Connect with us

በአዲስ አበባ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሴፍቲኔት በጀት ጥቅም ላይ ሳይውል ቀረ

በአዲስ አበባ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሴፍቲኔት በጀት ጥቅም ላይ ሳይውል ቀረ
Photo: Facebook

ዜና

በአዲስ አበባ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሴፍቲኔት በጀት ጥቅም ላይ ሳይውል ቀረ

የአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት ከምግብ ዋስትና ፕሮግራም ካፒታል በጀት ከተመደበላት አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ውስጥ የግዥ አቅም ባለመፍጠሩ አንድ ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር መጠቀም እንዳልቻለ ተገለጸ። በጀቱን መጠቀም ያልተቻለው ዓለም ባንክ ክፍለ ከተሞች ግዥ የማካሄድ አቅም የላቸውም በሚል ምክንያት መሆኑን የከተማው አስተዳደር የልማታዊ ሴፍትኔት ኤጀንሲ አመለከተ።

የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና አስተባባሪ አቶ ደበበ ባሩድ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በርካታ የማህበራዊ ልማት ችግሮች ያሉባት አዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት ከምግብ ዋስትና ፕሮግራም ካፒታል በጀት ከተመደበላት አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር የግዥ አቅም ባለመፍጠሩ የጥቅም ላይ የዋለው ከ60 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ ነው።

ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የካፒታል በጀት ቢመደብለትም የተጠቀመው ስድስት በመቶ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ደበበ፤ የከተማ አስተዳደሩ የካፒታል በጀቱን ለትምህርት ቤት ዕድሳት፣ለአቅመ ደካማ ቤቶችን ጥገና፣ለህዝብ መጸዳጃና መታጠቢያ(ሻወር)ቤቶችንና ውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ የሚውል ቢሆንም የዓለም ባንክ ከፍለ ከተሞች ለግንባታ የሚሆኑ ግብዓቶችን ግዥ ለማካሄድ አቅም የላቸውም በማለቱ አንድ ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር መጠቀም ሳይቻል መቅረቱን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእነዚህ ማህበራዊ ተቋማት ትልቅ ችግር እያለበት እንኳ ከበጀቱ የተጠቀመው 60 ሚሊዮን 585 ሺህ 413 ብር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በ2012 በጀት ዓመትም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት የተመደበለት ቢሆንም በጀቱን አይጠቀምበትም የሚል ስጋት አላቸው። በቀጣይም ተመሳሳይ የገንዘብ አጠቃቀም ችግር እንዳያጋጥም አስተዳደሩ ከወዲሁ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚኖርበት አቶ ደበበ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትናና የልማታዊ ሴፍትኔት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት እስጢፋኖስ ከምግብ ዋስትና ካፒታል በጀቱ ስድስት በመቶ ብቻ መጠቀሙን አምነዋል።የበጀት አፈጻጸሙ ዝቅ ያለው ግን ከግዥ ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልጸዋል። አስተዳደሩ የከተማውን ነዋሪ ፍላጎት መነሻ በማድረግ አንድ ሺህ 55 ብዛት ያላቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርፆ 600 ሚሊዮን ብር የግንባታ ግብዓቶች ግዥ እንዲፈጸም ዕቅዱን ለፌዴራልና ለዓለም ባንክ ቢያሳውቅም ከፍለ ከተሞች ግዥ የመፈጸም አቅም የላቸውም የሚል ምላሽ ተሠጥቶናል ብለዋል።

በምግብ ዋስትና ፕሮግራም አማካኝነት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የሚውሉ ግብዓቶች ግዥ የሚፈጸመው በማዕከል መሆን እንዳለበት ስምምነት ቢኖርም በአዲስ አበባ ከክፍለ ከተሞች ስፋት አንጻር በማዕከል የግብዓቶች ግዥ ቢፈጸም የህዝብ ገንዘብ ለሌብነት፣ ለአሰራር ዝርክርክነትና ለብክነት ተጋላጭ ይሆናል በሚል የማዕከል ግዥውን ማካሄድ አለመቻሉን ተናግረዋል። ግዥውን በተለይ የግንባታ ግብዓቶች አሽዋ፣ ጠጠርና እንጨት

በክፍለ ከተሞች ደረጃ ይፈጸም የሚል ጥያቄ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ለዓለም ባንክ ብናቀርብም የዓለም ባንክ ያቋቋመው ቡድን ክፍለ ከተሞች ግዥ የመፈጸም አቅም የላቸውም የሚል ምላሽ በመስጠቱ ምክንያት ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

“ኤጀንሲው የአቅም ክፍተቱት ለመድፈን የግዥ ሰራተኞችን ቅጥር የፈጸመና ስልጠና የሰጠ ቢሆንም እንደገና የዓለም ባንክ ያቋቋመው ቡድን ጥናት አድርጎ ከስድስት ወር በኋላም አሁንም መስተካከል ያሉባቸው ጉዳዮች አሉ የሚል ምላሽ ተሠጥቶናል።ይህም በመሆኑ ያለፈው ዓመትና የዘንድሮን አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት እስከ ታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ድረስ መጠቀም አልተቻለም” ብለዋል።

የፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ ደካማ በመሆኑ ምክንያትና በተደጋጋሚ በአፈጻጸም ችግር መተቸት የለብንም በሚል ኤጀንሲው ኃላፊነቱን ወስዶ በአሁኑ ጊዜ 576 ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ግዥ ለመፈጸም ጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለተማሪዎች ምገባ አዳራሽ፤ የህዝብ መጸዳጃና መታጠቢያ ቤቶች፣የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና የትምህርት ቤቶች ግምጃ ቤቶችን 137ሺ90 የምግብ ዋስትና ተጠቃሚዎችን በማሳተፍ ለመገንባት ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ለአቶ ታምራት ከሌሎች ከተሞች ልምድ ለምን አትወስዱም የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው፤ የሌሎቹ ከተሞች አንድ ክፍለ ከተማ ስፋት የአዲስ አበባን አንድ ወረዳ አያህልም። አዲስ አበባ 121 ወረዳዎች አሉ። ከአንድ ማዕከል የሚገዙትን የተለያዩ ግብዓቶች ለእነዚህ ወረዳዎች ተደራሽ ማድረግ ለብክነት፣ለስርቆት ይዳርጋል በሚል ብሩን መጠቀም አልቻልንም ሲሉ አብራርተዋል።

ከጋምቤላና ሀዋሳ በስተቀር ስምንት ከተሞች (መቀሌ፣ደሴ፣ሀረር፣አሶሳ፣ጅግጅጋ፣ሰመራ፣አዳማ፣ድሬዳዋ) የግዥ አቅማቸው በዓለም ባንክ በመረጋገጡ ከ90 በመቶ በላይ በጀታቸውን መጠቀማቸውን አቶ ታምራት ገልጸዋል።

(አዲስ ዘመን ጥር 29/2012)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top