Connect with us

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከጣልያኑ አቻቸው ሉዊጂ ዲ ማዮ ጋር ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከጣልያኑ አቻቸው ሉዊጂ ዲ ማዮ ጋር ተወያዩ
Photo: MFA

ዜና

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ከጣልያኑ አቻቸው ሉዊጂ ዲ ማዮ ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከጣልያኑ አቻቸው ሉዊጂ ዲ ማዮ ጋር ትናንት የካቲት 18 ቀን 2012 ዓም ተወያይተዋል። በውይይቱ ክቡር አቶ ገዱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ኢትዮጵያ ይበልጥ አጠናክራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል።

በዚሁ መሰረት በውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ደረጃ ውይይት ማካሄዱ ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን የሁለትዮሽና ዓለምዓቀፋዊ ትብብሮች በጋራ ለመገምገምና ትብብሮቹ የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት መንገድ ላይ ለመመካከር ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የጣሊያን ጉብኝት ወቅት እንዲሁም የጣሊያን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በአገራችን ባደረጓቸው ጉብኝቶች የኢትዮጵያና የጣልያንን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽና የአህጉራዊ የትብብር ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች መዘርጋታቸውን አስታውሰው ፤ አፈጻጸሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚንስትሩን ድጋፍ ጠይቀዋል። ሚንስትሩ በሁለቱ አገራት መካከል ስላለው የንግድ ልውውጥ እንዲሁም በአገራችን ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስረዳት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ አገራችን እንዲገባ የጣሊያን መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል የጣልያን የልማት ትብብር ተጠናከሮ እንዲቀጥል የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም ተፈጻሚ እንዲሆኑ የሚንስትር ዲ ማዮን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ጠይቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በአገራችን ለተጀመረው የሪፎርም ፕሮግራም ጣሊያን እስካሁን ላደረገችው ድጋፍ አመስግነዋል። በሃገር -በቀል ኤኮኖሚ ሪፎርም አማካይነት በተፈጠሩ መስኮችም የጣልያን ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቡዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ሁኔታና በድርድሩ ዙሪያ ኢትዮጵያ እያራመደች ያለው አቋም ለጣሊያን ወገን በዝርዝር የተብራራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ምክክር እየተደረገ መሆኑ ተገልጾላቸዋል።

የጣልያኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የለውጥ ሂደት በቅርብ እንደሚከታተሉና ሃገራቸውም ሙሉ ድጋፍዋን እንደምትሰጥ፤ በቅርቡ ለሚካሄደውም ምርጫ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማስፈን የምትጫወተውን ሚናም እንደሚያደንቁና ድጋፋቸውንም እንደሚሰጡ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በተፈጠሩ የኢኮኖሚ ዕድሎች መሳተፍ፣ ለወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞች እገዛ መስጠቱ ህገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረትም አይነተኛ መፍትሄ መሆኑንም አንስተው በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል ሲል መረጃውን ያደረሰን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነው።

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top