Connect with us

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ
Photo : Facebook

አለም አቀፍ

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ

ከጋዜጠኛ ሁሴን ከድር

ጉዳዩ ፦ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚልን በእጩነት ስለማቅረብ

በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንና ሕዝቦቿ የሚሊኒየሙን ግድብ በከፍተኛ ሞራልና ወኔ ገንብተን ለማጠናቀቅ በዝግጅት ላይ መሆናችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት አንዲት ሲኒ ውሃ እንኳ ለአባይ የማታበረክተው ግብጽ ጥቅሜን ይጎዳብኛል በሚል ተልካሻ ምክንያት በኮሎኒያሊዝም ዘመን በነበረ ኢትዮጵያ በገዛ ንብረቷ ባልመከረችበትና ባልፈረመችበት ስምምነት ልንዳኝ ይገባል፡፡ ግድቡ በውሃ ለመሙላት ረጅም ዓመታት መፍጀት አለባችሁ፣ እኛ ስንበላ እናንተ ጉልበታችሁን ታቅፋችሁ እስክንጠግብ ተመልከቱን የሚል የሚመስል ስምምነት እንድንፈርም በአሜሪካ አስገዳጅነት እየታገለች እንደሆነ እየተከታተልን ነው፡፡
ግብጽ እራሷ አጥፍታ በዓለም ዙርያ ዲፕሎማቶቿን እያላከች ኢትዮጵያ በረሃብ ልትቀጣኝ ነው እያለች ስማችንን እያስጠፋች ትገኛለች፡፡ የግብጽን ቅስቀሳ የሰሙ አንዳንድ አረብ አገራት ‹‹እውነቷን ነው ከግብጽ ጎን ነን›› በማለት በበደል ላይ በደል እየጫኑብን ነው፡፡

ይህንኑ የግብጾችን ጩኸት በእኩል ደረጃ ሊመክት የሚችል በቋንቋቸው፣ በደረጃቸው ሊመክት የሚገባ ዲፕሎማት ያስፈልገናል፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ብዙ ነገር እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ከሲቪል ማኅበረሰቡ መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በአረብ አገራት ከሚመደቡ የሎቢ ግሩፕ ዲፕሎማቶች ጋር ተካትተው በከፍተኛ የማሳመን ብቃታቸው ሀገራቸውን ይረዳሉና ክቡርነትዎ እንዲካተቱ ቢያደርጉ የጠረጴዛ ዙርያ ጦርነቱን በብቃት ያሸንፋሉ ብዬ በመገመት ነው፡፡

ጥቂት ስለረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል የማውቀውን ያህል ልንገርዎ፡-

ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በ1952 በወሎ ወርሳሜሳ ተወልደው ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ በሳውዲአረቢያ የመኖር እድሉ አጋጥሟቸዋል፡፡ በዚህም ወቅት የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃና የዩንቨርስቲ ትምህርታቸውን ተምረው በኢኮኖሚክስና ኢንተርናሽናል ሪሌሽን ሺፕ ተመርቀው በ1980 ጀምሮ በሀገራቸው ለመስራት ጥረት ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡
የቱሪዝም ድርጅት ከፍተው ለመሥራት ቢታገሉም ደርግ አስናክሏቸው ከሀገራቸው ወጥተው የነበረና ኢህአዴግ ከገባ በኋላ መመለሳቸውም ይታወቃል።

በጋዜጠኝነት ከ1986 ጀምሮ የአፍሪካ ቀንድ መጽሔት ባለቤት በመሆን ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃንና ጋዜጠኛ ነብዩ ሲረክን በመያዝ መጽሔቱን ሲያዘጋጁ ቆይተው በወቅቱ በነበረው የፕሬስ አፈና ከገበያ ወጥተዋል፣ ከዚህም በኋላ ‹‹አል-ሪሳላ›› የሚል ጋዜጣ በባለቤትነትና በማዘጋጀትም ማኅበረሰቡን በሚዲያ የማስተማሩን ስልት በተለያየ መንገድ ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡

ጋዜጣቸው ከገበያ ከወጣ በኋላም በየጊዜው በተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች በመቅረብ ሳይታክቱ የኢትዮ-አረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ስለ እስልምናና ሐበሻ፣ ኢትዮጵያ በእስልምና ያላትን ደረጃ የሚያሳዩ ፣ አረቦች የኢትዮጵያውያን ባለ እዳ ስለመሆናቸው ደግመው ደጋግመው በተለያየ ምሳሌ ሳይታክቱ አስረድተዋል፡፡ በእሳቸው ማብራርያ ብዙዎች የሐበሻን ደረጃ መገንዘብ ችለዋል፡፡

በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ላለፉት 27 ዓመታት ያደረጉትን ጥናት በመጽሐፍ መልክ ለማውጣት ከ2005 ጀምሮ የሐበሾች ክብርና ሞገስ በእስልምና፣ ሐበሾች በነብዩ ዙርያ፣ የሐበሾች አሻራ በእስልምና የሚሉና ሌሎችም አራት መጽሐፍትን ለኅትመት አብቅተው ሃሳባቸውን አስርጸዋል፡፡ በቅርቡም ኢትዮጵያን በኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ አፍሪካ አረቢካ እንድትታወቅ በመረጃ አቀራረብ ከአፍሪካ በአንደኝነት እንድትነሳ አድርገዋል፡፡

በመላው ዓለም እየዞሩ ኢትዮጵያን በተመለከተ በእስልምና ያለንን ደረጃና የአረቡ ዓለም የኢትዮጵያ ባለእዳ ነው በማለት ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ በአፍሪካ ሀገራት፣ በአውሮፓ፣በእስያ እና በአሜሪካ በተጋበዙባቸው ዩንቨርስቲዎች ደጋግመው በመሄድ ደረጃችንን አልቀውታል፡፡

ከጻፏቸው መጽሐፍት በጥቂቱ ያነሷቸውን ነጥቦች ጠቅሼ ወደ ነጥቤ ላምራ

‹‹እ.ኤ.አ. በ1979 ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በንጉሥ አብዱልአዚዝ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ያጋጠመኝ ጉዳይ ነው፡፡ ይኸውም አላህ ይርሃማቸውና መምሕሬ የነበሩ ሰው የሐበሻ ተወላጅ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ መሆኔን እንዳወቁ እንዲህ አሉኝ፤

#…እናንተ ሐበሾች በእስልምና ውስጥ ያላችሁን ክብርና ደረጃ ራሳችሁ አውቃችሁ ለሌላው ማሳወቅ ሳይሆን፣ ስለ እናንተ የተፃፈላችሁን እንኳ አንብባችሁ መረዳት አልቻላችሁም…$ በማለት የተናገሩኝ ቃል ውስጤን ሲቆጠቁጠው በመኖሩ ነው፡፡

ትምህርቴን ጨርሼ እዚያው ባሕረ ሰላጤው አካባቢ በሚገኙ ሀገሮች ውስጥ በኮንትራክተርነት ሙያ ላይ ተሰማርቼ በምሠራባቸው ጊዜያት አንድ የሥራ ባልደረባዬ ከሆነ ግብፃዊ ኢንጂነር ጋር እጅግ ተግባብተን አብረን እንሠራ ነበር፡፡ ይኸው ግብፃዊ የሥራ ባልደረባዬ የነበረው ኢንጂነር አንድ ቀን በጨዋታ መሀል እንዲህ አለኝ፡፡

#…ቢላል አል ሐበሺ ግብፃዊ ቢሆን ኖሮ በየዓመቱ ረመዷን 20 ቀን በሀገራችን በእሱ ስም ብሔራዊ የበዓል ቀን ብለን በሰየምነው ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህች ቀን ነቢዩ ሙሐመድ(ሰዐወ) የኢስላምና የእስልምናን ጠላቶችን ድል አድርገው መካን የተቆጣጠሩባት ዕለት ነች፡፡ በዚያች ቀንም መካ እና ሐረም በሙስሊሞች መዳፍ የገቡበት እና ነቢዩላህ ኢብራሂም (ዐሰ) በአልበቀራ ምዕራፍ አንቀፅ 129 ፈጣሪያቸውን የጠየቁት ጥያቄ መልስ ያገኘበት እና ታላቅ የኢስላም የድል ቀን መሆኗን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚያ የሚያምር መረዋ ድምፁ ያወጀውና ያረጋገጠው ቢላል አል ሐበሺ ነው፡፡$ በማለት አጫወተኝ፡፡

ታዋቂው ደራሲ ማሕሙድ ሻኪር #ኢስላማዊ ስደት ወደ ሐበሻ$ በሚለው መጽሐፉ ሙስሊም ምሁራንና ፀሐፊዎች ስለ እስልምና ሃይማኖትና ስለ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በሰፊው ዘግበዋል፣ ፅፈዋል፡፡ ምክንያቱም ከእምነታቸውና ከሕልውናቸው ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው፡፡ አንድ ግን የተዘለለና ትኩረት ያልተሰጠው ትልቅ ታሪክ አለ፣ ይኸውም ወደ ሐበሻ የተደረገው ኢስላማዊ ስደት እቅዱና አላማው ሲሆን ፈጣሪን የምለምነው አንድ ቀን ይህ ታሪክ ባለቤት አግኝቶ አውቆ እንዲያሳውቀው ምኞቴ ነው በማለት የፃፈውን በማንበቤ ነው፡፡

እንግዲህ በእነዚያ አፍላ የወጣትነት ዘመኔ እነዚህ ሦስቱ ትውስታዎች በህሊናዬ እየተመላለሱ ለረጅም ጊዜያት ውስጤን ሲያብሰለስሉት ቆይተዋል፡፡ ……

የሐበሾች አሻራ በእስልምና

‹‹በርካታ የምርምርና የጥናት ማዕከላትም ይህንን ዓለም አቀፋዊ መሠረትና ይዘት ያለውን የእስልምና ሃይማኖት አጀማመር፣ መስፋፋትና ዕድገት ለማጥናት ልዩ ትኩረት የሰጡት ከመሆኑም በተጨማሪ የእነዚህ የምርምርና ጥናት ማዕከላት ፀሐፊዎች ለዚህ ታሪክ ከፍተኛ ግምት በመስጠት በከፍተኛ ፍጥነት ከዓለም ዳር እስከ ዳር የመስፋፋቱ ምስጢርና በየዘመናቱ ያጋጠሙትን ችግሮች በማጥናት የሚወያዩበትና የሚዳስሱባቸው መድረኰች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ይህ በመላው ዓለም ከተራው ሕዝብ እስከ ከፍተኛ ምሁራን ድረስ ያሉትን ሁሉ ቀልብ መሳብ የቻለ ከመሆኑ አንፃር ምንም እንኳ ዋነኞቹ ባለቤቶቹ ታሪኩን ከጅምሩ አንስቶ በዝርዝሩ እያስተነተኑ የመፃፍ አቅሙና ችሎታው አልነበራቸውም፡፡

የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ባጠቃላይ ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ታሪኩ ከእምነቱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲጠናና እንዲታወቅ የሚለው ጥሪ በተደጋጋሚ እየተሰማ በመሆኑ፣ እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎችም በርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ይህንን ታሪክ እንዳተኩርበት አድርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሙስሊምነቴና እንደ ኢትዮጵያዊነቴ አቅሜ በሚፈቅደው መጠን በተለይ ለሀገሬና ለሕዝቦቿ፣ ለሀገር እድገትና ለብልፅግና፣ ለልማትም ሆነ በታሪክ ቅርስነት ሊያስገኝ የሚችለውን ብሔራዊ ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ለግብዓትነት የሚያስፈልጉኝን ጠቃሚ መረጃዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የማሰባሰብ ዘመቻ አካሂጃለሁ፡፡ እነዚህ ጠቃሚ መረጃዎች የሚገኙበት ምንጩ የዓረብኛ ቋንቋ ስለሆነ በተለያዩ የዓረብ ሀገሮች ውስጥ በሚገኙ የታወቁ የመዳሕፍት መሸጫ መደብሮችና ቤተ መጻሕፍት እየተዘዋወርኩ የማሰባሰብ እንቅስቃሴዬን ከጀመርኩ ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥሬያለሁ፡፡

እዚህ ላይ ለአንባብያን ማሳሰብ የምፈልገው ይህ የመጀመሪያው መጽሐፌ የ25 ዓመት የማሰባሰብ ዘመቻ ውጤት መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ከታሪኩ ስፋትና ጥንካሬ አንፃር አሁንም ቢሆን ቀጣይና ያልተቋረጠ ስር የሰደደ ጠንካራ የማሰባሰብ ዘመቻ የሚያስፈልግ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡በዚህ የመጀመሪያ ጥናታዊ መጽሐፌ ቁጥር 1 ውስጥ በተዳሰሱት ዓበይት ርዕሶች ተካትተው የሚገኙት፡-

1ኛ፡- የኢትዮ ዓረብ ጥንታዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በተመለከተ

በ2ኛው ምዕራፍ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ስልጣኔ በአካባቢው ምስራቅና ሰሜን ሀገሮች ውስጥ ያለው አሻራ፣

በ3ኛው ምዕራፍ የእስልምና ስደት ወደ ሐበሻ ዓላማው፣ ዕቅዱና ውጤቱ፣

በ4ኛው ምዕራፍ ሐበሾች በቁርአን፣ በሀዲስና በነብዩ (ሰዐወ) ልዩ አቋም የተሰጣቸው ክብር፣

በ5ኛው ምዕራፍ የንጉስ አስሃማ ታሪክ፣ በሚሉ አበይት ርዕሶች ተከፋፍለው ቀርበዋል፡፡

ይህ ባለበት ሁኔታ የዚህ ታሪክ ክብርና ሉዓላዊነት ዓለም አቀፋዊ ትኩረት መሳብ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የታሪኩ ባለቤቶችና ባለጉዳዮቹ ዝምታና ቸልተኝነትን በመምረጣችን ይህ ታሪክ ከኢንቨስትመንት፣ከቅርስ፣ከታሪክ፣ከቱሪዝም ገቢ ጥቅም አንፃር ግምት ማስገባት ባለመቻላችን ሌሎች ሀገሮችና ዜጐች የእኛ ነው የሚል የታሪክ ሽሚያ አነሱ፡፡ ለዚህም ትክክለኛ ማስረጃው እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ል በለንደን የሚገኘው አልሙስተቂላ የሚባለው የቴሌቪዥን ቻናል ለ9 ቀናት ያህል ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የተለያዩ ምሁራንን በመጋበዝ #ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገሮች ሳይቀር መስማማት ያልቻሉበትን የሰብዓዊ መብት፣ የሃይማኖት መቻቻልና የሙስናን መዘዝ ከ1400 ዓመት በፊት የሐበሻው ንጉሥ ነጃሺ ተግባራዊ ማድረጉና ከእሱ ምን እንማራለን;$ በሚል ርዕስ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡

ሌላው ከፍተኛ የውይይት መድረክ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ል ኳታር፣ ዶሃ በሚገኘው የዓረብ የጥናትና የምርምር ማዕከል አማካይነት የገልፍና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ግንኙነቶችን በተመለከተ ለ3 ቀናት በተካሄደ ውይይት ላይ 80 ከመቶው ሐበሻ በእስልምና ያላት ታሪክ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር፡፡ በነዚህ ሁለት ዓለም አቀፍ የውይይት መድረኰች ላይ ከእኛ ከታሪኩ ባለቤቶችናባለጉዳዮች አንድም ተሳታፊ አልነበረም፡፡ በለንደኑ ውይይት ላይ ከመድረክ በኢንተርኔትና በስልክ በነበረው ተሳትፎ የተሰነዘሩት ሀሳቦች እጅግ አሳዛኝ ነበሩ፡፡ ይኸውም ከሱዳንየተገኙት ተሳታፊ ኢስላማዊ ስደቱ በሙሉ የተካሄደው ወደ ሐበሻ ሳይሆን ወደ ሱዳን እንደነበር፣ ነጃሺ የሚባለው ንጉሥም ሆነ የመጀመሪያው ሙአዚን ቢላልና ነቢዩን (ሰዐወ) ያጠባችውና ያሳደገችው ኡሙ አይመን ሳትቀር ሱዳናዊያን ናቸው የሚል አቋም ይዘው የቀረቡ ሲሆን እንደ መረጃ አድርገው ያቀረቡትም ሱዳናዊው ሱሌይማን ሳልህ ዲራር የተባለው የታሪክ ፀሐፊ #አል ቢጃ$ በሚል ርዕስ የፃፈውንና ሱዳናዊውፕሮፌሰር አብደላ አጠይብ በተለያዩ መድረኰች ያቀረባቸውን ጥናቶች፣ በተጨማሪም ሱዳናዊው ዶ/ር ሀሰን ሼህ አልፋቲህ የተባለው #ሱዳን ዳሩል አል ሂጅረተይን አል ኡላ ሊስሃባ$ በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን መጽሐፉን መረጃና ዋቢ በማድረግ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ኤርትራዊያንም የታሪክ ሽሚያው ተካፋይ ሆነው ነበር፡፡ በተለይ በአሜሪካ የሚኖሩ ኤርትራዊያን በጁምአ ቀን በአንድ መስጊድ ውስጥ ኰሚቴ በማዋቀር #እኛ የነጃሺ ዜጐች ነን$ በማለት ርዳታ ሁሉ ያሰባሰቡት የታሪክ ሽሚያ ተፈፅሟል፡፡

ይህ የታሪክ ሽሚያና ዘረፋ ሲፈፀም ባለቤቶቹ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን ዝምታን መርጠን ተኝተናል፡፡ የታሪኩን እውነታን ለመጠበቅ ሲባል የተደረገውን የታሪክ ሽሚያ ለመከላከል በዜግነት ኢትዮጵያዊ ባይሆኑም እንደ ታሪክ ምሁርነታቸው በዚህ መድረክ ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ከፍተኛ ትግል ያካሄዱት ባሁኑ ወቅት በሳዑዲ ናይፍ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ጀላሉዲን ሙሐመድ ሳልህ ናቸው፡፡ ምሁሩ ባቀረቡት የመከላከያ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ኤርትራን በተመለከተ፣#ኤርትራን ጣሊያኖች ከ60 ዓመት በፊት በቅኝ ግዛትነት ነጥለው የያዟት የሐበሻ አንድ አካል የሆነች ነበረች፡፡ ሁለተኛ ሱዳናዊያን ላቀረቡትም ሱዳን የሐበሻ ነበረች ከተባለ መቀበል ይቻላል እንጂ ሐበሻ ግን የሱዳን ነበረች የሚለው አባባል ሐበሻ ካላት የረጅም ዘመናት ታሪኳ አንፃር ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ ስደቱ የተደረገው በቀጥታ ወደ ሐበሻ መሬት ነበር፡፡ በዛሬው ጊዜ የትግራይ ክልል ተብሎ በሚጠራው አክሱም ከተማ በነበረው ንጉሥ አስሃማ ቢን አብጀር መስተንግዶ የተካሄደ ስደት ነበር፡፡ ይህን ታሪክ በተመለከተ ብዙ መረጃዎች በዋቢነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ምንም እንኳ የታሪኩ ባለቤቶች ባይንቀሳቀሱና ባይጠብቁትም ታሪኩ ግን እንደ ታሪክ ክብሩንና እውነቱን ጠብቆ መቆየት አለበት፡፡ ሱዳናዊያን ፀሀፊዎች ያቀረቡት ሀሳብ በሙሉፈፅሞ አሳማኝነት የሌለው በመሆኑ ተቀባይነት የለውም$ በማለት ላንቀላፋነው የታሪኩ ባለቤቶች ተከራክረውልናል፡፡

በመቀጠልም #በጣም የሚያሳዝነው ሐበሻ ወይም ኢትዮጵያ ባለፈው ዘመን ታሪኳ በእሷና በዓረቡ ዓለም ያላትን ጥንታዊ የታሪክና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጠቀም ስትችል ከዓረቡ ዓለምና ከሙስሊሙ ዓለም ርቃ ከአውሮፓውያን ጋር የስትራቴጂ ግንኙነቷን አጠናክራ መቀጠሏ ነው፡፡ምንም እንኳ ከእስልምና እና ከዓረቦች ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ባይኖራትም የኰሞሮስ ደሴት እንኳ የዓረብ ሊግና የሙስሊም ሀገሮች ትብብር አባል በመሆን ተጠቃሚ መሆን ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለነኚህ ድርጅቶች ጀርባዋን ሰጥታ ትገኛለች፡፡ በተለይ በደርግ ዘመን የሶቪየት ህብረት ኤክስፐርቶች አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ሲጐበኙ ኢትዮጵያ ካላት ኢስላማዊ ታሪኳና ከዓረቡ ዓለም ጋር በጂኦግራፊና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በዩኒቨርስቲዎችዋ ውስጥ የእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ ዲፓርትመንት ሲኖራት የዓረብኛ ቋንቋ መማሪያ ዲፓርትመንት አለመኖሩ በጣም ያስደንቃል$ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌሎች ሀገሮች በዚህ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የገቡት ከዚህ ታሪክ በኢኰኖሚ ደረጃ ያለውን ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ግምት በማስገባት ነው፡፡ በተለይ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት፣ በቅርስና በታሪክ ያለውን መስህብ በማጠናከር ዋና የገቢ ምንጭ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ነው፡፡

የሀበሾች አሻራ በእስልምና

ከዚህ ቀን ጀምሬ ሀበሻን በእስልምና ያላትን ክብር መመራመር እና ማጥናትን ስራዬ ብዬ ጀመርኩኝ፡፡ ከነኚህ ጥናቶች ውስጥ እስላማዊ ስደት ወደ ሀበሻ ዓላማው እና እቅዱ እንዲሁም ውጤቱ፣ሀበሾች በነብዩ ዙርያ ፣ የሀበሾች አሻራ በእስልምና እነኚህ በመጽሀፍ መልክ ተዘጋጅተው ለህትመት የበቁ ሲሆን ሌሎች ወደ 22 የሚሆኑ ጥናቶች በተለይም የገጠር ዑለማዎች ታሪክ በሚል የተዘጋጀው ለህትመት ያልበቃ ስለሆነ ለአንባብያን አልደረሰም፡፡

እስልምና ብቸኛው መፍትሔ

እነዚህን መጽሐፍት ጽፈው ለሕብረተሰቡ አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰር አደም ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ በመሆኑ በውጭ ሀገራት የመኖርና የመሥራት ከፍተኛ ገንዘብ የማግኘት እድል እያላቸው በሀገራቸው ተወስነው በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተወስነው ሀገራቸውን እያገለገሉ ነው የሚገኙት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እኒህን ውድ ኢትዮጵያዊ በጋዜጠኝነት ሥራዬ አጋጣሚ ያወቅኳቸው እንጂ ዝምድናም ሆነ የተለየ ቤተሰባዊ ቀረቤታ የለንም፡፡

እኚህን ውድ ኢትዮጵያዊ በዚህ ወሳኝ ወቅት ለሀገራቸው እንዲያገለግሉ እንዲያጯቸው በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

ከሰላምታ ጋር

Click to comment

More in አለም አቀፍ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top