Connect with us

ፈስ መቋጠርና የጤና ጠንቁ

ፈስ መቋጠርና የጤና ጠንቁ
Photo: Facebook

ጤና

ፈስ መቋጠርና የጤና ጠንቁ

በደንደኔያችን ውስጥ ጋዝ እንዲከማች የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን ከነኝህ ውስጥ በትንፈሳ የምንምገው አየር፣ የምንመገበው ምግብ እንዲሁም በአንጀታችን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ባክቴሪያዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ ምግብ አላምጠን ስንውጥ 10 ሚሊ ሊትር የሚሆን አየር አብረን እንውጣለን፤ ማስቲካ ስናኝክ በቋሚነት አየር እያስገባን ነው፤ በጥናቶች በታወቀው መሰረት በ24 ሰዓት ውስጥ 30 ሊትር የሚሆን አየር በአንጀታችን ያልፋል፤ ይህ አየር እንግዲህ ንጥር እንደመሆኑ መጠን ህይወት እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለሰውነት በማቀበል የድርሻውን የሚወጣ ነው፤ ከዚህ አየር ውስጥ ጠቃሚ የሆኑት ወደ ደም ይቀላቀላሉ፤ ከ200 እስከ 500 ሚሊ ሊትር የሚሆን ጋዝ ደግሞ ከሰውነት እንዲሸኝ ይደረጋል፤ በአንጀታችን የሚላወስ አየር ጤናማና ለህይወት አስፈላጊ ነው።

የምንምገው አየር በግሳት መልክ ተመልሶ ካልወጣ በምግብ እንሽርሽረት ስርዓት ውስጥ እስከ አንጀታችን ይጓዛል።

በደንደኔያችን ውስጥ ጋዝ እንዲከማች የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን ከነኝህ ውስጥ በትንፈሳ የምንምገው አየር፣ የምንመገበው ምግብ እንዲሁም በአንጀታችን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ባክቴሪያዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል
ከምንምገው አየር ውስጥ አብዛኛው የኦክስጅን ጋዝ ወደ አንጀታችን ከመድረሱ በፊት በሰውነት ይመጠጣል፤ በመሆኑም የተማገው አየር ወደ ትልቁ አንጀት ሲደርስ አብዛኛው ይዘቱ የናይትሮጅን ጋዝ ነው።

በከርሳችን ውስጥ የሚገኘው አሲድና ሌሎች ፈሳሾች ከምግብ ጋር የሚያደርጉት ኬሚካላዊ ውህደት የካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ጋዝ ሊፈጥር ይችላል። ናይትሮጅንም ሆነ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዞች የምንተነፍሰው አየር አካል ናቸው። ከነዚህ በተጨማሪ ሃይድሮጅንና ሜቴን ጋዝ በባክቴሪያዎች እንቅስቃሴ አማካኝነት በደንደኔያችን ውስጥ ይፈጠራል። እንግዲህ በፈስ አማካኝነት የሚለቀቁት እነኝህ ጋዞች ናቸው። የነዚህ ጋዞች ዓይነት፣ ልኬታቸውና ሽታቸው በተመገብነው ምግብ፣ በማግነው አየር እና በደንደኔያችን ውስጥ ተጠልለው በሚገኙ የባክቴሪያዎች ዓይነት የሚወሰን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ይህንን ጋዝ ቋጥረን የያዝንበት የጊዜ ርዝመት የናይትሮጅን ጋዝ መጠን በደንደኔ ውስጥ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል፤ ምክንያቱም ሌሎቹ ጋዞች ወደ ደም ተመልሰው በአንጀት ግድግዳዎች አማካኝነት ሊመጠጡ ይችላሉ።

በፈስ አማካኝነት የምናስወግደው አየር ምን ያክል ነው?

ቀደም ብለን እንደጠቀስነው በአማካኝ ከ200 እስከ 500 ሚሊ ሊትር የሚሆን ጋዝ ከአንጀታችን በቀን እንለቃለን፤ በዚህ ስሌት መሰረት አንድ ሰው በአመት ቢያንስ 73 ሊትር ጋዝ ወይም ፈስ ይለቃል ተብሎ ይገመታል፤ አብዛኞቻችን ይህንን አየር በቀን ውስጥ ከ10 እስከ 20 በሚደርስ የአየር ጊዜ ብን እናደርጋለን።

አንድ ሰው በአመት ቢያንስ 73 ሊትር ጋዝ ወይም ፈስ ይለቃል ተብሎ ይገመታል

ምግብ ስንመገብ በምግቡ ውስጥ የሚገኝ ንጥር ከኛ በተጨማሪ በደንደኔያችን ተጠልለው የሚገኙ ባክቴሪያዎች ይጠቀሙታል፤ በደንደኔያችን ውስጥ ከ10 ቢልየን የሚበልጡ ባክቴሪያዎች ይገኛሉ፤ ይህ ማለት በአንድ ሰው ውስጥ ከሚገኝ አጠቃላይ የህዋሳት ቁጥር በአስር እጥፍ የሚበልጥ ነው፤ የነኝህ ባክቴሪያዎች ኑሮ እንግዲህ እኛ በምንመገበው ምግብ ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፤ እነኝህ ባክቴሪዎች አብዛኞቹ በጎ ምግባር ያላቸውና ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሚባሉ ናቸው።

ከምግብ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ሆዳችን ለምን ይነፋል?

ማንኛውም ሰው ጥሬ ሽንኩርት የበዛው ምግብ፣ ጥቅል ጎመን፣ ባቄላ፣ አተር እና የጥራጥሬ ምግቦችን ከበላ በኋላ ሆዱ የመነፋት ሁኔታ ያጋጥመዋል፤ ይህ የሚሆንበት ምክንያት እነኝህ ምግቦች በሰው ልጅ በቀላሉ የማይፈጩ ካርቦሃይድሬት ያላቸው ምግቦች በመሆናቸው ነው፤ ነገር ግን ይህ ለኛ የማይፈጭ ምግብ በአንጀታችን ውስጥ ተጠልለው በሚገኙ ባክቴሪያዎች ዘንድ ልክ እንደ ተወዳጅ ምግብ ነው። ባክቴሪያዎች ይህንን ካርቦሃይድሬት በሚሰባብሩ ወቅት የተለያየ ጋዝ ይፈጠራል፤ ክምችቱም እየጨመረ ሲሄድ በአንጀታችን ግድግዳዎች ላይ ግፊት በመፍጠር የመወጠር ሁኔታ ይፈጠራል፤ ይህ ጋዝ መላ ካልተባለ ምቾት ማጣትና የሆድ ሕመም ሊያጋጥመን ይችላል።

ማንኛውም ሰው ጥሬ ሽንኩርት የበዛው

እንደ ሽንኩርት፣ አበባ ጎመን፣ ጥቅል ጎመን ያሉ ምግቦች ራፊኖስ( raffinose) የተባለ ካርቦሃይድሬት አላቸው፤ ይህ ካርቦሃይድሬት በከርስም ሆነ በትንሹ አንጀት ውስጥ ተሰባብሮ በሰውነት አይፈጭም፤ ጤናማ የሚባሉ ምግቦች አብዛኞቹ ከፍተኛ ጋዝ በደንደኔ ውስጥ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው፤ ምቾትም ላይሰማን ይችላል። በጠቅላላው አባዝርት(አበባ ዝርት) ምግቦች ሆድ የመንፋት ሁኔታ አላቸው፤ ጠንካራ ጠረን ያለው ጋዝም አላቸው።

በተለይ በምግብ ድቀትና ልመት ስርዓት ውስጥ ሳይፈጩ አልፈው ትልቁ አንጀታችን ውስጥ የደረሱ ምግቦች በባክቴሪያዎች አማካኝነት ይፈላሉ(ferment)፤ በሂደቱ ብዙ ጋዝ ስለሚፈጠር የሆድ መወጠር ሁኔታ ይፈጠራል። በተለይ ምግብ በፍጥነት ስንበላ፣ ጋዝ ያላቸው መጠጦችን ስንጠጣ፣ መስቲካ ስናኝክ አየር ወይም ጋዝ በደንደኔያችን ይከማቻል፤ ይህ ሁኔታ ኢሮፋጂያ(aerophagia) ይባላል። በሕክምናው ዘርፍ በደንደኔ ውስጥ ስለሚፈጠር ጋዝ ጥናት የሚያደርጉ ሐኪሞች ያሉ ሲሆን ዘርፉ ፍላቶሎጂ(flatology) ይባላል፤ የሚያጠኑት ሰዎች ደግሞ ፍላቶሎጂስት(flatologists) ይባላሉ።

የጋዝ(ፈስ) ኬሚካላዊ ይዘትን ልኬት ምን ይመስላል?

በአንድ ሰው ደንደኔ ውስጥ የሚፈጠረው የጋዝ(ፈስ) ክምችት ከሰው ሰው የሚለያይ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱ ደግሞ በአመጋገብ ልማድ፣ በደንደኔ ውስጥ የተጠለሉ ባክቴሪያዎች ዓይነትና ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በመሆኑም ሆዳችን ሲወጠር ምክንያቱ በሳብነው አየር የተነሳ ከሆነ የዚህ ጋዝ ክምችትም ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፤ በመሆኑም ብዙም ሽታ አይኖረውም።

ነገር ግን የሆድ መወጠር የመጣው በበላነው ምግብ ወይም በውስጣችን ተጠልለው በሚገኙ ባክቴሪያዎች እንቅስቃሴ ከሆነ፣ ጋዝ(ፈስ) ከበድ የሚል ጠረን ሊኖረው ይችላል። እንግዲህ ሰው ሁኖ የማይመገብ ስለሌለ ለብዛኞቻችን የጋዝ(ፈስ) የኬሚካል ሙሊቱ ከዚህ በታች ተገልጧል። ከነዚህ ጋዞች ውስጥ ሚቴን እና ሃይድሮጅን ተቀጣጣይ ጋዝ በመሆናቸው በአመቺ ሁኔታ ውስጥ እሳት መፍጠር የሚችሉ ናቸው።

የምናስወጣው ጋዝ አይነትና መጠን

ናይትሮጅን(Nitrogen): 20-90%
ሃይድሮጅን(Hydrogen): 0-50% (ተቀጣጣይ ጋዝ)
ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ(Carbon dioxide): 10- 30%
ኦክስጅን (Oxygen): 0-10%
ሚቴን(Methane): 0-10% (ተቀጣጣይ ጋዝ) ነው።
ባቄላ ከሁሉም ምግቦች በበለጠ ለምን ጋዝ በጋዝ ያደርገናል?

የባቄላ ጋዝ ማብዛት ምክንያቱ የአሰር( fiber) ምግብ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፤ ማለትም ኢሟሚ( insoluble) የሆነ ካርቦሃይድሬት አለው፤ ምንም እንኳን ካርቦሃይድሬት ቢሆንም፣ አሰር ድርብርብ ስኳር ነው(oligosaccharide)፤ ይህ ማለት በኛ በምግብ ድቀት ስርዓት ውስጥ አይሰባበርም፤ በመሆኑም ልክ እንደ ስኳርና ስታርች ለኃይል ጥቅም ላይ አይውልም፤ ለምሳሌ ባቄላ ኢሟሚ የሆነ ሦሥት ዓይነት ድርብርብ ስኳር አለው( stachyose, raffinose, and verbascose)።

ይህ ሁኔታ እንዴት ወደ ጋዝ ያመራል?

ባቄላ ስንመገብ እነኝህ ድርብርብ ስኳሮች(oligosaccharides) ከአፍ ጀምረው ከርስ፣ ትንሹ አንጀት እና ትልቁ አንጀት እስከሚደርሱ ድረስ አይፈጩም ወይም አይነኩም፤ እነኝህን ስኳሮች ሰው ለመፍጨት የሚያስችለው አቀላጣፊ ኢንዛይም የለውም፤ ነገር ግን በደንደኔያችን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ባክቴሪያዎች ሊሰባብሩት ይችላሉ፤ ይህንን ሲያደርጉ ጠቃሚ የሆኑ ሚነራሎች በመለቀቅ ወደ ደማችን ይዘልቃሉ፤ ተጠቃሚም እንሆናለን። እነኝህ ዘአካሎች (microbes) በተጨማሪም ሌሎች ድርብርብ ስኳሮች(oligosaccharide polymers) ቀለል ወዳሉ ካርቦሃይድሬት ይቀይሩዋቸዋል፤ ባክቴሪያዎች ይህንን ሲያደርጉ ሃይድሮጅን፣ ናይትሮጅን እና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ እንደተረፈ ውጋጅ በመፍላላቱ ሂደት ይለቀቃል፤ ከነዚህ ዘአካሎች ውስጥ ደግሞ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሚቴን ጋዝም ይለቃሉ።

በመሆኑም በአሰር የበለፀጉ ምግቦች በተመገብን ቁጥር ብዙ ጋዝ ከባክቴሪያዎች ይመረታል፤ ይህ ሂደት ሆድን በመወጠር ምቾት እስከመንሳት የሚደርስ ነው። እየገፋ ሲመጣ ደግሞ የፊንጢጣ ሸምቀቆ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ጋዙ ብን ብሎ ይወጣል፤ በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ፈሳ ይባላል፤ ይህ እንግዲህ ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ የሆነ ሂደት ነው። ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ የአሰር ምግቦችን ለሰዓታት ወይም ለቀናት በውኃ በመዘፍዘፍ እና አብስሎ መመገብ ሊረዳ ይችላል።

አልፋ ጋላክቶሲዴስ (alpha-galac tosidase) የተባለው ኢንዛይም እነኝህን ድርብርብ ስኳር (oligosaccharides) ያላቸውን ምግቦች እንዲፈጩ የሚያስችል ሲሆን እነኝህ ኢንዛይሞች ተደርገውባቸው የሚሸጡ ድርብርብ ስኳር (oligosaccharides) ያላቸው ምግቦች ሁኔታውን ሊቀርፉ የሚችሉ ናቸው።

ጥራጥሬ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች በጣም ጤነኛ የሆነ ደንደኔ ቢኖራቸውም ፈስ ግን ያስቸግራቸዋል፤ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ደግሞ የጤናማነታቸው ሁኔታ ብዙ ጥያቄ ያለበት ቢሆንም ፈስ የመፍጠር ሁኔታቸው ግን ዝቅተኛ ነው።

የጋዙ (የፈስ) ሽታ ከየት መጣ?

በጣም ከባድ የሆነ ሽታ ያላቸው ጋዞች ድኝ ወይም ሰልፈር ያላቸው በናኝ ጋዞች ናቸው፤ በመሆኑም እንደ እንቁላል እና ጥቅል ጎመን ያሉት ድኝ ወይም ሰልፈር የሚበዛቸው ምግቦች ከተመገብን ጠንከር ያለ ሽታ ያለው ጋዝ ይኖረናል። የጋዙ ኬሚካል ይዘትና ሽታው ከሰው ሰው የሚለያይበት ምክንያት ከምንመገበው ምግብ እና ከአንዳንድ የጤና ሁኔታዎች የተነሳ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ የአትክልት ተመጋቢና የስጋ ተመጋቢ ሰው የተለያየ ነው። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት

•ስካቶል(skatole) እና ኢንዶል(indole )( ስጋ ከተመገብን በኋላ የሚፈጠሩ ተረፈ ኬሚካሎች)
•ሚቴንኢቶል(methanethiol) (የድኝ ውቅር)
•ዳይ ሚቴል ሰልፋይድ(dimethyl sulfide) (የድኝ ውቅር)
•ሃይድሮጅን ሰልፋይድ(hydrogen sulfide) (የበሰበሰ እንቁላል ሽታ ያለውና ተቀጣጣይ ጋዝ)
•አጭር ሰንሰለት ያላቸው ፋቲ አሲዶች(short chain fatty acids) እና
•በባክቴሪዎች (bacteria) የሚፈጠሩ የተለያዩ ጋዞች ናቸው።

እስካሁን ከተመለከትናቸው ውጪ የምናበነው ጋዝ ጠረኑ ከባድ ከሆነ፣ ከምንመገበው ምግብ ውስጥ ሰውነት አንዳንድ ንጥሮችን ሰባብሮ መምጠጥ ሲያቅተው ሊሆን ይችላል፤ በተለይ በዳቦ፣ በፓስታ፣ በሩዝ እና በድንች ውስጥ ያሉ ካርቦሃይድሬት ይህንን ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሁሉም ሰው ለተለያዩ ምግቦች የተለያየ ምላሽ ሊኖረው ይችላል፤ ብዙ ሰዎች ደግሞ በካርቦሃይድሬት ውስጥ የሚገኘው ላክቶስ ስኳር አይስማማቸውም፤ ላክቶስ የሚገኝባቸው ምግቦች ወተት፣ አይስክሬም፣ እርጎ፣ ቅቤና አይብ ናቸው። ላክቶስ ደማችን ውስጥ ከመግባቱ በፊት ወደ ግሉኮስ እና ወደ ጋላክቶስ መለወጥ አለበት።

እነኝህ ሰዎች ላክቶስን መፍጨት ስለማይችሉ፣ የተጠቀሱትን በላክቶስ የበለፀጉ ምግቦች ሲመገቡ ችግር ይገጥማቸዋል። በመሆኑም እንደ አይስክሬም፣ እርጎ፣ ወተት የመሳሰሉትን ምግቦች ከተጠቀምን በኋላ ከፍተኛ የሆነ ጋዝ የሚያስቸግረን ከሆነ ምናልባትም ሰውነታችን ተፈጥሯዊ የሆነውን ላክቶስ(lactose) የተባለ ስኳር መፍጨት እንደማይችል የሚያመለክት በመሆኑ ሁኔታውን ተረድተን ምርጫችንን ማስተካከል አለብን።

ምግብ በልተን ሆዳችን የመነፋት ሁኔታ ካጋጠመው፡-
•በላክቶስ የበለፀገ ምግብ በልተን ሊሆን ይችላል፤
•በአሰር የበለፀገ ምግብ ተመግበናል፤
•በደንደኔያችን ውስጥ መጠናቸው የበዛ ባክቴሪያዎች አሉ፤
•ሲጋራ የምናጨስ ከሆነ ብዙ አየር ምገናል፤ በመሆኑም ይህ ችግር ሊፈታ የሚችልበት በር አንድ ነው።

በምግብ ድቀት ላይ የሚፈጠሩትን ጋዞች በአንዳች መንገድ ማስወጣት ካልቻልን ምቾት አይኖረንም፤ ስለዚህ….አመቺ ቦታ በመሄድ ማስተንፈስ ተገቢ ነው፤ በሰዎች ፊት ካመለጠንም፣ በተፈጥሯዊ ሂደት የመጣ በመሆኑ ይቅርታ ማለት እንጂ የሚያሳፍር ድርጊት መሆን የለበትም። እንደው የባሕል ጉዳይ ሆኖ ነው።

ፈስን መቆጣጠር ይቻላል ወይ?

በርግጥ ፈስን መቆጣጠር ይቻላል፤ ነገር ግን ምቾት የማጣት ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል፤ ምክንያቱም የዚህ ጋዝ መውጫ በር አንድ ነው፤ ወዴትም ሊሄድ አይችልም፤ ካላስወጣነው ሊያቁነጠንጠን ይችላል። የተቆጣጠርነው ቢመስለንም ሲቆይ ሆዳችንን ቀፍትቶ በመያዝ መላወስ ሊከለክለን ይችላል።

ፈስ መቋጠር ለጤና አደገኛነት አለው ወይ?

ፈሱን በመቋጠሩ የተነሳ የሞተ ሰው የለም፤ ነገር ግን በደንደኔያችን ውስጥ የጋዝ መጠራቀምና የሆድ መወጠር ፍፁም ምቾት የሚነሳና ሕመምም ያለው ነው፤ ተፈጥሯዊ ሁኔታውን የተረዱ ሰዎች ለአካባቢያቸው ብዙም ግድ ሳይሰጡ ሊተነፍሱ ይችላሉ፤ በተለይ ወንዶች ብዙም ግድ አይላቸውም፤ በሴቶች በኩል ግን አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታውን መቋጠር አንዳለ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፤ ሂደቱ ተፈጥሯዊ በመሆኑ ተፈጥሯዊ ማስወጫውን ተጠቅመን ብንተነፍስ የተሻለ ነው፤ ጋዝን አመቺ ቦታ ላይ በመሄድ ሰዎችን በማያስቀይም መልኩ ማስተንፈስ ተገቢ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ጥናቶች ጋዝ ቋጥሮ መያዝ ግፊቱ እየጨመረ ሲመጣ የኪንታሮት ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል የሚያሳዩ ናቸው፤ ይህ ሁኔታ ወይም ልምድ ሲደጋገም ደግሞ የተለጠጠ ሆድ እንዲኖር ያደርጋል የሚሉም ባለሙያዎች አሉ።

ፈስ በተፈጥሮ ሂደት የሚፈጠር ከሆነ መፍሳት ለምን ነውር ሆነ?

ፈስ ሁለት ነገሮች አሉት፤ ድምፅና ደስ የማይል ጠረን፤ ማንኛውም ወደ ሰውነታችን የሚገባ ነገር(ምግብና መጠጥ) የተቀደሰና ንፁህ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ በአንጻሩ ደግሞ ከሰውነት የሚወገዱ ነገሮች(ላብ፣ ፈስ፣ ሰገራ…) በሙሉ እንጠየፋለን፤ ይህ ነገር ተፈጥሯዊ ይመስላል። ጋዝ ማስወጣት(ፈስ) ለአብዛኞቻችን የሚያስቅ፣ አፀያፊ ወይም አድርገን የማናውቀው ነገር ብናስመስለውም፤ ሂደቱ ፍፁም ተፈጥሯዊና ለጤናችን አስፈላጊ የሆነ ነው።

ጋዝ(ፈስ) በተለያዩ የዓለም ማኀበረሰቦች ዘንድ

በአብዛኛው ማኀበረሰብ ጋዝ ወይም ፈስ መጨቆን አለበት የሚል አመለካከት ያለ ቢሆንም፣ አንዳንዶች ደግሞ ልክ እንደ አንድ አስደሳች ሁኔታ ይመለከቱታል፤ ለምሳሌ በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ዮኖማሚ( the Yanomami) የተባሉ ማኀበረሰቦች በሰው ፊት መፍሳት ይቅርና ላጥ በማድረግ እንደሰላምታ መለዋወጫ ይጠቀሙበታል፤ በቻይና ደግሞ የፈስ ሽታ በሽታን ለመለየት ያስችላል የሚል ሳይንስ አላቸው፤ እንደውም እንደ አንድ ሙያ ዘርፍ ነው፤ ሰዎች እንደ ባለሙያተኛ አሽታች ሆነው ገንዘብ ያገኙበታል። በጥንቷ ሮም ደግሞ ንጉሰ ነገስት ክላውደስ፣ ፈስን ጨቁኖ መያዝ ለበሽታ ያጋልጣል በሚል ሰው በተሰበሰበበት ድግስ ቦታም ቢሆን ሰዎች እንዲፈሱ ሕግ አስተላልፎ እንደነበር ድርሳናት ያሳያሉ።

ካርቦሃይድሬት በአንጀት ውስጥ በተገቢው ሁኔታ መመጠጥ ካልቻለ፤ በደንደኔ ወይም በሆድ ዕቃ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪዎች ስለሚጠቀሙት እና እንደ እርሾ ስለሚያፈሉት በሂደቱ ከፍተኛ የጋዝ መጠን ይፈጠራል፤ ይህ ጋዝ እንዲወገድ ካልተደረገ፣ ሆዳችን እንዲወጠር ያደርጋል።

ጋዝ ማለት ብንጨቁነውም ምርቱ እስካለ ድረስ በተፈጥሮው እየተስፋፋ የሚሄድ ነገር ነው፤ አንዳንዴ ከምግብ በኋላ ሆዳችን ቀስ እያለ የሚወጠረው ምግቡ ሲሰባበር በሂደቱ የሚፈጠረው ኬሚካላዊ ውጤቶች በጋዝ መልክ መጠራቀም ነው፤ ይህ ጋዝ ወዴትም መሄድ አይችልም፤ መውጣት፣ መተንፈስ አለበት። በተጨማሪም ጋዝ በከፍተኛ አልቲቲዩድ እንዲሁም የአየር ጉዞዎችን ስናደርግ የግፊት ልዩነቶች ስለሚፈጠሩ የመስፋፋት ሁኔታ ይኖረዋል፤ በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን የሆድ መወጠርና ምቾት ማጣት ሁኔታ ሊጨምር ይችላል።

ከእንስሳት እንደምስጥ የሚፈሳ የለም

ምስጦች ሚቴን የተባለውን ጋዝ ይለቃሉ፤ ሚቴን ጋዝ ለዓለም ሙቀት መጨመር እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ጋዞች አንደኛው ነው፤ ምንም እንኳን ለማመን የሚከብድ ቢሆንም ከእንስሳት ምስጦች ሚቴን ጋዝ በመልቀቅ ቀዳሚ ቦታ ይዘዋል። በአካባቢ ደህንነት ባለስልጣን መረጃ መሰረት ምስጦች በተፈጥሯዊ መንገድ ከሚፈጠረው የሚቴን ጋዝ የቀጣይነት ደረጃን ይዘዋል። ሚቴን ምስጦች የሚመገቡትን ምግብ ከተጠቀሙት በኋላ የሚፈጠር ተረፈ ውጋጅ ጋዝ ነው፤ በመሆኑም የምስጦች ፈስ ልንለው እንችላለን።

በመጨረሻም ሰዎች ከሞቱ በኋላም እስከ ሦስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የፈስ ድምፅ ሊወጣቸው ይችላል፤ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው ሲሞት የሚያጋጥመው ጊዜያዊ የሆነ የጡንቻ መኮማተር ስለሚኖር ነው። በመሆኑም ይህ ሁኔታ እንደው በአንድ አጋጣሚ ቢያጋጥመን የሚያስደነግጥ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ይህ ሁኔታ እንዳለ አስታውሱ፡፡

(ምንጭ አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top