Connect with us

ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ – ስለ ግብረሰዶማዊነት ይናገራሉ

ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ - ስለ ግብረሰዶማዊነት ይናገራሉ
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ – ስለ ግብረሰዶማዊነት ይናገራሉ

– ትውልዱን ለማዳን የሚረዳ ማስታወቂያ ለመልቀቅ ተከልክለናል
– በአሜሪካ 10 ግዛቶች የግብረሰዶምን አስከፊነት አስተምሬአለሁ
– በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለምም በታሪካዊነቱ የሚጠቀስ ማህበር ነው

ሊቀ ትጉሃን ደረጀ ነጋሽ ዘ ወይንዬ ይባላሉ፡፡ “የማህበረ ወይንዬ አቡነ ተክለሃይማኖት” ሰብሳቢ፣ በጄቲቪ ኢትዮጵያ የ‹‹ወይንዬ›› ቴሌቪዥን ፕሮግራም መስራች፣ አዘጋጅና አቅራቢ ሲሆኑ የ“ወይንዬ የጉዞ ወኪል” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ፣ ‹‹ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረ ሰዶም እንታደግ›› ማህበር መስራችና ሰብሳቢም ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታትም ትውልድን ከአስከፊው ግብረ ሰዶም ድርጊት ለመታደግ በግላቸው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድርጊቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ አጠንክሮ ለመታገል ሕጋዊ ማህበር መመስረት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል – በዚህም መሰረት በጳጉሜ 2011 ዓ.ም ማህበሩ ተመስርቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በማህበሩ ዓላማና እቅድ፣ ግብረ ሰዶማዊነት በዓለምና በአገራችን ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ በግብረ ሰዶማዊነት ላይ ለመስራት ያነሳሳቸውን ምክንያትና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከመምህር ደረጀ ነጋሽ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ውድ አንባቢያን፤ በጉዳዩ ዙሪያ ጥሩ ግንዛቤ ያገኙበታል ብለን እናምናለን፡-

ለበርካታ ዓመታት በግልዎ ግብረ ሰዶማዊነትን ሲታገሉና ትውልዱን ከዚህ አስከፊ ተግባር ለመታደግ ሲጥሩ ቆይተዋል:: በዚህ ጉዳይ ላይ ለመስራት ያነሳሳዎት ምንድን ነው?

እኔ ቀደም ሲል የምሰራው የገዳማት ታሪክ ላይ ነበር፡፡ በገደማት ታሪክ ላይ ስሰራ ታዲያ ወንዶች “ተደፈርን” እያሉ በማልቀስ ይነግሩኝ ጀመር፡፡ እኔም ጉዳዩ እያሳሰበኝ መጣ፤ እናም ጥናት ለማድረግ ተነሳሁ፡፡ በአጋጣሚ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማራ ዮሴፍ የማነብርሃን የሚባል ሰው አግኝቼም አናገርኩት፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ግብረ ሰዶማዊነትን የማስፋፋት ዕቅድ እንዳለና ይህም በተደራጀ መልኩ ሊከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቆመኝ:: ይሄ ሰው ድንግል ሴት ብትቀርብለት እንኳን እንደማይነካ፤ ይልቁንም ከወንድ፣ ከውሻና ከሌሎች እንስሳት ጋር ግንኙነት እንደሚፈጽም ታሪኩን ነገረኝ፡፡ ይህን ከሰማሁና አንዳንድ ጽሑፎችን ካነበብኩ በኋላ ነገሩ አስከፊና ዘግናኝ በመሆኑ፣ በ2003 ዓ.ም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ የሀይማኖት አባቶች ለትውልዱ እንዲያስተምሩና ሕዝቡም ራሱን ከዚህ ጉዳይ እንዲጠብቅ ለማሳሰብ ‹‹እባብን በእንጭጩ›› የሚል ፕሮግራም አቀረብን፡፡
ይህንን ፕሮግራም ከሰራን በኋላ ባደረግነው ግምገማ ግን ሁኔታው ሊቆም ባለመቻሉና እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በ2005 ዓ.ም ከ7-32 ዓመት ድረስ በዚህ ሕይወት ውስጥ የቆዩ ሰዎችን ቃለ ምልልስ በማደረግ፣ በፓርቲያቸው ውስጥ በመግባት፣ ወንዱ ሂውማን ሄይር አድርጎ፣ ሊፕስቲክ ተቀብቶ፣ ቀሚስ ለብሶና ተኳኩሎ የሚያደርገውን ጭፈራና አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርፀንና በሲዲ አሳትመን ‹‹ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም›› በሚል ርዕስ ለሕዝብ ዕይታ ለቀቅነው፡፡

ምንም እንኳ አስከፊነቱን፣ የደረሰባቸውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ፣ የጤና እክልና መገለል በሲዲው በማሳየት ልንከላከል ብንጥርም ድርጊቱ ግን ሊቆም አልቻለም፡፡ እኔም ጥናቴን አጠናክሬ ቀጠልኩበት፡፡ ሰው ከመፍራትና ከመደንገጥ ይልቅ እየባሰበት የመጣው ለምንድን ነው? የሚለውን ለማወቅ ጥናቴን ወደ ‹‹ማህበረ ወይንዬ ዘ አቡነ ተክለሃይማኖት›› አመጣሁትና ማህበሩ ያግዘኝ ጀመር፡፡ በጥናቱ ያገኘሁት ውጤት፤ ችግሩ ውስጥ ለውስጥ እየተስፋፋና ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እያመጣ መሆኑን የሚጠቁም ነበር፡፡ በመሆኑም አገር አቀፍ እውቅናና ሕጋዊ ሰውነት ያለው ማህበር ተቋቁሞ፣ በጥንካሬ ካልተሰራ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚደረገው ሩጫ የትም እንደማያደርስ መገንዘብ ቻልን፡፡ “ወይንዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማህበር” ሀይማኖታዊ ተቋም ስለሆነ ሁሉንም አይወክልም፤ አገር አቀፍና ከሀይማኖት ውጭ ያለ ማህበር ከሆነ ግን ሙስሊሙን፣ ክርስቲያኑን፣ ፕሮቴስታንቱን እንዲሁም፣ ሀይማኖት የሌለውንም ጭምር ማሳተፍ ስለሚችል፣ አገራዊ ማህበር ለማቋቋም ወሰንን፡፡ ከዚያም ይህንን የመፍትሄ ሀሳብና የማህበሩን 10 ዓላማዎች ይዘን፣ ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስብሰባ ማዕከል፣ 74 የሚዲያ ተቋማት በተገኙበት ማህበሩን መሰረትን:: በምስረታው ላይ ባቀረብነው ጥናትም፤ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ከሕግ፣ ከሀይማኖት፣ ከስነ ልቦና፣ ከማህበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮች አንፃር ሊያስከትል የሚችለውንና እያስከተለ ያለውን መጠነ ሰፊ ችግር ለሕዝቡ ለማሳየት ሞክረናል፡፡

ከዚህ በፊት የተቋቋሙ በግብረ ሰዶም አስከፊነት ላይ የሚሰሩ ማህበራት የሉም ማለት ነው?
የሉም! ይሄ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለምም በታሪካዊነቱ የሚጠቀስ ማህበር ነው፡፡ በአንፃሩ ‹‹ILGA›› (International Lesbian and Gay Association) ከተመሰረተ 40 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ ማህበር የግብረ ሰዶማዊያንን መብት የሚጠብቅ፣ የሚሟገት ግብረ ሰዶማዊነት መብታቸው እንደሆነ የሚቆረቆር ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ በዓለም ላይ 1 ሺህ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ አስቢው… የዓለም አገራት እንኳ 1 ሺህ አይሞሉም፤ የእነሱ ማህበር ግን 1 ሺህ ቅርንጫፍ ያሉት ቢሊዬነር ማህበር ነው፡፡ ነገር ግን እነሱን ከዚህ አስከፊ ድርጊት የሚያድንና የሚጠብቅ አንድም ማህበር አልነበረም፡፡ ይሄው እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ መስርተናል፡፡ ማህበሩ በደሃ አገር ባልተጠበቀ ሁኔታ በመመስረቱ፣ ብዙ ትኩረትና የሚዲያ ሽፋንም በተለይ በውጭው ዓለም አግኝቷል፡፡ ከዚያም ሥራ አስፈጻሚና አመራሮችን በመምረጥ፣ ሁሉን አሟልተን ባለፈው ህዳር ወር ሕጋዊ ሰውነት አግኝተን መንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡

በአሁን ወቅት ግብረ ሰዶማዊነት በሀገራችን ያለበት ሁኔታ ከሀይማኖት፣ ባህል፣ ሕግና ሥነ ልቦና አንፃር እንዴት ይተነተናል?
ከሕግ አኳያ ሲታይ፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 629 ወንጀል መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በነገራችን ላይ ግብረ ሰዶም ከሀጢያትነቱ ክብደት አንፃር ስምም እንኳን አልተሰጠውም፡፡ ለምሳሌ የሚሰርቅ ሰው ‹‹ሌባ››፣ የሚሰክር ሰው ‹‹ሰካራም››፣ የሚዋሽ ሰው ‹‹ዋሾ (ቀጣፊ)›› ይባላል፡፡ ግብረ ሰዶም ግን ስም አልወጣለትም፡፡ ‹‹ግብረ ሰዶም›› ማለት ‹‹የሰዶም ስራ›› ማለት ነው። ስያሜ ያጣ ከባድና አስፀያፊ ሀጢያት ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እግዚአብሄርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሄርም ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ሰጣቸው›› ሲል የተናገረው፡፡ ከጤና አኳያ ሲታይ ደግሞ፤ ለኤችአይቪ ያጋልጣል፣ የፊንጢጣ ካንሰር ያስከትላል፣ የፊንጢጣ መንቦርቀቅ ይፈጥራል፣ ሄፓታይስ A እና B ያመጣል፤ የጉሮሮ ቂጥኝ ያስከትላል፡፡ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
የጉሮሮ ቂጥኝ ምንድን ነው? ሰምቼ አላውቅም…

አሁን ሰው ያላወቀው ይሄንን ነው፡፡ ብዙ ሰው ሰምቶም አያውቅም፡፡
በሳይንስና በሕክምና የተረጋገጠ ነገር ነው?
በትክክል በሕክምና የተረጋገጠ ነው፡። በአፍ የሚፈፀም ግንኙነት (ኦራል ሴክስ) ነው የጉሮሮ ቂጥኝን የሚያመጣው፡፡ በዚህ በሽታ ብዙ ግብረ ሰዶማዊያን አስከፊ የጤና እክል ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ የልብ ድካም፣ ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥና ራስን ማጥፋት ደረጃ ላይ ሁሉ ያደርሳል። በተለይ አሁን አሁን የሚፈፅሙት ‹‹Danger Sex›› የሚባለው… ለተስፋ መቁረጥ እየዳረጋቸው ነው፡፡
እስኪ “ዴንጀር ሴክስ” (አደገኛ ዝሙት) ስለሚባለው ያብራሩልኝ…?

አደገኛ ዝሙት የሚባለው ብዙ ዓይነት ነው፡፡ አንዱ በሽንት መታጠብ (‹‹Golden Shower››) ይሉታል፣ አሺሽ ይወስዱና ሲሰክሩ ይህን አደገኛ ዝሙት ይፈጽማሉ:: ምንድን ነው የሚያደርጉት? አንድን ወንድ ብዙ ሆነው በመድፈር ፊንጢጣውን መበታተን ነው፡፡ ሌላው አንድን ወንድ ለአምስትና ለአስር ሆነው በአፉ ሴክስ በማድረግ ሁሉም የዘር ፈሳሻቸውን ያጠጡታል፡፡ ሌላው አይነ ምድርን መቀባት (Cream) – ክሬም የሚሉት ሰገራን እንደ ሎሽን ሰውነታቸውን መቀባት ሲሆን አይስክሬም የሚሉት ደግሞ መላስና መብላቱን ነው፡፡ በዛ ጡዘት ውስጥ በሽንት ሲታጠቡ፣ አይነ ምድር ሲቀቡ፣ ሲልሱና ሲበሉ ትልቅ ደስታ ያገኙ ይመስላቸዋል፤ ወደ አቅላቸው ሲመለሱ ግን ከቁጥጥር ውጭ ይሆንባቸውና ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ ይሄ አሁን ወደ አገራችን እየመጣና እየተስፋፋ ያለ አደገኛ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የስልክ ዝሙት (Phone Sex) ራስን በራስ ማርካት፣ አርቲፊሻል የወንድ ብልት መጠቀምና በርካታ ከጤናማና ከተፈጥሮ ያፈነገጡ ድርጊቶች ተበራክተዋል፡፡ እነዚህ ግን በሕግ ወንጀል ተብለው ስላልተመዘገቡ ትኩረት አላገኙም፡፡

ከማህበራችን አላማ አንዱ፤ በዚህ ዙሪያ ያለው ሕግ እንዲሻሻል ማድረግ ነው፡፡ በወንጀልነት የተደነገገው ወንድ ለወንድና ሴት ለሴት ግንኙነትን ብቻ ነው፡፡ አንድ ጊዜ እኔ ጋ የወንጀል ክስ ደርሶኝ ነበር፡፡ ‹‹ልጁ ልጅቷን በፊንጢጣዋ ደፈራት›› የሚል ክስ ነው፡፡ አቃቤ ሕጉ “ደፈራት” ሲል፤ እኔ ደግሞ “ደፈራትም ግብረ ሰዶም ፈፀመባትም” አልኩኝ፡፡ እኔ ያልኩት ግን በሕግ ላይ አልተቀመጠም:: ለምሳሌ ትራንስ ጀንደር (የፆታ ቅየራ) በግብረ ሰዶምነት በሕጉ አልተካተተም፡፡ ራስን በራስ ማርካትና አርቲፊሻል የወንድ ብልትን መጠቀም በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች በስፋት እንደሚፈፀም ጥናቶች ይጠቁማሉ:: ግን አሁንም በግብረ ሰዶም ሕጉ አልተካተተም፡፡ አሜሪካውያን እንኳን “ትራንስ ጀንደር”ን፣ አርቴፊሻል የወንድ ብልት መጠቀምን፣ ከሁለቱም ፆታዎች ጋር ግንኙነት የሚፈጽሙትን (ባይሴክሽዋል) ግብረ ሰዶም ብለው በሕግ ሲያስቀምጡ፤ በኢትዮጵያ ሕግ እነዚህ አልተካተቱም፡፡ ስለዚህ ወንጀሉ እየተስፋፋ፣ ሰውም ይበልጥ ተጋላጭነቱ እየጨመረ በእጅጉ እየተጎዳ ነው ያለው፡፡

በአገራችን ግብረ ሰዶማዊነት በሕግም ወንጀል፣ በባህልም አስፀያፊ፣ በእምነት አኳያም ቢሆን ሀጢያት ስለሆነ በድብቅ ነው የሚፈፀመው፡፡ እናንተ ጥናቱን የምትሰሩት እንዴት ነው? መረጃዎችንስ ከየት ነው የምታገኙት?

አንደኛ ምንጮቻችን በዚህ ሕይወት ውስጥ ሆነው፣ ነገር ግን ከዚህ ሕይወት መውጫ መንገድ የሚፈልጉ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛ እንደምንም ታግለው ከዚህ ሕይወት የወጡ ሰዎች፤ በ“እኛ ይብቃ” ብለው ያሳለፉትን ችግርና ከመከራ ለመውጣት ያደረጉትን ትንቅንቅ ይነግሩናል፡፡ ሶስተኛ ምንጮቻችን ሴተኛ አዳሪዎች ናቸው፡፡ ሴተኛ አዳሪዎችና ግብረ ሰዶማዊያን በፍፁም አይግባቡም፡፡

በምን ምክንያት አይግባቡም? ምንስ ያገናኛቸዋል?
የማያግባባቸውና የሚያገናኛቸው ምን መሰለሽ… ሴቷም ወንድ ለማደን፣ ወንዱም ወንድ ለማደን ሲወጡ ሜዳው ላይ ይገናኛሉ፡፡ አስፋልት ላይ ያለች ሴተኛ አዳሪ፣ ወንዱን ይዛ ከሄደች ‹‹ይቺ አይነ ጥላ ወሰደችው›› ብሎ ወንዱ ይናደዳል፡፡ ሴተኛ አዳሪዋም ማን ግብረ ሰዶም እንደሆነ፣ ማን ሌዝቢያን እንደሆነ በደንብ ለይታ ታውቃለች፡፡ ስለዚህ በደንብ ምስጢር ይነግሩናል፡፡ ገንዘብ በመክፈልና በማግባባት መረጃ እንሰበስባለን፡፡ እኔ እንደውም ጥናቱን ሳጠና ገንዘብ ጨርሼ ልብሴንና የአንገቴን ወርቅ እስከ መሸጥ ደርሼአለሁ፡፡ ልብሴን አውልቄ የሰጠሁበት ጊዜም አለ፡። ከዚያ ውጭ በቀናነት ወገኖቻቸው ከዚህ ተግባር እንዲወጡ ሲሉ መረጃ የሚሰጡንም አሉ፡፡ በራሳችንም መንገድ በምናያቸው እንቅስቃሴዎችና በድርጊቶቻቸው በመለየት እናጠናቸዋለን፡፡ እኛም እነሱን በመምሰል፣ ሰዎችም እነሱን እንዲመስሉ በማድረግ ወደ እነሱ በመላክ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ጥናታችንን እንሰራለን፡፡
መጥፎ ድርጊት በአደባባይ ሲወጣና በሚዲያ ተደጋግሞ ሲነገር የበለጠ እየተዋወቀና እየተባባሰ ይመጣል ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃርም ስለ ግብረሰዶም መወራቱን አይደግፉትም:: እርስዎ ምን ይላሉ?

ምንም ነገር ቢሆን መታወቅና ሕብረተሰቡ ተገንዝቦ ራሱን መጠበቅ አለበት፡፡ ይሄ ብዙ ሲነገር ችግሩን ያባብሰዋል የሚለው ከእንግሊዝ የተቀዳ ነው። እንግሊዞች በፊት አንድ ግብረ ሰዶማዊ ሲገኝ ይገድሉ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ውስጥ ውስጡን እንደ ጋንግሪን ተስፋፍቶ ትላልቅ ሰዎችን ማለትም ባለሥልጣናትን፣ ታዋቂዎችን ሀብታሞችንና ትላልቅ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ከያዙ በኋላ ሕጋዊ አደረጉትና ዛሬ ዓለም ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ እዚህም አገር ጉዳዩን መዘገብ ችግሩን ማስፋፋት ነው ብለው፣ በኤዲቶሪያል ቦርዳቸው ውሳኔ አሳልፈው፣ የማይዘግቡ ሚዲያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ስለ ኤችአይቪ መዘገብ፣ ኤችአይቪን ማስፋፋት ነው እንዴ? ግንዛቤን መፍጠርና ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ መንገር ስንቱን ታድጓል እኮ! ዝም ብንል ምን ሊመጣብን ይችል እንደነበር ስናስበው በጣም ከባድ ነው፡፡

አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ባወቀ ቁጥር ራሱን ከዚያ ነገር ይጠብቃል እንጂ አይኑ እያየ ገደል አይገባም፡፡ ሁለተኛ ይህን አስከፊ ድርጊት በገለጽንና ወንጀልነቱን ባሳየን ቁጥር፣ ሕዝቡ በዚህ ወንጀል ውስጥ ገብተው ያገኛቸውን ሰዎች ወደ ሕግ ያቀርባል፤ ወንጀልን ይከላከላል፡፡ ስለዚህ በጉዳዩ ዙሪያ መናገር ችግሩን ማስፋፋት ነው የሚባለው ፍፁም የተሳሳተና አገርንም ሕዝብንም ባህልንም የሚጎዳ በመሆኑ ዝም መፍትሔ አይደለም፡፡ እዚህ አገር ትውልዱን የሚጎዳ የመጠጥ ማስታወቂያ እየተለቀቀ፣ ትውልድን ለማዳን የሚረዳ ማስታወቂያ ተክልክለናል፤ ይሄ በራሱ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡

የግብረ ሰዶማዊያን ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ እየተስፋፋ ነው ብለዋል፡፡ በአሃዝ አስደግፈው ሊነግሩን ይችላሉ?
መናገር ይቻላል፡፡ ከ8 ዓመት በፊት 13 ሺህ ነበሩ፣ በሁለት ዓመቱ 30 ሺህ ደረሱ:: አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግብረ ሰዶማዊያን ቁጥር 100 ሺህ ደርሷል፡፡ ይሄ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ጉዳዩን በመደበቃችንና ሕዝቡን በስፋት ባለማስተማራችን የመጣ ውጤት ነው። በተለይ የአይካሳ ስብሰባ አዲስ አበባ ከተካሄደ በኋላ ግብረ ሰዶማዊያን በእጅጉ ተበራክተዋል፡፡
የዚህ ቁጥር ምንጭ ምንድን ነው?

በ2003 ዓ.ም ከተበተኑ መጠይቆች፣ በዚህ ህይወት ውስጥ ቆይተው ከወጡት፣ አሁንም በዚህ ህይወት ውስጥ ከሚገኙት፣ በውጭም በአገር ውስጥም ድርጊቱን ከሚከታተሉና በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነው ጥናትና ምርምር ከሚሰሩ እንዲሁም ከራሴ ተከታታይ ጥናት በመነሳት የተገኘ ዳታ ነው፡፡
በአይካሳው ስብሰባ ጊዜ የሀይማኖት አባቶች ድርጊቱን ለማውገዝ ጋዜጠኞች ከተሰበሰቡ በኋላ ውግዘቱ መከልከሉን አስታውሳለሁ…

ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ያን ጊዜ ማውገዙ የቀረው በሀይማኖት አባቶች ድክመት ነው ባይ ነኝ፡፡ ሀቅ እስከያዙና ማህበረሰቡን የማዳን ሃላፊነት እስካለባቸው ድረስ መንግሥትን ፈርተው ከማውገዝ መገታት አልነበረባቸውም፡፡ ስብሰባው ተካሂዷል:: በስብሰባው ላይ ግብረ ሰዶማዊያንም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ብዙ መርዝ የተረጨበት ስብሰባም ነበር፡፡

ባለፈው ጊዜ “ቶቶ ቱርስ” የተባለው ድርጅት ግብረ ሰዶማዊያንን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በተነሳበት ጊዜ፤ በሕዝቡ ተቃውሞና ቁጣ ጉዞው ተሰርዟል፡፡ በዚህ ላይ የእናንተስ ሚና ምን ነበር?

እኔ አስጎብኚ ድርጅት አለኝ፡፡ ኢየሩሳሌም ሰዎችን ስወስድ ስንት ነው የማስከፍለው? የት ነው የማሳርፈው? የሚለውን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ “ቶቶ ቱርስ” 7 ሺ 900 ዶላር ሲመድብ ከማን ጋር ተነጋግሮ ነው? ይህ ይታወቃል፡፡ ዞሮ ዞሮ እኛም በከፍተኛ ደረጃ ተቃውመናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውም ተፅዕኖ ፈጥሮ ሕዝቡ ነው ጉዞውን ያሰረዘው። በወቅቱ በመንግሥት ሚዲያዎች በጣም ነበር ያፈርኩት፤ አንድም ትንፍሸ ሳይሉ በዝምታ ነው ያለፉት፡፡ ሕዝቡ ግን በፌስቡክ ተረባረበ፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም አወገዘ፣ የሰልስቱ እምነት ተቋማት ተቃወሙ፤ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገን ጉዞው ተሰረዘ፡፡ እኔም ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ በመሄድ ጉዳዩን ለአባቶች አስረድቼ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያወግዝ እስከ ማድረግ ደርሼአለሁ፡፡ በጣም የሚገርምሽ አትላንታ ላይ “ከሞታችን በፊት ላሊበላን እንጎብኝ፤ ማንም የሚያስቀረን የለም” የሚል ዛቻ የመሰለ ማስታወቂያ ተለቅቋል፡፡ ይሄ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡

እኛ ሀገር ግብረሰዶማዊያን ህዝቡን ይፈራሉ፡፡ በሌላው ዓለም ሕዝቡ ግብረሰዶማውያንን ይፈራል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
ትክክል ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ካላት 328 ሚ. ሕዝብ ግብረ ሰዶማዊያኑ 4.5 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው 95.5 በመቶው ግብረ ሰዶምን አይቀበልም፤ ነገር ግን እነሱን መቃወም አይችልም፤ ፊቱን እነሱ ላይ ማጥቆር አይችልም፡፡ ጥቃት ተፈፀመብኝ፣ አገለለኝ ተፀየፈኝ ብለው ክስ ይመሰርታሉ:: ለምሳሌ አንድ ኬክ ቤት ገብተው፣ ኬክ ካዘዙ በኋላ “አርማችን ኬኩ ላይ ይሰራልን” ሲሉ ኬክ ሰሪው “ያንን አላደርግም” ቢል ይከሰሳል፡፡ “መብቴን ከለከለኝ፤ አቢዩዝ አደረገኝ” ይባላል፡፡ ስለዚህ 95.5 በመቶው ሕዝብ እነሱን ይፈራቸዋል፡፡ አገራችንም ላይ የቀስተ ደመናው ቀለም (የእነሱ መለያ) በጃንጥላ፣ በቲ-ሸርት፣ በጌጣ ጌጥ መልክ እየተስፋፋ ነው ያለው፡፡ ይሄንን ሁሉ ግን መከላከል አለብን፡፡ አሁን አሁን በኢትዮጵያ የሕጻናት መብት ከአሜሪካ የውሻ መብት ያነሰ እየሆነ መጥቷል፡፡ እስኪ ልጠይቅሽ… ስንት ወንድ ሕጻናት ሲደፈሩ የትኛው ባለሥልጣን፣ የትኛው የተቃዋሚ መሪ ነው ስለ ሕጻናት መደፈር ወጥቶ የተናገረ? ማን ነው ስለ መብታቸው የተቆረቆረ? ማንስ ነው ከሕግም ከባህልም ከእምነትም አንጻር ጽዩፍ ነው ብሎ ያወገዘ? ለዚህ ነው የሕጻናቱ መብት ከአሜሪካ የውሻ መብት ያነሰ ነው የምለው፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ የሚያንገበግበኝ:: መንግሥታችንም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡

ለምሳሌ ቭላድሚር ፑቲን፣ ዶናልድ ትራምፕ ይሄንን ነገር አይቀበሉትም፤ አለመቀበላቸውን በግልጽ ያሳውቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን በዚህ ላይ አቋሙን አልገለፀም፡፡

በእናንተ አቅም ብቻ ይሄን ድርጊት እንከላከላለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
አንደኛ የተለያዩ ሰዎች ከዚያ ሕይወት እየወጡ ነው ያሉት፡፡ ሁለተኛ ማህበሩ ከተመሰረተ ገና ጥቂት ወራት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት፡፡ እስከ ዛሬ እኛ በግለሰብ ደረጃ ስንንቀሳቀስ ነበር እንጂ አቅም አልነበረንም፡፡ አሁን ግን ሕጋዊ ሰውነት ስላገኘን፣ የተቀናጀ ሥራ በመስራት ለውጥ እናመጣለን፤ አቅምም ይኖረናል ብለን እናስባለን፡፡

በቅርቡ ለዚሁ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ነበር፡፡ እዚያ ምን ሰርተው ተመለሱ?
አሜሪካ የሄድኩት የማህበሩን አላማና ግቦች ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በአስር ግዛቶች ተዘዋውሬም የግብረ ሰዶምን አስከፊነት አስተምሬያለሁ፡፡ ይታይሽ ‹‹ቤከር›› የተባለው የእነሱ ሰው በ1978 ዓ.ም ቀስተ ደመና አርማቸውን በመሰረተበት በራሳቸው አገር፣ ሳንፍራንሲስኮ ተገኝቼ ነው አስከፊነቱን ያስተማርኩት፡፡ ይሄ የእግዚአብሔር እገዛ ነው፡፡ እዚያ እንግዲህ እንደነ ዶ/ር ዕልልታ አይነት ጠንካራ ኢትዮጵያዊያንን በማግኘትና ዳላስና ሌሎች ግዛቶችም ላይ ንዑስ ማዕከላትን ለማቋቋም፣ ማህበሩ ድጋፍ የሚያገኝበትንና የሚጠናከርበትን አሰራር በመዘርጋት በኩል አመርቂ ሥራ ሰርቼ ነው የተመለስኩት፡፡

በሚያስተምሩበት ጊዜ ችግር አልገጠመዎትም?
የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ምንም አይነት ችግር አልገጠመኝም፡፡ እዚያ ከጳጳሱ ጀምሮ ሕዝቡ ያደረገልኝ አቀባበል ልብ የሚነካ ነው:: በጣም ጥሩ ቆይታ ነው የነበረኝ፡፡ እዚያ ስለዚህ አስከፊ ድርጊት ለመናገር ፈርተው የቆዩት ነገር ተሰበረና ለካ መናገር ይቻላል የሚለው መንፈስ ሁሉ ተፈጥሯል፡፡

ማህበራችን በርካታ አላማዎች አሉት:: ለምሳሌ በዚህ አስከፊ ሕይወት ውስጥ የሚገኙና ለመውጣት ፈቃደኛ የሆኑትን የስነ ልቦና የማገገሚያ ማዕከል በማስገባት፣ የገንዘብና መሰል ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ ቀደመ ኖርማል ሕይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ ከዚያ ሕይወት መውጣት ያቃታቸው መገለል እንዳይደርስባቸው ፍቅርና ምክር መስጠትና ቀስ በቀስ እንዲወጡ ማድረግ፣ ወጣቱ ወደዚህ አስከፊ ድርጊት እንዳይገባ ማስተማር፣ በግድ ተደፍረው ጥቃት ለደረሰባቸው የሕግ አገልግሎት፣ የስነ ልቦናና የሕክምና ድጋፍ መስጠት ከማህበራችን ዋና ዋና አላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ማህበሩ ምን ያህል አባላትን ይዞ ነው የተመሰረተው?
በ10 ሰው ማህበር መመስረት ይቻላል:: እኛ ግን 32 የተለያየ አቅምና እውቀት ያላቸውን አባላት ይዘን ነው የመሰረትነው:: አባላት ስንቀበልም ዝም ብለን አይደለም:: የፖለቲካ፣ የሀይማኖት፣ የዘርና መሰል አጀንዳዎችን የያዘ አንቀበልም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ስሜት በዚህ አስከፊ ሕይወት ውስጥ ያሉ ወገኖቹን በቅንነት ለመርዳት፣ ሕዝቡን ከግብረ ሰዶም ለመታደግ ብቻ የሚሰራን ነው የምንቀበለው:: የነደፍነውን የ100 ሺህ ዶላር ፕሮጀክትና አጠቃላይ የማህበሩን እንቅስቃሴዎች ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተናል፡፡ ሕጋዊ ሰውነት ማግኘታችንም የበለጠ አቅም ስለሚሆነን፣ ለውጥ እናመጣለን የሚል ከፍተኛ እምነት አለን፡፡

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top