ኢንተርኔት ሶሳይቲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኢንተርኔት ልማት ኮንፍረንስ አካሄደ
– በኢትዮጵያ አዲሱን የድርጅቱ ኢንተርኔት ቻፕተር አስመርቋል
ኢንተርኔት ሶሳይቲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የኢንተርኔት ልማት ኮንፈረንስ ከየካቲት 24-26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው። ይህ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ፕሮግራም ኢትዮጵያን ለተከፈተው የግል ቴሌኮም ዘርፍ አዲስ ዘመን ለማዘጋጀትና የኢንተርኔትን ሲስተም በማሳደግ በዚህም ዜጎችን እንዲሁም የተለያዩ ቢዝነሶችን ለመጥቀም ያለመ ነው።
በኢትዮጲያ የኢንተርኔት ስርፀት በአሁኑ ወቅት 18 ነጥብ 6 በመቶ ሲሆን ይህም ከመላው አፍሪካ የኢንተርኔት ስርፀት አማካይ ያነሰ ነው።

በአህጉሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እስመዘገቡ ካሉ ሀገሮች መካከል አንዷ መሆኗ፣ ስትራቴጂያዊ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ እነዲሁም ከ105 ሚሊዮን በላይ ከሆነው ህዝብ ቁጥሯ ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ከ30 አመት በታች የሚገኝ ወጣት ኃይል መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ስር ሰደድ የሆኑትን እንደ የወጣቶች ስራ አጥነት የመሳሰሉ ችግሮች ለማስወገድ የኢንተርኔትን ተደራሽነት ማስፋትና ሀገሪቷን ማገናኘት ቁልፍ የኢትዮጵያ መንግስት ስትራቴጂ መሆኑ ይታወቃል።
የኢንተርኔት ስርጸት በኢትዮጵያ በአመት በ45 በመቶ እድገት የሚስመዘግብ ቢሆንም ከሌሎች አቻ የአፍሪካ አገሮች ላይ ለመድረስ ግን አሁንም ይቀራታል። በኢትዮጵያ ከሚታዩ የኢንተርኔት ክፍተቶች ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙት በአብዛኛው የሀገሪቷ ገጠራማ ክፍሎች የኔትወርክ ግንኙነት አለመኖርና የ4ጂ አገልግሎት በዋና ከተማዋ ብቻ መገኘት ዋናዎቹ ናቸው። በተጨማሪም ኢትዮጰያውያን ሌሎች አለም ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግና የህዝቦቻቸውን ህይወት ለማሻሻል የሚጠቀሙባቸው ከኢንተርኔት ጋር ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶች እስካሁን ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም።
ኮንፈረንሱ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ ቢዝነሶችና ቴክኖሎጂስቶች እንዲሁም አቅሙ ላላቸው ስራ ፈጣሪዎች ስለ ኢንተርኔት ሞዴልና ቴክኖሎጂ ግንዛቤን በማስጨበጥ በዚህ አዲስ ከሞኖፖሊ የተላቀቀ ዘመን ጠንካራ የሆነ የኢንተርኔት ሲስተም መሰረት ለኢትዮጰያ ለመፍጠር ያለመ ነው።

የኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ አህጉር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ዳዊት በቀለ ሲናገሩ “ከአጠቃላይ ህዝቧ ውስጥ 20 በመቶ ብቻ በኢንተርኔት የተገናኘ በመሆኗ ኢትዮጲያ የህዝቦቿን ኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና የኢንተርኔትን ተደራሽነት ለማስፋፋት ትልቅ እድል አላት። በኢንተርኔት ላይ በመስራት አንጋፋ ከሆኑ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መካከል አንዱ በመሆናችን ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ለሀገራት የኢንተርኔት ግንኙነትን እንዲፈጥሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማገዝ ረገድ ረጅም አለምአቀፍ ታሪክና ልምድ አለን። በዚህ አጋጣሚ ይህንን ዝግጅት ስናዘጋጅ
በኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል ስለተደረገልን እገዛ ለማመስገን እወዳለሁ።
በቀጣይነትም በትልልቅ ከተሞችም ሆነ በገጠራማ ቦታዎች የኢንተርኔት ተደራሽነት በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማሳደግ በኩል የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ዝግጁ መሆናችንን እገልፃለሁ” ብለዋል።