Connect with us

አየር መንገዱ 70 በመቶ የምግብ ግብዓቶችን ከውጭ እንደሚያስመጣ ገለፀ

አየር መንገዱ 70 በመቶ የምግብ ግብዓቶችን ከውጭ እንደሚያስመጣ ገለፀ
Photo: Facebook

ኢኮኖሚ

አየር መንገዱ 70 በመቶ የምግብ ግብዓቶችን ከውጭ እንደሚያስመጣ ገለፀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቅርቦት ማነስ የተነሳ ለተጓዦች መስተንግዶ አቅርቦት የሚያውለውን 70 በመቶ የምግብ ግብዓቶችን ከውጭ እንደሚያስመጣ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቋሚ ኮሚቴ አባላት አየር መንገዱን በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት አየር መንገዱ በቀን 50ሺ ቶን ምግብ ለተጓዦች እንደሚያቀርብ ገልጸው፤ በአገር ውስጥ በቂና አስተማማኝ የምግብ ግብዓቶች አቅርቦት ማግኘት ባለመቻሉ ከውጭ ለማምጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አየር መንገዱ ከመቂና ባቱ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር መፍጠሩና ደብረ ብርሃን አካባቢም ለአየር መንገዱ የግብርና ምርቶችን እንዲያቀርቡ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተወልደ፤ አቅርቦቱ በጥራትና በመጠን አስተማማኝ ባለመሆኑ አየር መንገዱ አሁንም 70 በመቶ የምግብ ግብዓት ከውጭ እያመጣ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ በውጭ ምንዛሬ እየገዛ ከውጭ የሚያመጣቸውን የምግብ ግብዓቶች በአገር ውስጥ ምርት መተካት ቢቻል የውጭ ምንዛሬን ከማዳን በተጨማሪ የስራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፤ አምራቾች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚፈልጋቸው 81 የምግብ ግብዓቶች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ዶሮ፣ማር፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚገኙበት የሚገልጹት የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ሱሉልታ ፤ከእነዚህ የምግብ ግብዓቶች ውስጥ አየር መንገዱ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኘው መቂ ባቱ ህብረት ስራ ማህበር ጋር ውል ባሰረው መሰረት 11 ዓይነት ምርቶች ማህበሩ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ ያስፈልጉናል ብሎ ካቀረባቸው 81 የምግብ ግብዓቶች መካከል አብዛኛውን በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለማቅረብ ከአየር መንገዱና ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ የተወጣጡ የጋራ የግዥ ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ማህበራቱ ማቅረብ የሚችሏቸውን ምርቶች ለይቶ የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡

ቀደም ሲል አየር መንገዱ የስንዴ ዱቄት ከማህበራቱ መግዛት የጀመረ ቢሆንም በኋላ የግዥ ስርዓቱ አይፈቅድልንም በሚል የስንዴ ዱቄት አቅርቦትን አቋርጦ እንደነበር አውስተው አሁን የስንዴ ዱቄቱን ለማቅረብ ከአየር መንገዱ ጋር ስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡

በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች የተደራጁት የህብረት ስራ ማህበራት አየር መንገዱ የሚፈልገውን የምግብ ግብዓቶች ማቅረብ ይችላሉ የሚሉት አቶ ታረቀኝ ምርቶቹን ጥራታቸውን የጠበቀና አስተማማኝ ለማድረግ ለአርሶ አደሮች የአቅም ግንባታ ስራዎች እንደሚያስፈልጉና በአየር መንገዱ በኩል ጅማሮ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱም ከውጭ የሚያስገባቸውን አብዛኞቹን የምግብ ግብዓቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ህብረት ስራ ማህበራትና አየር መንገዱ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው የተጠናከረና የተናበበ ስራ መስራት ከተቻለ ሁሉንም ግብዓቶች በአገር ውስጥ ምርት መተካት የማይቻልበት ሁኔታ የለም ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበራት ለአየር መንገዱ የተወሰኑ የምግብ ግብዓቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ ለአዲስ አበባ ሸማቾች ማህበራትና ለሶማሌ ላንድ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 29/2012

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top