Connect with us

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ሥጋት ውስጥ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ሥጋት ውስጥ
Photo: Quartiz Africa

ጤና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ሥጋት ውስጥ

ቫይረሱ ሊዛመትባቸው ይችላሉ ተብለው ከፍተኛ ስጋት ካለባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ለቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ያደረጋት ከቻይና ጋር ያላት ቀጥተኛ እና ከፍተኛ መጠን ያለው የተጓዥ ቁጥር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ ባደረገ ቁጥር ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰራጭበትን አጋጣሚን ከፍ ያደርጋል የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች እንደቀጠሉ ናቸው።

አየር መንገዱ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ መሰረዝ አለበት ብለው ከሚከራከሩት መካከል አንዱ የጤና ባለሙያው ዶ/ር የሺዋስ መኳንንት ይገኙበታል።

ዶ/ር የሺዋስ የበሽታውን ባህሪ እና የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሽታው ወደ አገር ቢገባ የሚያስከትለው ኪሳራ በቀላሉ የሚተመን አይሆንም ይላሉ።

“ባለን የጤና ሥርዓት አይደለም ኮሮናቫይረስ፤ ቀላል የሚባሉ ወረርሽኞችን መቆጣጠር አቅቶናል” የሚሉት ዶ/ር የሺዋስ እንደማሳያነት ከዚህ ቀደም ድሬዳዋ አካባቢ ቺኩንጉኒያ የሚባል ወረርሺኝ ተነስቶ መሠረታዊ የሆኑ መድሃኒቶች እጥረት አጋጥሞ እንደነበረ ያስታውሳሉ።

“እኔ ድሬዳዋ ነው የምሰራው። ባለፈው ክረምት ላይ ቺኩንጉንያ የሚባል ቫይረስ ተከስቶ ፓራሲታሞል ጠፍቶ ታማሚዎችን ሆስፒታል አስተኝተን የሰውነት ሙቀት ስናወርድ የነበረው በውሃ በተነከረ ጨርቅ ነበር። ይህ የጤና ሥርዓት ኮሮናቫይረስን ይከላከላል ማለት ከባድ ነው” ይላሉ።

“የሙቀት መጠንን በመለካት በሽተኛን በትክክል መለየት አይቻልም። አንድ ሰው የበሽታውን ምልክት ሳያሳይ 14 ቀናት ሊቆይ ይችላል። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ሰዎች ከማንም ጋር ሳይገናኙ መቆየት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ግን ከማህብረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ነው የሚገኙት።

“አንድ ምልክቱን ያሳየ ሰው አክሱም ላይ አለ ሲባል በጣም ነው ያዘንኩት። ቫይረሱ እኮ በ 6 ጫማ [2 ሜትር ገደማ] ርቀት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። ይህ ሰው አክሱም እስኪደርስ ከስንት ሰዎች ጋር ተገናኝቶ ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ ዶክተሩ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እስከ ጥር 24/2012 ድረስ 47 ሺ 162 ተጓዦች በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሙቀት መለያ ምርመራ እንደተደረገላቸው እና ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺ 695ቱ የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት መሆኑን አስታውቋል።

ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሃገር ውሰጥ በሚቆዩበት ወቅት አድራሻቸው ተመዝግቦ ለአስራ አራት ቀናት ክትትል ይደረግባቸዋልም ተብሏል።

ክትትል ይደረግባቸዋል የተባሉት ከ1 ሺ 600 በላይ ሰዎች ወደ ማህብረሰቡ ተቀላቅለዋል።

ከእነዚህ መካከል በጣት የሚቆጠሩት ሰዎች እንኳ ቫይረሱ ቢኖርባቸው እስካሁን ባላቸው ቆይታ የሚገናኟቸው ሰዎችን እንዲሁም የተገናኟቸው ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉትን ግነኙነት በማስላት ቫይረሱ በቀላሉ ሊሰራጭ እንደሚችል ስጋታቸውን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።

በቅርቡ አውስትራሊያ ከቻይና ዜጎቿን ማስወጣቷ ይታወሳል። አውስትራሊያ የሰውንት ሙቀት ለክታ ወደ አገር ከማስገባት ይልቅ፤ ከቻይና ተመላሽ ዜጎቿን ለ14 ቀናት ርቃ በምትገኝ ደሴት ላይ ለማቆየት ነው የወሰነችው።

የዩናትድ ኪንግደም መንግሥትም ከቻይና የተመለሱ እንግሊዛውያንን ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ስፍራ ለማቆየት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል።

ኢንስቲትዩቱ ግን ቫይረሱ ቢከሰት 4 ተርሸከርካሪዎች እና አራት የጤና ተቋማትን ጨምሮ በተጠንቀቅ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ቡድን መኖሩን አሳውቋል።(ምንጭ፡- ቢቢሲ አማርኛ)

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top