Connect with us

ኮሮና እና እኛ

ኮሮና እና እኛ
Photo : Facebook

ጤና

ኮሮና እና እኛ

ኮሮና እና እኛ | (ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

የኮሮና ቫይረስ በራችንን አንኳኩቶ ሰተት ብሎ ገብቷል። መደንገጥ አያስፈልግም። በባዶ ሜዳ “ዘራፍ” ብሎ መኮፈስም አይበጅም። እንዲያውም ቢቻል “እንኳን ደህና መጣህ” ብሎ መቀበል እና አገር በቀል መፍትሔ መዘየድ ያዋጣል።

በኮሮና ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች ነን ብዬ አስባለሁ። እስካሁን ቫይረሱ ሳይጎበኘን ያረፈደው በመከላከል ረገድ ከአውሮፓና ከአሜሪካኖቹ ስለላቅን እንዳይመስልህና እንዳትሸወድ። ፈጣሪ ስለሚወደን ነው። ልብ በል!… የኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያ ተጠቂ በቻይናዋ ወሀን ከተማ መታየቱ የተሰማው በእኛ አቆጣጠር ህዳር 7 ቀን 2012 ዓ.ም (ኖቬምበር 17 እኤአ) ነው። እስቲ አስበው የዛሬ ሶስት ወይንም አራት ወር ከቻይና ቀጥሎ ትላንት ቫይረሱ የታየበት ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ሌላው ቀርቶ በውሀ እሽኮለሌ ከገጠመችን ከግብፅ በፊት አድርጎን ቢሆን ኖሮስ? አትጠራጠር!…ዓለም በአንድ ጀምበር እርግፍ አድርጎ ይተወን ነበር። ሌላው ቀርቶ ሸምተን የምናስገባው ሸቀጥ እንኳን ይጠገርርብን ነበር።

ሲያድለን፤ ከዓለም 138ኛ ገደማ አሰለፈን። እነቻይና፣ ኢጣሊያ፣ ኢራን፣ደቡብ ኮርያ፣ ስፔን፣ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ሲዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ… በበሽታው በመያዝም በሞትም በቅደም ተከተል ቀድመው መሰለፋቸው ከእኛ አንፃር ስናየው ለበጎ ነው። እነዚህ ሀያላን ቀድመው ባይቀምሱት ኖሮ ዛሬ እኛን ካካ እንደነካው እንጨት በተጠየፉን ነበር።

ወዳጄ ወደገደለው ልግባ። እስካሁን ባለው መረጃ ኮሮና ያን ያህል ገዳይ በሽታ ተብሎ በአስፈሪነት የሚፈረጅ አይደለም። ይህን ያልኩት እኔ ሳልሆን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ነው። አባባሌን በቁጥሮች ለማስደገፍ ያህል፤ እስከትላንት እኩለ ለሊት ድረስ ቫይረሱ ወደ 138 አገራት ዘልቆ ገብቷል። በእነዚህ አገራት 145 ሺ 360 ህዝብ በቫይረሱ የተያዘ ሲሆን 70 ሺ 931 ያህሉ አገግሟል። 5 ሺ 416 ሰዎች ደግሞ ገደማ እስከወዲያኛው አሸልበዋል። የሟች ቁጥሩ ከተያዘው አንፃር ሲሰላ 4 በመቶ ገደማ ነው። እናም ተመስገን ነው። እንደአስፈሪነቱ ገዳይ ቢሆን ኖሮ ዓለም ጉድ ፈልቶባት ነበር።

ይኸም ሆኖ ኮሮና ቫይረስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እጅግ አስፈሪ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ለምን? እንደእኔ እንደእኔ ሶስት አበይት ምክንያቶች አሉ። አንዱና ዋናው የጤና ሥርዓታችን እጅግ ደካማ የመሆኑ እውነታ ነው። በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ የተደራጁ የህክምና ማዕከላት የሌሉን መሆኑ ግዙፉ ችግራችን ነው። ሌላው ድህነታችን ነው። የትራንስፖርት ችግሩ ብቻ ደራርቦ፣ አስተቃቅፎ የሚያጓጉዝ ነው። አኗኗራችን፣ የንፅህና አጠባበቅ (ሳኒቴሽን) ስርአታችን እጅግ ሀላቀር መሆኑ ከባድ ችግር ነው። እንደአገር የንፁህ መጠጥ ውሀ ስርጭታችን ገና እንጭጭ ነው። ሌላውና ሶስተኛው ምክንያት ጥብቅ የሆነ ማህበራዊ ትስስራችን ለኮሮና ስርጭት የሚመች የመሆኑ ጉዳይ የሚጠቀስ ነው። ሰብሰብ ብለን በምክንያት ከመብላት ከመጠጣት በተጨማሪ በደስታ እና በሀዘን ተሰባስበን መዋላችን ኮሮና ጭንቅላታችን ላይ ጎጆ እንዲቀልስ ሊያደርግ የሚችል ነው።

እናም መዳኛ መፍትሔው ዘልማዳዊ እሳቤዎችን ቆርጦ መጣል ነው። የባለሙያዎችን ምክር ያለማንገራገር መተግበር ብቻ ነው።
ከማሳረጌ በፊት እንደአገር ወግ ልመርቅ። ከሚፈራው፣ ከሚወራው መቅስፈት ፈጣሪ ይጠብቀን። እኛም የሐኪሞችን ምክር ሰምቶ በመተግበር ራሳችንን፣ ቤተሰባችንን፣ አገራችንን ለመጠበቅ ይርዳን። አሜን!!

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top