Connect with us

ለግድቡ ስኬት ምሁራን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ

ለግድቡ ስኬት ምሁራን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ

ባህልና ታሪክ

ለግድቡ ስኬት ምሁራን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ እንዲሆን ምሁራን የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ተጠየቀ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀውና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ዓባይ ላይ ያተኮረ የምሁራን የምክክር መድረክ ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ኢትዮጵያ ለዘመናት የበይ ተመልካች ሆና የቆየችበትን የዓባይን ወንዝ እንድትጠቀም የተጀመረው ስራ ስኬታማ እንዲሆን ምሁራን የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

አገሪቱ ሐብቷን እንዳትጠቀም ተጭነውባት የነበሩ ኢ-ፍትሐዊ ክልከላዎች መቆም እንዳለባቸው ወስና ከዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ ተጠቃሚ ለመሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች እንደሆነ ገልጸዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ምሁራን ይህን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል።

የግድቡ ግንባታ ስኬታማ ሆኖ ኢትዮጵያ ከሐብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ምሁራን ጥናት የማቅረብና የማማከር ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ግድቡ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲከናወን የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ‹‹በዘመነ ቅኝ ግዛት የተደረገን ኢ-ፍትሐዊና የውሃውን ዋና ባለቤት ያላካተተ ስምምነት ለመቀበል ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ታ ች ን አ ይ ፈ ቅ ድ ልን ም › › ብለዋል።

‹‹የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማት የግድቡን ስራ በገንዘብ እንዳይደግፉ ሴራ ተሲሮብናል›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለግድቡ ግንባታ ሁሉም ዜጋ በፀሎት፣ በሐሳብ፣ በገንዘብና በእውቀት ዋጋ የከፈለበትና ተሳትፎ ያደረገበት እንደሆነም አስታውሰዋል፤ከዚህ በኋላም የግድቡ ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋ ጉዳይ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል።

‹‹ግድቡ ግዙፍ የልማት ስራዎችን በራሳችን አቅም መገንባት እንደምንችል ለዓለም የምናሳይበትና ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ብዙ መልዕክቶችን ለዓለም ህዝብ የምናስተላልፍበት ፕሮጀክት ነው›› ብለዋል።

በድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሐብቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ፤ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸውና ከዚህ ቀደም የተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈሩ በመሆናቸው ተቀባይነት እንደሌላቸው ከኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ቢገለፅም የግብፅ ባለስልጣናት ግን ስምምነቶቹ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በቬይና ኮንቬንሽን መሰረት አንድ አገር ተሳታፊ ያልሆነችበትን ስምምነት የማክበር ግዴታ ስለሌለባት ኢትዮጵያም ባልተሳተፈችባቸው የቅኝ ግዛት ዘመናት ስምምነቶች የመገዛት ግዴታ እንደሌለባት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የውሃው ባለቤትና ምንጭ ሆና ሳለ የተፋሰሱ አገራት ውሃውን በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙ ያሳየችው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የሚያስመሰግናት ነው ብለዋል።

ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ውስጥ ተደራዳሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ ሲጠነሰስ ጀምሮ በፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እያራመደች እንደምትገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ግብጽ ይህን የፍትሐዊነት አጠቃቀም መርህን የሚቃረን አቋም እንዳላት ጠቁመዋል።

ካለፈው ጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄዱ ባሉት ድርድሮች ላይም እያሳየችው ያለው አቋም ይህንን የፍትሐዊነት አጠቃቀም መርህን የሚፃረር እንደሆነም ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም ከዓባይ በተጨማሪ በሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች ላይም መሰል ጥያቄዎች መነሳታቸው ስለማይቀር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ከወዲሁ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ኢንጂነር ጌዲዮን አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፤ ግብጽ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ለዘመናት ስታራምደው የቆየችው አቋም ፍትሐዊነት የጎደለው ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ሀብቱን በጋራ ለመጠቀምና ለድርድር ዝግጁ እንደሆነች በተደጋጋሚ አሳይታለች ብለዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ዓባይን የምትጠቀመው ለቅንጦት ሳይሆን ለልማትና ለእድገት ነው›› ያሉት ዶክተር ያዕቆብ፣ ኢትዮጵያ የምታቀርባቸው የድርድር ሃሳቦች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የፍትሐዊነት ማሳያዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።

ከአሜሪካ የቪዲዮ ገለፃ ያቀረቡት ዶክተር ዮናስ ብሩ በበኩላቸው፤ ግብጽ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላት አቋም ፍትሐዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ግብጽ ውሃውን የምትጠቀመው በውሃው ላይ ብክነት በሚፈጥር መልኩ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ላይ አጀንዳ ተቀባይ ከመሆን እንድትወጣና ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን በማጠናከር በግድቡ የመጠቀም መብቷን ለቀሪው ዓለም የማሳወቅ ስራዎች በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

አዲስዘ መን መጋቢት 05 ቀን 2012 ዓም

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top