Connect with us

ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን!

ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን!
Photo: Catherine Hamlin Fistula Foundation

ባህልና ታሪክ

ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን!

ታካሚዎቹ “እማዬ!” ነው የሚሏቸው አሉ፡፡ እጅግ ይወዷቸዋል፡፡ እርሳቸውም ምን ቢያማቸው፤ አቅማቸው ቢደክም ጠዋት ላይ አዝግመው እነርሱን ሳያዩ አይውሉም፡፡ አቅፈው፤ ስመው አበረታተዋቸው ነው የሚሄዱት፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ቀዶ ህክምናውን የሚሰጡትም እርሳቸው መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡

የሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታልን በመመስረት ከ60 ሺህ በላይ ሴቶችን አክመዋል፤ አካላቸውን ብቻ ሳይሆን አዕምሯቸውንም ጭምር፡፡ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት በአዲስ አበባ የሚገኘውን ፊስቱላ ሆስፒታልን ተማሪዎችና መምህራንን ለማስጎብኘት በሄድኩበት ወቅት፤ የታካሚዎቹ ቤቶች በጎጆ ቤት ቅርጽ መሰራቱ፣ ከቤቶቹ በታች የሚፈስ ወንዝ መኖሩ፣ በዛፍ መከበቡ፣ በአበቦች ያጌጠ መሆኑ አብዛኞቹ ታካሚዎቹ ከገጠር የመጡ በመሆናቸው፤ ቀያቸውን ጥለው የመጡ እንዳይመስላቸው የተደረገ መሆኑን ስሰማ እጅግ ነበር የገረመኝ፡፡ ያኔ ትንሽ አሟቸው ተኝተው ስለነበር በአካል አላገኘኋቸውም፡፡

ዶ/ር ካትሪን የሚኖሩት እዚያው ግቢ ውስጥ ባለው ቤት ነው፤ በወቅቱ ያስጎበኘን የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አስቻለው ፤ “የቤታቸው የውስጥ ግድግዳ ተላልጦ ስናይ፤ ‘ይታደስልዎት’ አልናቸው፤ ‘በማን ገንዘብ? በሴቶቹ ገንዘብ? አልነካም፡፡ ቀስ ብዬ በራሴ ገንዘብ ይታደሳል’ አሉ” በማለት እምቢ ማለታቸውን አጫውቶናል፡፡ ያረፉትም በዚችው ቤታቸው ነው፡፡

እርሱም አለ፡፡ “የሕዝብ ሃብትና ንብረት መዝብሮ በሚሊየኖች የተገዛ መኪና የሚያሽከረክር ነው ኢትዮጵያዊ? ወይስ እኝህ ሴት?” እውነቱን ነው፡፡ ዶ/ር ካትሪን ወጣትነታቸውን ያሳለፉትም ለኢትዮጵያ በመትጋት ነው፡፡

ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ወጣት ነበሩ፡፡ ከ60 ዓመታት በላይም ያለመታከት ኢትዮጵያን አገልግለዋል፡፡

ያኔ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደልብ ባልነበረበት ዘመን የህክምና ቁሳቁሶችን በመርከብ እያስጫኑ እርሳቸውም ለወራት እየተጓዙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ለመርዳት አልታከቱም ነበር፡፡

እናመሰግናለን ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን!
ነፍስዎ በሰላም ትረፍ!
(ፍሬህይወት ካሳ መሐመድ)

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top