Connect with us

ፈጣሪ ኾይ የእኛን የንስሐ ማግስት በደል አትቁጠርብን

Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

ፈጣሪ ኾይ የእኛን የንስሐ ማግስት በደል አትቁጠርብን

ፈጣሪ ኾይ የእኛን የንስሐ ማግስት በደል አትቁጠርብን፤ ይልቁንስ የፈሰሰውን የአባቶቻችንን እንባ ተመልከት፤ በር ዘግተው ስለ ምድራችንና ስለ እኛ ስለሚቃትቱት ብለህ ህዝብን አድን፤ | ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

እኛ ሐጢአተኞች ነን፡፡ በዚህ በፈሰሰው እንባ የጎጠኝነት ቆሻሻችንን እጠብልን፤ የራስ ወዳድነት እድፋችን አንጻልን፣ የበቀል፣ የቂም፣ የጥላቻና የማንአለብኝነት ሐጢአታችንን አሰወግድልን፡፡ አቤቱ በድለናል፤ ፍርሐት ምሪቱን ሞላ፤ ጉልበተኞች ጉልበት አጡ፡፡ እኛ ቀድሞውኑም ጉልበት ያልነበረን ደካሞች ነበርን፤ የምንታመንበት የአባቶቻችንን ድምጽ ነው፡፡ ፈጣሪ ኾይ ድምጻቸውን ስማ፤

እኛ የማናውቃቸው አንተ የምታውቃቸው በየዘጉበት በዓት ስለ ምድራችንንና ስለ ህዝባቸው የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ የእኛን ነገር አትመልከት፡፡ እኛ እንዲህ ያለው ቅጣት የሚያንሰን ነን፡፡ እምነት ተቋማትን አውድመናል፤ አባቶችን አንገት አስደፍተናል፤ እናቶችን አስለቅሰናል፡፡ እኛ በአንተ ፊት ማረን የምንልበት ጉልበት የለንም፡፡ ስለዚህ ስለአባቶቻችን እንባና ልመና ብለህ ምድራችንን ፈውስ፤

ጉልበታችንን አይተነዋል፤ የማሸነፍ መንፈስ ከእኛ ዘንድ ርቋል፡፡ ስልጣኔያችን እጅን እንኳን በአግባቡ ከመታጠብ የላቀ አይደለም፤ መሬታችን ያልነው፣ ቋንቋችን ብለን የተመካንበት፣ ሌላውን ያሳደድንበት ጎሳችን ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ያየንበት መዓት በፊታችን ወጣ፤ ስለ አባቶቻችን እንባ ብለህ አንተ ቅደም፤

በደለኞች ብንሆንም በሀገራችን ካዝና አንታመንም፤ ሐጢአተኞች ብንሆንም በትውልዱ እውቀት ደረት አንነፋም፤ ነውር በፊት ብንፈጽምም ትንሽ ሀገር እንደሆንን እናውቃለን፡፡ አቤቱ ይኽቺን መሳሪያዋ፣ ሀብቷ፣ እውቀቷ፣ ንብረቷ አንተ ትደርስልኛለህ ብሎ ማመን ብቻ የሆነችዋን ሀገረ ኢትዮጵያ አስባት፡፡

ኢትዮጵያ በምኗም የማትመካ ሀገር ናት፡፡ ዛሬም ከአባቶቻችን የወረስነው ሀብት አንተ አንዳች ተአምር እንደምታደርግ ማመናችን ነው፡፡ ስለዚህ እምነታችን ስትል በደላችንን አትቁጠር፣ ሐጢአታችንንም አታስብ፤ በፊት የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል መልካምነት የሌለበት ትውልድ እንዲህ ካለው አስፈሪ መዓት ጋር ተፋጧል፡፡ አንተ ትሰማን ዘንድ የፈሰሰው የአባቶቻችን እንባ በደላችንን ሁሉ ይጠብልን፡፡ አቤቱ ምህረትህን እንለምናለን፤

አቤቱ ፈጣሪያችን ኢትዮጵያ ምንም የሌላት ማንም የማይደርስላት ብዙ መከራዎችን ሁሉ በአንተ ርዳታ እና በአንተ እገዛ አልፋ እዚህ የደረሰች ሀገር ናት፡፡ አሁንም ይህንን ፈተና አንተ አግዘን፤ የማንደማመጥ በደለኞች፣ በንስሀ ማግስት ወደ ትፋታችን የምንመለስ አስቸጋሪዎች ነን፤ ነገር ግን ስለ ታመኑት ባሪያዎችህ፣ ስለ ደጋጎቹ አበው ጸሎትና የቃል ኪዳን አደራ ብለህ ኢትዮጵያን አስባት፤

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top