Connect with us

አብን ምርጫው በአንድ ዓመት እንዲራዘም ጠየቀ

አብን ምርጫው በአንድ ዓመት እንዲራዘም ጠየቀ
Photo Facebook

ዜና

አብን ምርጫው በአንድ ዓመት እንዲራዘም ጠየቀ

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተዘጋጀ አገራዊ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ስትራቴጅ ማስተዋወቂያና አገራዊ የክተት ጥሪ!

ይድረስ ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣
ለኢፌዴሪ መንግስት፣
ለመላው ኢትዮጵያዊያን፣
ክቡራትና ክቡራን

መነሻዉን በአገረ ቻይና ዉሃን ከተማ ባደረገው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ አለማችን መታወክ ከጀመረች እነሆ ከሁለት ወራት በላይ ሆነ፡፡ ቫይረሱ መላውን ዓለም ያዳረሰ ሲሆን በአገራችንም የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እስካሁን 20 የሚደርሱ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸዉ ተረጋግጧል፡፡ ይህም መረጃ በአለም አቀፍ የኮሮና ክትትልና መከላከል ግብረ ሃይል እንዲሁም በጆንስሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ይፋ የሆነ ነው፡፡ ምርመራ በስፋት ቢደረግ ከዚህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ሊሆን እንደሚችል የህክምናና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያች ግምታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከብሄራዊ አስፈጻሚው ጀምሮ በየዞኑና ወረዳዎች ግብረ ኃይል ያቋቋመ ሲሆን ግብረ ኃይሉ በየአካባቢው ከሚገኙ ባለሃብቶችና በጎ አድራጊዎች የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያቀርቡ በማስተባበር ወደ ስራ እንዲገባ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

አብን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን እንዳይገባ ያደረገው የቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ ቀድሞ በተዘጋጀ በዕቅድ ተመስርቶ ሊፈጸም ሲገባው በዚህ በኩል በቂ ስራና ዝግጀት ሳይደረግ እንደቀረ፣ እንዲሁም ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ ስርጭቱን ለመግታት የተደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑን ብናውቅም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ጉዳዩ የተሻለ ትኩረት ማግኘት መጀመሩ በበጎ የሚታይ ነው፡፡ መንግስት አሁንም ቢሆን የኮሮና ወረርሽኝ እየፈጠረ ያለዉን ከፍተኛ የሆነ የጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ግምት ዉስጥ ያስገባ አጠቃላይ አገራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ስንል ለማስታወስ እንፈልጋለን፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና የጤና፣ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ለሚደረገው ብሔራዊ ጥረት የፓለቲካ መስመር ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆኖ አብን ከመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞና ተባብሮ ለመስራት፣ እንዲሁም በአገራችንና በህዝባችን ላይ የመጣዉን ችግር ተደጋግፎ ለማለፍ ቁርጠኝነቱን እየገለጸ፤ በሚቋቋሙ ብሔራዊ ኮሚቴዎች አመራሮችንና ባለሙያዎችን መድቦ አገራዊ ጥረቱን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ያሳውቃል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሚከተሉት ርምጃዎች በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በመንግስት እንዲተገበሩ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

1) መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር መሬት ላይ የወረደ ስራ ከማከናወን ይልቅ ከተጠመደበት የሕዝብ

ግንኙነትና የገጽታ ግንባታ ድርጊት ተላቆ ቫይረሱ በአገራችን ላይ የሚያደርሰዉን የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ የተገለጠ ቢሆንም ይሄው ኮሚቴ ሁሉን አካላት ያቀፈና ያሳተፈ እንዲሆን፤ ይህም ኮሚቴ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ብሔራዊ ስትራቴጅ በአስቸኳይ ቀርጾና በቂ በጀት መድቦ ወደ ስራ እንዲገባ አብን ታሪካዊ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

2) ወረርሽኙ የሚያደርሰዉን ተጽዕኖ ለመቀነስ

• ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ሰዉ ተጠጋግቶ ያለባቸዉን እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የስደተኛ ካምፓችና ጣቢያዎች፣ የወታደር፣ የፓሊስና የልዩ ሃይል ካምፓች፣ ሕዝብ በብዛት ተጠጋግቶ በሚኖርባቸው የከተማደሳሳ ሰፈሮች፣ ኮንዶሚኒየሞችና ባለብዙ ፎቅ ህንጻዎች አካባቢ ለቫይረሱ መከላከል የግልና የአካባቢ ንጽህናን ለመጠበቅ የሚያስችል ውኃ አቅርቦት ላይ አተኩሮ እንዲሰራ፤

• አካላዊና ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅን (social distancing) ሕዝባችን በአግባቡ እንዲተገብረው ጥሪ እያቀረብን፣ ሕዝባችን በቂ ዝግጀት እንዲያደርግ ቀድሞ እንዲያውቀው ከተደረገ በኋላ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የሚተገበርና ቢያንስ ለሁለት ሳምንት የሚተገበር ከቤት ያለመውጣት፣ እንቅስቃሴን የመገደብ አዋጅ እንዲታወጅ፣ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት ተግባራዊነቱ ላይ ክትትል እንዲደረግ፤

• ከክፍለ አገር ወደ አዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ወደ ከፍለ አገር የሚደረግ የትራንስፓርት እንቅስቃሴ እንዲገደብና ማናቸውም ከአገር ውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚደረጉ በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ በረራዎች (non-essential flights) ቢያንስ ለ2 ሳምንት እንዲቋረጥ፤ ለአንድ ወር ለሚሆን ጊዜ ደግሞ እንደ ሰርግ፣ ቀብር፣ ማህበር፣ ሰደቃ ወዘተ አይነት ፕሮግራሞች በቤተሰብ አባላት ብቻ እንዲከወኑ ማድረግ፤

• የገጠሩ ወገናችንን ማዕከል ያደረገ የማስተማርና ቅስቀሳ ስራ ሬዲዮን ጨምሮ በልዩ ልዩ መንገድ ትኩረት ተደርጎበት እንዲሰራ፤ ለጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ተገቢዉን ስልጠና በመስጠት ገጠር አካባቢ በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ማኅበረሰባችን ዘንድ ሊከሰቱ የሚችሉ የቫይረሱን ወረርሽኝና የህመም ምልክቶች የመለየትና የመከታተል ስራ በከፍተኛ ትኩረት እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡

• የምርመራ መሳሪያዎችን በማሟላት በአዲስ አበባና በጥቂት ሆስፒታሎች የተወሰነዉን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ወደ ክፍለ አገራትና ወደ ወረዳዎች እንዲስፋፋ ከፍተኛ ጥረት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

• ወረርሽኙ በሚያደርሰው ህመም፣ ጭንቀት፣ ስራ አጥነትና ተያያዥ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ዜጎች የነጻ ምክር አገልግሎት የሚያገኙባቸው የስልክ መስመሮች እንዲዘጋጁ በማድረግና በጎ ፈቃደኛ የስነ ልቦና ባለሙያዎችና ከሁሉም እምነቶች የተዉጣጡ የሃይማኖት አባቶች ምክር የሚለግሱበት የነጻ የምክርአገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እንዲደረግ፡፡

• አማራ ክልል ከሚገኙ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ጋር ካደረግናቸው ግንኙነቶች ለመረዳት እንደቻልነው በመንግስት በኩል በቫይረሱ ሊጠቁ የሚችሉ ሰዎችን ቁጥር አሳንሶ የማየት አዝማሚያ እንዳለና ግምቱ 15 ከመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሊጎዳ ይችላል የሚል ቅድመ ትንበያ ከፌደራል መንግስት እንደተገለጸላቸው ተገንዝበናል፡፡ከፍተኛ የጤና እና የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት በዘረጉና የቫይረሱን ስርጭት በተሻለ ሁኔታ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ ተብሎ በሚታሰቡ አገሮች እንኳ በቫይረሱ ሊጠቁ ይችላሉ ተብሎ የተገመተዉ ከ50-60 በመቶ የሚሆነው ህዝባቸው ነው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሃገራችንም ከፍተኛ ዝግጅት እንዲደረግና በአገር አቀፍ ደረጃ ተገቢዉን ዝግጅትና ጥንቃቄ ካላደረግንና የበሽታውን ስርጭት መግታት ካልቻልን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሊያዙ እንደሚችሉ፣ በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ እስከ አስራአምስት በመቶ ወይም ከ1-2 ሚሊየን የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ሰዎች ህክምና ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል፣ በቂ ህክምና ካላገኙ ደግሞ በመቶ ሺዎች ሊደርሱ የሚችሉኢትዮጵያውያን ህይዎታቸው ሊያልፍ እንደሚችል ግምት ዉስጥ አስገብቶ ለዚህ ችግር ሊመጥን በሚችል መልኩ አገራዊ ዝግጅት እንዲደረግ እናሳስባለን፡፡ የጉዳቱ የግምት መጠንም ለኢትዮጵያዊያን በግልጽ እንዲገለጽ እንጠይቃለን፡፡

• በቫይረሱ የሚጠቁ ዜጎች ቁጥር ካሉን የጤና ተቋማት አቅም በላይ ሊያሻቅብ ስለሚችል ጊዜያዊ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ዝግጅት በበቂ ሁኔታ እንዲደረግ፤ ጊዜያዊ የጤና አገልግሎት ሰራተኛ ቅጥር በመፈጸም፣ እንዲሁም የህክምና ተማሪዎችን የሚያሳትፍ ጊዜያዊ ቅጥር እንዲፈጸም በማድረግ ሊያጋጥም የሚችል የጤና ባለሙያዎችን እጥረት ለመቅረፍ ዝግጅት እንዲደረግ፤ ሜቴክን ጭምሮ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ግላቮችን፣ የፊት መሸፈኛ ማስኮችን፣ የወረርሽኙን መከላከያና ልዩልዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ማምረት እንዲያተኩሩ አቅጣጫ እንዲቀመጥ እንጠይቃለን፡፡

• መንግስት በዚህ አጋጣሚ ራሳቸዉን ለአደጋ አጋልጠው የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎችን ደመዎዝና ጥቅማጥቅም በማሳደግ በከፍተኛ ሞራል ተበረታተው እንዲያገለግሉና ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በሙሉ አቅማቸው እንዲደግፉ ምክረ ሃሳብ እናቀርባለን፡፡

• ምርጫን በተመለከተ፡- ምንም እንኳን አብን ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ምርጫው በታቀደለት ጊዜ እንዲካሄድ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ወረርሽኙ ከፈጠረው አለማቀፍና አገራዊ ችግር አኳያ በተለይም የወረርሽኙ መስፋፋት በቶሎ በቁጥጥር ስር የማይውል ከሆነ በመጪዉ ነሐሴ ምርጫ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የጠበበ ስለሚሆንየብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች ጋር ውይይት በማድረግ ምርጫውን ለአንድ ዓመት ግዜ በመግፋት 2013ዓ.ም እንዲካሄድ ዉሳኔ እንዲያስተላልፍ እንጠይቃለን፡፡

• የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከሰሞኑ በውጭ አገራት ለሚገኙ ደጋፊወቹ ጥሪ አድርጎ በGoFundMe በኩል ለማሰባሰብ ከቻለው የድጋፍ ገንዘብ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ እንደሚመድብ ለአባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያኖች ማሳወቅ ይፈልጋል፡፡

• ገዥው ፓርቲ (ብልጽግና) ለምርጫ ቅስቀሳና ተያያዝ ስራወች በሚል ከሳምንት በፊት በሚሌንየም አዳራሽ ከባለሃብቶች የሰበሰበውን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ጨምሮ በፓርቲ የልማት ድርጅቶች ይዞታ የሚገኘውን ግዙፍ የሕዝብ ገንዘብ ለብሔራዊ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ስራ ላይ እንዲያውለው ስንል እንጠይቃለን፡፡

• የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ የሚደረገውን ትግል በፋይናንስ ለመደገፍና ሊፈጠር የሚችለዉን የፋይናንስ እጥረት ለማቃለል ከሌሎች ዘርፎች በጀት የማዘዋወር ስራ መስራት፣ እንዲሁም አንዳንድ አስቸኳይ ያልሆኑ ፕሮጅክቶችን እንዲራዘሙ ወይንም እንዲታጠፉ በማድረግ በጀት ወደ ጤና ዘርፉ የማዘዋወር ስራ እንዲሰራ እንዲሁም መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ቫይረሱን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የሚያደርገዉን የሃብት ስርጭት ፍትኃዊና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያከናዉን እንጠይቃለን፡፡

• በተለይም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኮሮና ወረርሽኝ እየተስፋፋ በሚገኝበትና አጠቃላይ የህልውና ስጋት ጋርጦ ባለበት በዚህ ሰአት እያካሄደ ያለውን ሃላፊነት የጎደለው ህዝባዊ ስብሰባም ይሁን የካድሬ ፖለቲካዊ ስልጠና አሁኑኑ እንዲያቆም፤ ይልቁንም የክልሉ መንግስት ሙሉ ትኩረቱን የአማራን ህዝብ በአንድ መንፈስ ለኮሮና መከላከል በማሰለፍ ስራ ላይ እንዲያተኩር እንጠይቃለን።

• በጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይል እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ በጥንቃቄ ስንከታተለው የቆየንና ይህንኑም ለህዝባችን ያሳወቅን ሲሆን ሰላም በማስከበር ስም ባህላዊውን የፋኖ መዋቅርና የቁርጥ ቀን የአማራ ልጆችን ለማፈን የተያዘውን እንቅስቃሴ የምናወግዝ ሲሆን መንግስት በዚህ ሰአት ሙሉ ትኩረቱን የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋትን መግታት ላይ እንዲያውል እናሳስባለን፡፡

• የአብን አባላትና ደጋፊዎች የህዝብና የሃገር ፍቅር ከፖለቲካ ትርፍ እሳቤ በራቀ ዲሲፕሊን ወቅቱ የጣለባቸውን ታላቅ ሃላፊነት እንደሚወጡ እያረጋገጥን ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ድርጂቶች ይህንኑ እንዲያደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

3) ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዉን አስመልክቶ፡-

i. ቫይረሱ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰዉን ችግር ለመቀነስ በብዙ አገራት የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ተከትሎ ተከሰተውን የብድር ወለድ ምጣኔ መቀነስ በመጠቀም ዝቅተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች ማፈላለግና ሊዳከም የሚችለዉን የአገራችን ኢኮኖሚ እንዲጠናከር ለማድረግ እንዲውል፤ እንዲሁም እንደ ነዳጅና መድሃኒት ያሉ መሰረታዊ አቅርቦቶችን ከውጭ ገዝቶ ለማቅረብ ማዋል፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ብድር የሰጡ አገራት የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጡ በመጠየቅ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጠረውን ጊዜያዊ ጫና ለመቀነስ ጥረት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡

ii. በአገር ውስጥ ያለዉን የብድር አቅርቦት በማሻሻልና በጥናት ላይ የተመሰረተ የወለድ ምጣኔ ቅነሳ በማድረግ በወረርሽኙ ምክንያት በተለየ የሚጎዱ እንደ ቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፉን ለመደገፍ በዝቅተኛ ወለድ የብድር አቅርቦት የማመቻቸት፣እንዲሁም ትላልቅ ካምፓኒዎች ሰራተኛ እንዳይቀንሱ ድርድር የማድረግና ማበረታቻ የማቅረብ፣ ብድር ያለባቸዉን ድርጅቶችና ነጋዴዎች የብድር መመለሻ እፎይታ ጊዜ አንዲመቻች እንጠይቃለን፡፡

iii. በውጭ ምንዛሬ ችግር ምክንያት ወደ አገር ዉስጥ ማስገባት ለምንቸገርባቸው ምርቶች በአገር ውስጥ አምርቶ መተካት (import substitution) ዉስጥ እንዲሳተፉ ማበረታቻ እንዲደረግ፤ እንዲሁም ሊፈጠር የሚችለውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተቀጣሪዎች የግብር ተቀናሽ ለጊዜው ማስቀረትና አዲስ ሰራተኞችን ለሚቀጥሩ ካምፓኒዎች የታክስ ማበረታቻ መስጠት፤ ስራ ፈጠራ ጋር ተያይዞ ያሉ የቢሮክራሲ ሂደቶችን በማስቀረት አዳዲስ ቢዝነሶች ወደ ስራ እንዲገቡ ማበረታታት ኢኮኖሚውን ከውድቀት ሊታደግ እንደሚችል እንመክራለን፡፡

iv. ከውጭ የሚገባው የሃዋላ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ እንዲገባ ለማበረታታት የውጭ ምንዛሬ ገበያውን መንግስት ከሚወስንበት ስርዓት (fixed exchange rate) ወደ ነጻ የምንዛሬ ስርዓት (free exchange rate) መቀየር በዚህ አጋጣሚ እንዲጀመር እናሳስባለን፡፡

4) በመጨረሻም አገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ላደረጉት ተጋድሎ መሪና ደጋፊ የነበረች መሆኗን በማስታወስ በአፍሪካ ደረጃ የሚደረገዉን የቫይረሱን ወረርሽኝ የመዋጋት ስራ በአህጉር ደረጃ ማቀናጀት እንዲቻልና በአህጉር ደረጃ አገራችን የሚጠበቅባትን ሃላፊነት እንድትወጣ የአፍሪካ ህብረት (African Union) አስቸኳይ ጉባኤ እንዲጠራ የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን እንዲያቀርብና በአህጉር ደረጃ የተቀናጀ የኮሮና19 ምላሽ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ መሪነታችን እንድንወጣ አብን ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያንና ህዝቧን ፈጣሪ ይባርክ!
ሰላምና ጤና ለአለማችን ይሁን!

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top