Connect with us

ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ “ጠባቂዎቼ ከእኔ ጋር ይቆያሉ” አሉ

ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ "ጠባቂዎቼ ከእኔ ጋር ይቆያሉ" አሉ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ “ጠባቂዎቼ ከእኔ ጋር ይቆያሉ” አሉ

በመንግሥት ተመድበው ለረጅም ጊዜ ለጃዋር ሞሐመድ ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት በእራሳቸው ፈቃድ ከእርሱ ጋር ለመቆየት መወሰናቸው ተነገረ።

በቅርቡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) በመቀላቀል ከመብት ተሟጋችነት ወደ ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የገባው ጃዋር ሞሐመድ ለቢቢሲ እንደተናገረው መንግሥት የመደባቸውን ጠባቂዎቹን እንደሚያነሳ እንዳሳወቀውና ይህንንም ተከትሎ ጠባቂዎቹ ከመደበኛ ሥራቸው ይልቅ “እኔ ጋር መቅረትን መርጠዋል” ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያ የፌደራል ፖሊስን ጠቅሶ ለጃዋር ሞሐመድ ተመድበው የነበሩት ጥበቃዎች እንዲነሱ መደረጉን መዘገቡን ተከትሎ ጃዋር በፌስቡክ ገጹ ላይ “ሰላም ነው። ከፌደራል ፖሊስ ጋር ተወያይተን ከስምምነት ላይ ደርሰናል። አታስቡ” ሲል ለደጋፊዎቹ መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

ጃዋር ለቢቢሲ እንደተናገረው የጥበቃዎቹን መነሳት በተመለከተ ከፌደራል ፖሊስ ኮማንደር ጋር መነጋገሩንና አባላቱ ለስልጠና እንደሚፈለጉና ወደ ተቋማቸው እንዲመለሱ መጠየቁን አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ የእሱ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ጥበቃ የተመደበላቸው ሰዎች ጠባቂዎችን ማንሳት እንደጀመሩና የእሱንም ጥበቃዎች እንደሚያነሱ እንደነገሩት ገልጿል።

ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ለረጅም ጊዜ አብረውት ከቆዩት ጠባቂዎቹ ጋር ስለዚሁ ጉዳይ ተነጋግሮ እንደነበር የሚናገረው ጃዋር “አነሱም ወደ ፌደራል ፖሊስ መመለስ እንደማይፈልጉና ከእኔ ጋር መቆየት እንደሚፈልጉ ነግረውኛል” ምክንያታቸውም ስምና ፎቷቸው በስፋት ሲሰራጭ ስለነበር ለደህንነታቸው በመስጋት እንደሆነ ነግረውኛል በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህንንም የጠባቂዎቹን ውሳኔ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ እንደተናገረና ኮሚሸነሩም የጠባቂዎቹ ፍላጎት ይህ ከሆነ የፖሊስ አባልነታቸውን በመተው ሊሆን እንደሚገባ ተነጋግረው፤ “በእጃቸው ላይ የነበረውን የጦር መሳሪያና የመንግሥት ንብረት መልሰው ከእኔ ጋር ቀርተዋል” ሲል ጃዋር ተናግሯል።

ለጃዋር ከፌደራል ፖሊስ ተመድበውለት ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት የሠራዊቱ አባላት አራት ሲሆኑ አራቱም የፖሊስ አባልነታቸውን ትተው ከእሱ ጋር ለመሆን መወሰናቸውንም ተናግሯል።

የፌደራል ፖሊስ ቀደም ሲል ለተለያዩ ታዋቂ ፖለቲከኞች መድቧቸው የነበሩትን ጥበቃዎች የማንሳት እርምጃ እየወሰደ መሆኑ እንደተገለጸለት የሚናገረው ጃዋር “የእኔን ያንሱ ችግር የለብኝም፤ ብዙ ሕዝብ ነው ያለኝ። እርምጃው ግን ትክክል አይመስለኝም” ይላል።

በሌሎች አገሮች አሰራር መሰረት አከራካሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው የደህንነት ስጋት ያለባቸው ሰዎች ጥበቃ ይደረግላቸዋል በማለት “ለጃዋር ብለው ሌሎችን አደጋ ላይ መጣል የለባቸውም” በማለት በግሉ ጠባቂዎች መጠበቅ እንደሚችል ገልጿል።

ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በድንገት እኩለ ሌሊት ላይ ጠባቂዎቹን ለማንሳት ሙከራ እንደተደረገና ይህንንም ጃዋር በማህበራዊ መድረኮች ላይ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በተከሰተ ውዝግብና ግጭት ከ80 በላይ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል።(ምንጭ፡- ቢቢሲ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top