Connect with us

አራት አዲስ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ ተገኙ

አራት አዲስ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ ተገኙ
Photo: Facebook

ጤና

አራት አዲስ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ ተገኙ

በአሁኑ ወቅት አራት ሰዎች ማለትም አንድ ቻይናዊ እንዲሁም ሶስት ኢትዮጵያውያን በኖቭል ኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ፤ አንድ በአክሱም እና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት መጠናቀቁን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ የሚከተለውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21, 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን (Wuhan) ግዛት የተከሰተ መሆኑን አሳውቋል፡፡ በድርጅቱ ሪፖርት መሰረት ይህ በሽታ ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 24, 2012 ድረስ ከ 23 ሀገራት በጠቅላላ 14, 557 ታካሚዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ከቻይና ውጪ ያሉ አገራት 146 በቫይረሱ የተጠቁ ታካሚዎችን ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ፈረንሳይ፣ ኔፓል፣ ካናዳ፣ ማሌዥያ፣ ቬትናም፣ ካምቦዲያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሲሪላንካ፣ ፊንላንድ፣ ህንድ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ ይገኙበታል፡፡ ሌሎች የመረጃ ምንጮች (የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮኖና ቫይረስ ኬዞች) እስከ ጥር 25 ድረስ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ 17,373 ሰዎች የደረሰ ሲሆን 362 ታካሚዎች ህይወታቸው ማለፉን ዘግበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስትር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ እየተወሰዱ ካሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ውስጥ ብሔራዊ ታስክ ፎርስ እና በኢንስቲትዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ማዕከል ስራ ጀምረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከቦሌ አየር መንገድ፣ ከግልና ከመንግስት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ለ200 የሚሆኑ የሆስፒታል አመራሮች እና ባለሞያዎች በጤና ሚኒስተር አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል፡፡

በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እና 27 የተለያዩ የድምበር መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ ይገኛል፡፡

የማጣራት ምርመራው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸውን ተጓዦች የሚለይ ሲሆን ይሄም የቫይረሱ የበሽታ ምልክት የሚያሳዩትን ለመለየት ይረዳል፡፡እስከ ጥር 24/2012 ድረስ 47,162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1,695ቱ የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሀገር ውስጥ በሚቆዩበትን ግዜ፤ አድራሻ፤ እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎች መዝግቦ በመያዝ እስከ 14 ቀን ድረስ የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ይህም ምልክት በሚያሳዩበት ግዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና ንክኪ ያላቸውን ለመለየት ይረዳል፡፡ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን (rapid response team) ተዋቅሮ የቫይረሱ ምልክቶችን ጥቆማ በተሰጠ ከ2 ሰዓት ባነሰ ግዜ ውስጥ ማጣራት እንዲችል ለ24 ሰዓት በፈረቃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡ ለዚህም ስራ የአየር ማረፊያዎች ፤ ሆስፒታሎች፤ የታክሲማህበራት፤ ኢንደስትሪያል ፓርኮች እና የኮንስትራክሽን ቦታዎች የጠበቀ እይታ አግኝተዋል፡፡

ቫይረሱ አለባቸው ተብሎ የሚጠረጠሩትን ታካሚዎች ህክምና ወደ ሚያገኙበት ቦታ የሚወስዱ 4 ተሸከርካሪዎች(2 ኣምቡላንሶች)ተመድበው ወደ ስራ ተሰማርተዋል፡፡የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በቦሌ ጨፌ ያለው የህክምና ቦታ እና የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ለህክምና መስጫነት ተመርጠዋል፡፡ የህክምና ቦታዎች የወረርሽኝ ስርጭት ለመቀነስ የታካሚ ብዛትን ያማከለ ሲሆኑ፤ የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ስፔሻላይዝ ባደረገበት በጽኑ ህሙማን እና በሳንባ ህመም ዘርፍ የአርተፊሻል የሳንባ ሕክምና መርጃ መሳሪያ (mechanical ventilator) ህክምና ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ እንዲሁም ለህክምና የሚያስፈልጉ መድሀኒቶች፤ የህክምና እቃዎች ፤ የግል ደሕንነትን መጠበቂያ እቃዎች ( personal protective equipment) ወደ ህክምና ቦታዎች ተሰራጭተዋል፡፡ ህክምና ለመስጠት የሚያስችሉ ፕሮቶኮሎች እና መመሪያዎች ተሰርተዋል፡፡ በክልሎች ላይም ተመሳሳይ መዋቅር እንዲደራጅ የተጠየቀ ሲሆን አንዳንድ ክልሎች ላይ የዝግጅት እና ምላሽ ስራ ተጀምሯል፡፡

ለጥቆማ እና መረጃ ለማግኘት ነጻ የስልክ መስመር 8335 ከጥር 24/ 2012 ጀምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ እስካሁን 17 ጥቆማዎች የደረሱን ሲሆን ፤ ከነዚህም ስምነቱ በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲደረግላቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ከቻይና ውሃን ግዛት የመጡ እና የመተንፈሻ አካል ህመምና ከፍተኛ ሙቀት ማሳየት የጀመሩ ሁለት (2) ሰዎች እና ከእነርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ተጨማሪ ሁለት(2) ሰዎች ተገኝተው በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንና ናሙናቸውም ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ጥር 21/2012 ዓ.ም. የምርመራ ውጤቱ የደረሰንና ሁሉም ናሙናዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ በዚያው ቀን ከለይቶ ማቆያ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ለቤተሰቦቻቸው ሲደረግ የነበረው ክትትል ተቋርጧል፡፡

በአሁኑ ወቅትም አራት ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው ፤ አንድ ቻይናዊ እንዲሁም ሶስት ኢትዮጵያውያን፤ አንድ በአክሱም እና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

የኖቬል ኮሮና ማረጋገጫ ምርመራ ሪኤጀንት በአለም የጤና ድርጅት ትብብር አማካኝነት ወደ ሀገራችን በቅርቡ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቫይረሱ የተጠቁ ታካሚዎችን በመለየት እና አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት ለወረርሽኝ ቁጥጥር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

በሽታውን ሪፖርት ወደ አደረጉ ሀገራት ሄዶ የበሽታውን ምልከቶች ማሳየት የጀመረ ሰውን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቋም ማሳወቅ ወይም ከታች በተገለፁት አድራሻዎች በመጠቀም ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን phemdatacenter@gmail.com ወይም ephieoc@gmail.com በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡
(ምንጭ :- ኢ.ኘ.ድ)

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top