያ ነው፤ ከዚህ ቅጥር የቀረበውን የኪነት ድግስ ስመለከት ግን ስራው ጠቅላያችንንም ቅጥራቸውንም እንደማይመጥን አውቄያለሁ፡፡
ከዚህ ቀደም ትልልቆቹ ከያኒያን እኮ እንደ “መላ መላ ወገን አትበል ችላን” ሰርተዋል፤ “አንድ ሰው ለአንድ ነው” ለኤድስ የማይመስል ድንቅ ጥበብ ነበር፡፡ ዛሬ ጥበብ ነጥፎ የሰው ዘፈን ወስዶ ግጥምን በመቀየር ኮሮናን ልዋጋ ማለት የፈጠራ ኮሮና ከመሆን በስተቀር ዋጋ የለውም፡፡
እንዲህ ያሉ የኪነት ስራዎች ችግራቸው የተሳታፊዎች የት መጤነት ነው፡፡ ተሳታፊዎች ከማኅበር ይመለመላሉ፤ ይሄ ኮሚኒስታዊ ነው፡፡ ብዙውን ግዜ በማህበር የሚሰበሰቡት አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡ አቅም ያለው እንዳይመጣ ካስፈለገ ከማኅበር ጥራ የሚለው መርህ ኮሚኒስታዊ ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
ደራሲያን ማህበርን ስትጠራ ዘነበ ወላ፣ በእውቀቱ ስዮም፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ አዳም ረታ፣ በድሉ ዋቅጅራ ይስማከ ወርቁ የምትላቸውን መሰል ሰዎች ፈጽሞ አታያቸውም፡፡ ሙዚቀኞች ማህበር ስትሄድ የማታየው ማንን መሰለህ ቴዲ አፍሮ የሚባል አስማተኛን ነው፤ ሙሐሙድን የሚያህል ዋርካ ነው፤ አስቴርን መሳይ ምልክት ነው፤ አሊበራን ዓይንት ጌጥ ነው፤ የማህበር ችግሩ ይሄ ነዋ፡፡
ማህበርተኞች ከተጠራሩ ተዋናያን ተብለው ያላለቀ ድራማ ላይ ከቤተህ አልጠፋም ያሉትን እንጂ እንደ ግሩም ኤርምያስ እንደ ሮማን በፍቃዱ እንደ ሰላም ተስፋዬ ብቻ ምን አለፋህ ምልክቶችህን ማህበር ተብዬው አያሳይህም፡፡
የዚህ ድምር ውጤት ለማህበር በተሰጠው ድግስ ትልቅ ሀገር ትልቅ ስራ ትልቅ ነገር አይታይም፡፡ ችግሩ እሱ ሳይሆን እስከመቼ የሚለው ነው?