Connect with us

አጃኢብ ነው!… ሜንጫችንን እንደጦር መሣሪያ?

አጃኢብ ነው!... ሜንጫችንን እንደጦር መሣሪያ?
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

አጃኢብ ነው!… ሜንጫችንን እንደጦር መሣሪያ?

አጃኢብ ነው!… ሜንጫችንን እንደጦር መሣሪያ?

(ጫሊ በላይነህ)

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ ዐዋጅን በትላንት ውሎው አጽድቋል፡፡ የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ የድጋፍም የተቃውሞም ድምጾች እየተሰሙ ነው፡፡ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እንዲሁም አጠቃቀም አስፈሪ በሆነ መልክ መስፋፋት ያስተዋሉ ወገኖች የሕጉን መውጣት ከመዘግየቱ በስተቀር በአዎንታ ተቀብለውታል፡፡

ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎቹ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ…በተቀሰቀሱ ግጭቶች ጥቅም ላይ መዋላቸው የሰብዓዊ ቀውሱን በአስቸጋሪ ደረጃ እንዳሳደገውም የምናስታውሰው ነው፡፡ እነሜንጫ፣ ገጀራ፣ ቀስት፣ ጦር፣ ሴንጢ እና የመሳሰሉት ባህላዊ መሣሪያዎች ሳይቀር ኢ- ሰብዓዊ በሆነ መልኩ ለሰዎች ጭፍጨፋ ውለውም ተመልክተናል፡፡

አዲሱን አዋጅ የጦር መሳሪያ፣ ቀላል የጦር መሳሪያ፣ ትናንሽ የጦር መሳሪያ፣ ሙሉ አውቶማቲክ፣ ግማሽ አውቶማቲክና አውቶማቲክ ያልሆነ የጦር መሣሪያ ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም አስቀምጧል፡፡ ለዚህ አዋጅ በሚመች መልኩ አንዳንዶቹም ከአለምአቀፍ ትርጉማቸው ለየት ባለመልኩ ለመተርጎም ጥረት ተደርጓል፡፡

የጦር መሳሪያ ባይሆኑም የጦር መሳሪያን ያክል አደገኛ በመሆናቸው አጠቃቀማቸውን፣ ስርጭታቸውን እና የአመራረት ሂደቱን መቆጣጠርና በህግ አግባብ መግዛት አስፈላጊ በመሆኑ “ጉዳት ማድረሻ ዕቃዎች”ን በህጉ ውስጥ ለማካተት የተሞከረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት፣ በስለታማነታቸው ምክንያት ወይም የኤሌክትሪክ ሀይል በመጠቀም ወይም መርዛማ በመሆናቸው በሰው አካልና ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ የሚችሉ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ጎራዴ፣ ሴንጢ፣ ጦር፣ ሜንጫ፣ቀስትና ተመሳሳይ መሳሪያዎችን እንዲሁም በእጅ የሚያዙ ቴዘር መሳሪያዎች፣ አስለቃሽ ጢስ፣ እና ተመሳሳይነት ያላቸውን ኬሚካሎች ጉዳት ማድረሻ እቃዎች በሚል ትርጉም ሰጥቷል፡፡

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ሁለተኛው ተቃውሞ የሚነሳው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ አርሶደሮችና አርብቶአደር አካባቢዎች እንደሳንጃ፣ ሴንጢ፣ ሜንጫ፣ ጦርና ጎራዴ መያዝ እንደባህልም የሚታይ ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም እንደምስራቅ ሐረርጌ ባሉ አካባቢዎች እንደሜንጫ ያሉ መሣሪያዎች ለመደበኛ የእርሻ ሥራ አርሶአደሩ የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በከፊል ጋምቤላ እና ደቡብ እና በአማራ ክልሎች ጦር፣ ጎራዴ እና ቀስት መታጠቅ እንደባህል የሚታይና የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በአዋጁ እነዚህ የሕዝብ የዕለት ተዕለት መገልገያዎች በጦር መሣሪያነት የመካተቱ ተገቢነት ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዳባ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ሐተታ ክልከላው አርሶደሩ የሚጠቀምበትን መሣሪያዎች እንደማይመለከትና አርሶአደሮች ለማምረቻ መሣሪያነት የፈለጉትን ያህል መጠቀም እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም በአዋጁ የተከለከለው ሆን ተብሎ ሕዝብን ለሕዝብ ለማጫረስ እንደሩዋንዳ እንደሆነው በብዛት ለጥፋት እንዲውል የሚመረት ወይንም ከውጭ የሚገባ ከሆነ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

እዚህ ላይ ዐብይ ጥያቄው እነዚህን መሣሪያዎች ለምርት ተግባር የሚውል ነው ወይንም ለጥፋት ተግባር የሚውል ነው ብሎ የመጨረሻ ውሣኔ የሚሰጠው አካል ማነው? ይህን ውሣኔ አስፈጻሚው አካል የሚሰጥ ከሆነ እንደፈለገ ለመወሰንና ለማጥቂያነት ቢጠቀምበት መከላከያው ምንድነው የሚለውም በግልጽ መስመር መለየት አለመቻሉ ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ መሣሪያዎቹ ሰዎችን ለማጥቃት ሲውሉ ጉዳት አድራሽ ናቸው፡፡ ግን እነዚህ መሣሪያዎች በጦር መሣሪያነት መመዝገብ ከሕዝቡ የቆየ ባህል አንጻር ምን አንደምታ ሊኖረው ይችላል የሚለው በአዋጁ ውስጥ በግልጽ አለመመልከቱ በቀጣይ የግጭትና አለመረጋጋት መንስኤ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top