Connect with us

መቼም ወግ ነውና ህወሓቶችን እንኳን አደረሳችሁ ልበል?!

መቼም ወግ ነውና ህወሓቶችን እንኳን አደረሳችሁ ልበል?!
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

መቼም ወግ ነውና ህወሓቶችን እንኳን አደረሳችሁ ልበል?!

መቼም ወግ ነውና ህወሓቶችን እንኳን አደረሳችሁ ልበል?!
#እንኳን_አደረሳችሁ!!

ዛሬ የካቲት 11 ቀን ነው። የዛሬ 45 ዓመት ጥቂት የከፋቸው ታጋዮች “ነገ እልፍ እንሆናለን” ብለው ጫካ ገብተው የብረት ትግል ጀመሩ። የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ትግል እነሆ ትግራይን ነፃ ከማውጣት ህልም በዘለለ ኢትዮጵያን ከደርግ ወታደራዊ መንግሥት ነፃ ወደማውጣት ተሸጋግሮ በ17 ዓመት የታዳጊ ዕድሜው የሚኒልክ ቤተመንግሥት አልጋ ወራሽ ለመሆን በቃ።

ትግሉ እጅግ መራራ፣ ብዙ መሰዋዕትነትን የጠየቀ ነበር። ትልቅ ህልም የነበራቸው ወጣት ጀግኖች ለእኩልነት፣ ለነፃነት፣ለዴሞክራሲ፣ ለሠላም፣ለኘረስ ነፃነት፣ ለህግ የበላይነት፣ መከበር…ሲሉ መተኪያ የሌለውን ውድ ህይወታቸውን ገብረዋል። እናም የካቲት 11 እነዚህ ጀግኖች የሚከበሩበት፣ የሚዘከሩበት መሆኑ ብቻውን ያኮራል። የእነዚህን ሰማዕታት ተጋድሎ በዘነጉ፣ አደራቸውን ቀርጠፈው በበሉ ጥቂት ከሀዲዎች አጋፋሪነት መከበሩ ደግሞ ያማል፤ ልብን ያደማል።

አዎ!.. እነዚያ ብርቱ ጀግኖች የታገሉት ለሠላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነት…ነበር። ይህን ራዕይ እና አደራ ለማስፈፀም ዕድሉን ያገኙት የህወሓት ጥቂት የማይባሉ ጎምቱዎች ግን ይህን ክቡር የደም መሰዋዕትነት የተከፈለበት ዓላማ የዘነጉት ውለው ሳያድሩ ነበር። ብዙዎች በድል ማግስት በከተማ ብልጭልጭ ህይወት ተጠለፉ። እምቢ ለነፃነቴ ብለው ብረት ጨብጠው የኖሩ እጆች የከተማ ሴት ወጣቶች ለስላሳ ገላ ላይ ሟሙ። አንዳንድ ተጠላፊዎች ታጋይ ሚስቶቻቸውን ለመፍታት ጊዜ አልፈጁም።

ትንሽ ይሉኝታ ያጠቃቸውም ደግሞ በታጋይዋ ሚስታቸው ላይ ከተሜዎችን ወሸሙ። ከህወሓት ጎምቱዎች አንዳንዶቹ ለታይታ ያህል የሴቶች ሚኒስትር እንዲቋቋም ፈቅደናል እያሉ በተግባር ግን የሴቶችን ክብርና ጥቅም ደፍጣጭ ሆነው ታዩ። አንዳንዶች ጠዋት ማታ በትላልቅ መሸታ ቤቶች አልኮል ውስጥ መደበቅ መደበኛ ሥራቸው አደረጉ። ውስኪና ጮማ እንዲሁም ሴሰኝነት እንደገናም መስመር የሳተ ቅብጠት፤ የት ይደርሳሉ የተባሉ የትላንት የነፃነት ታጋዮችን መናኛ አደረጋቸው።

ችግሩ፤ የነፃነት ታጋዮቹ – ነፃነት ጨፍላቂዎች ወደመሆን ሲሸጋገሩ ከልካይ፤ ተቆጪ የሌላቸው ሆነው መቆየታቸው ነው። ይባስኑ “እኛ ታግለን ባመጣነው ነፃነት…” የሚል መታበይ ውስጥ የገቡ የህወሓት ሹማምንቶች እጅግ ብዙ ነበሩ። በዚህም ምክንያት በአገር ሥርዓት አልበኝነት ሰፈነ። ዜጎች በገዛ አገራቸው ያመኑበትን ሀሳብ ማራመድ፣ ቀና ብለው መሄድ ብርቅ ሆነባቸው። የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ… ጥያቄ ያነሱ ወገኖች ማረፊያቸው የቀድሞ ማእከላዊና ቂሊንጦ ሆነ። የግፍ ፅዋው ሞልቶም ፈሰሰ።

በህወሓት ውስጥ ቀስ በቀስ ያቆጠቆጠው ዘረኛና ጠባብ የቡድንተኝነት ስሜት እያደገ መጥቶ ሰዎች በብሄር፣ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጎጥ ወደሟቧደን ተሸጋገረ። በህወሓት ውስጥ “እገሌ አድዋ ነው። እገሌ ሽሬ ነው…” የሚሉ የመንደርተኝነት፣የጎጠኝነት አዝማሚያዎች ገዥ ሆነው ብቅ አሉ። እነሆ ህወሓቶች ላለፉት 28 አመታት በዘሩት ጠባብ ብሄርተኝነት ተኮትኩቶ ያደገ አዲስ ትውልድ ለመፈጠርም በቃ። በመጨረሻም ብዙዎች የሞቱለት፣ የደሙበት የተከበረ ትግልና መሰዋዕትነት በጥቂት ሌቦች፣ ሴሰኞች፣ ጠባብ ብሄርተኞች፣ ቡድንተኞች… ተጠልፎ ውሀ በልቶት ቀረ።

እነሆ ህወሓቶች ትላንት የቀበሩት የዘረኝነት፣የአክራሪ ብሔርተኝነት ፈንጅ ዛሬ ጊዜውን ጠብቆ በየክልሉ እየፈነዳ ነው። እነሱም አንድ ቀን እሳቱ ሊበላቸው እንደሚችል ከማሰብ ይልቅ “እኛ ጋር ሠላም ነው” የሚል ነጠላ ዜማ እየዘመሩ የዳር ዳሩን እሳት ከበው መሞቁን ቀጥለዋል።

መቼም ወግ ነውና ህወሓቶችን በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ ልበል። ለእነዚያ ብርቱ፣ ትንታግ ታጋዮች አክብሮቴን ልግለፅ። ከትግሉ መለስ ግን ያለው ሁሉ “ድንጋይ ውሀ ውስጥ 40 ዓመት በመኖሩ ዋና አልተማረም” የሚለውን ብሂል ከማስታወስ የዘለለ ፋይዳ የለውም።( ጫሊ በላይነህ)

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top