Connect with us

አድዋ ከዋለበት ሰኞም ቅዳሜ ይኾናል

አድዋ ከዋለበት ሰኞም ቅዳሜ ይኾናል

ባህልና ታሪክ

አድዋ ከዋለበት ሰኞም ቅዳሜ ይኾናል

አድዋ ከዋለበት ሰኞም ቅዳሜ ይኾናል፤
በአንድ ቀን ድል ዘለዓለም ነጻ የወጣን ህዝቦች አድዋን እንዲህ አክብረነዋል፡፡
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ትናትን በድምቀት የተከበረውን የአድዋ ድል በዓል ሰኞ ቢኾንም ቅዳሜን መስሎ አከበርነው ሲል ድባቡን እንዲህ ይተርከዋል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

አዲስ አበባ የሚምርባት እንዲህ ስትሆን ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም፣ ዛሬ የአፍሪቃ ብቻ አይደለችም፤ ዛሬ የጥቁር ዛሬ የፍትሕ ዋና ከተማ መስላለች፡፡ ከቆመው ሐውልት ስር የቆምነው በተራሮቹ አናት አባቶቻችን ወድቀው ነው፡፡ አንድ ቀን ድል አድርገው ዘለዓለም ነጻ የሆንን ህዝቦች የአድዋ ድልን እንዲህ አከበርን፤

ያ ሰፊ አውድ ጠበበ፣ እንዲህ ያለውን ድል ለመዘከር ስፍራ ያንሳል፤ ምድር እንደ ሰፌድ ብትዘረጋም ስፍራ ያንሳል፡፡ ይሄ እኔ ትውልድ ልብ ውስጥ ተቀብሮ የኖረ ፍቅር ነው፡፡ የመሳሪያ ብዛት፣ የጉልበተኛ ህግ፣ በአባቶቹ ታሪክ የሚሸማቀቅ ሰው ደባ የማያጠፋው ምስጢር፣

አስቀድሞ አድዋን ልባችንን ከሚያህል ሰፌ ጎዳና ላይ አክበረነው ኖረናል፡፡ ደግሞስ ከልብ የሚደምቅ አደባባይ ወየት አለ? ደግሞስ ከልብ የሚገዝፍ ጎዳና በዓለም ላይ የት ተሰርቷል? ዛሬ ግን ከነ ልባችን ወጣን፤ ዛሬ ግን አፍሪቃን መሰልን፣ ዛሬ ያስከበሩንን አከበርን፤

ሰባተኛው የአድዋ ድል በዓል መታሰቢያ በተከበረበት ስፍራ ቆመናል፡፡ እንዲያ ባለ ድምቀትና ውበት ተገልጸናል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት አባቶቹን መምስል ይችልበታል፤ ማንም እንዳይመስል የተሰራበት ወጣት በአባቶቹ መልክ ጎዳናዎቹ ላይ ተገለጠ፤ ይህ አዲስ አበባ ነው፤ ይህ እቆምኩበት ጎዳና ላይ ቆሞ ታላላቆቹን በማሰብ ታላቅ ስራ የሰራው የኔ ትውልድ ልዩ ቀን ነው፡፡

ትውልድ ክብሩን ተቀባብሏል፡፡ ይህ ክብር ነው፡፡ አንድ ላይ ድል ላደረጉ አባቶች ክብር አንድ ላይ ውለናል፤ አጠገቤ ያለው ሰው ማንነት ለኔ ምንም ነው፤ አንድ ነገር ግን አውቃለሁ ለሱም ለእኔም ዋጋ ተከፍሎልናልና ሁለታችንም የአንድ አያት ልጆች ነን፤
አዲስ አበባ እንዲህ ስትሆን ማየት መታደል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አድዋ ሆኜ እንዲህ ያለውን ቀን እዚህ ህዝብ መካከል መሆን እመኝ ነበር፤ ተገኘሁ፤

ይሄ ትውልድ ፍም እሳት ነው፡፡ ረመጡም ይነዳል፤ በአባቶቹ ታሪክ የሚያፍር ደካማ በዚህ ዓይነት የድል በዓል ይፈወሳል፡፡ በጋራ ለተደረገንል በጋራ አንድ ሀገር አቁመን የምንከበርበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ ወደ አድዋ ድልድይ እየወርኩ ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ እንኳንም አዲስ አበባን ቆረቆሯት፤ እንዲህ ያለ ስም አስጠሪ ትውልድ ምን ኮረብታ ይበቃው ነበር? በፈጠሯት ከተማ ድንቅ ነገር የፈጠረ ትውልድ አባል በመኾኔ ደስ ብሎኛል።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top