በአደይ አበባ ቅርፅ እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊው ብሄራዊ ስታዲየም ሁለተኛ ዙር ግንባታ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
መንግስት ለግንባታው ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግም ተገልጿል።
በታህሳስ ወር 2008 ዓ.ም የተጀመረው የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር በዝግጅት ላይ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ዙር የሚገነባው ስታዲየሙ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ 99 በመቶ መድረሱን ኮሚሽኑ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ባዘጋጀው የጉብኝት መርሃ ግብር ወቅት አስታውቋል።
ቀሪው የሜዳ ግንባታና የመም ማንጠፍ ስራዎች፤ በመጀመሪያው ውል በስታዲየሙ ግንባታ ማጠቃለያ ላይ የሚገነቡ ይሆናል። የሁለተኛው ምዕራፍ ስራ የጨረታ ሂደት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ቴክኒካዊ ጉዳዮች በአማካሪው ድርጅት በመገምገም ላይ ይገኛል።
በመሆኑም በቅርቡ ተጠናቆ የስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓት ሲካሄድ የተቋራጩ ማንነት እንዲሁም የገንዘብ መጠን ለህዝብ ይፋ ይሆናል። ከፍተኛ ወጪ በሚጠይቀው በዚህ ፕሮጀክት መንግስት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፤ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት በተቀመጠው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ጥረት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ 900 ቀናት ቢሆንም ከውጪ በሚገቡ ቁሳቁስ ምክንያት ጥቂት መዘግየት አጋጥሟል።
ይህ ግንባታም ከሁለት ዓመት ተኩል እስከ ሶስት ዓመት የሚፈጅ ሲሆን፤ በምንዛሬ ችግር በተለያዩ ክልሎች እንደሚስተዋለው መዘግየት እንዳያጋጥም መንግስት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽነር ኤሊያስ ሽኩር ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ተገኝተው መግለጫ የሰጡት ኮሚሽነሩ፤ በመንግስት በኩል ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አረጋግጠዋል።የመጀመሪያው ዙር ግንባታ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል።ለሁለተኛው ዙር ግንባታ ከዚህ በላይ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ መንግስት ለዚህ ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መድቧል።
ሁለተኛው ዙር ግንባታ በስታዲየሙ፤ የዙሪያ ጣራ ማልበስ፣ የደህንነትና የድምጽ ሲስተሞችን መዘርጋት፣ የወንበርና ስክሪኖች ገጠማ እንዲሁም የተለያዩ ክፍሎች፣ ቢሮዎችና የመገናኛ ብዙሃን መገልገያ ክፍሎች ስራን ያጠቃልላል።
ከስታዲየሙ ውጪም፤ ቢሮዎች፣ የዕቃ ማከማቻ ክፍሎች፣ የመኪና ማቆሚያና ሄሊኮፕተር ማረፊያ ስፍራዎች፣ ቲያትር ቤት፣ የባድሜንተን እና ሶስት በአንድ መጫወቻ ሜዳዎች፣ ሁለት የመለማመጃ ሜዳዎችን እንዲሁም በስታዲየሙ አጠገብ የሚያልፈውን ወንዝ አልምቶ ለመዝናኛ ማዋልን የያዘ ሰፊ ስራ ነው። (ኢኘድ)