Connect with us

ሚዲያዎች ተተቹ

ሚዲያዎች ተተቹ
Photo: Facebook

ዜና

ሚዲያዎች ተተቹ

አብዛኞቹ ሚዲያዎች የተራራቁ ሃሳቦችን፣ አተያዮችንና አመለካከቶችን በማቀራረብ ረገድ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ አለመሆናቸውን ጥናት አመላከተ፡፡ በዚህም ምክንያት ከሃሳብ ፍጭት ይልቅ ኃይል እንደ አማራጭ እየታየ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ መድረክ “የሚዲያው ሚና ሃሳቦችን ለማቀራረብ” በሚል መሪ ቃል በሂልተን ሆቴል በትላንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡ ‹‹ሚዲያ በሽግግር ወቅት ሊኖረው የሚገባው ሚና›› በሚል ለውይይት መነሻ የሚሆን የዳሰሳ ጥናት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ አቅርበዋል፡፡

አብዛኞቹ ዘገባዎች ዛሬም መደበኛ የሚዲያም ሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ዘገባዎች ከአንድ ምንጭ የሚቀዱ ከመሆን ባለፈ አንድ አይነት አስተሳሰብና አስተያየት የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ ሚዛናዊነት የሌላቸው፣ ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት የሚስተዋልባቸው እንደሆኑም ጥናት አቅራቢው ዶክተር ሙላት አስታውቀዋል፡፡

የሚሰሩ ዘገባዎች ህዝብን ከህዝብ፣ አስተሳሰብን ከአስተሳሰብ፣ አመለካከትን ከአመለካከት ጋር ከማቀራረብ ይልቅ ግጭት ቀስቃሽ፣ የጥላቻ ጽሁፎችና ንግግሮች በመደበኛ እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት መሰራጨታቸውን በጥናቱ ተመላክቷል። አብዛኞቹ የክልል ሚዲያዎችም ከክልላቸው ውጪ ስላለው ነገር ለአድማጭ እያደረሱ አይደለም፡፡ ዘገባዎቹም ስሜት ቀስቃሽ በማድረግ ‹‹እኛና እነሱ›› በሚል መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ሚዲያዎቹ ስለ አንድ አካባቢ እና ስለ አንድ አመለካከት ብቻ በመዘገብና ስለ ሌላኛው አካል አሉታዊ ዘገባ ስለሚሰሩ ‹‹እኛና እነሱ›› የሚል እሳቤ በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርጽ ማድረጋቸውን በዶክተር ሙላቱ የቀረበው የጥናት ውጤት አመላክቷል፡፡

እንደ ዶክተር ሙላቱ ማብራሪያ፤ በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰሩ ዘገባዎች ውስጥ ቀላል የማይባል የጥላቻ ቃላት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ከማህበራዊ ሚዲያ ከተወሰዱት 273 መረጃዎች ውስጥ አንድ ስድስተኛው የጥላቻ ቃላትን ተጠቅመዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት አብዛኞቹ ሚዲያዎች መንግሥት ላይ አሉታዊ ዘገባዎችን በመስራት ላይ ትኩረት ያደርጉ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ሃይማኖትና ብሄርን ያነጣጠሩ አሉታዊ ዘገባዎች በስፋት መስተዋላቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ሚዲያዎች ለሀገር ሰላምና መረጋገጥ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ቢታሰብም ጥቂት የማይባሉት በተጻራሪ መቆማቸው ተጠቁሟል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ሚዲያዎች የተለያዩ ሀሳቦች፣ አተያዮችና አመለካከቶች በሚዲያ እንዲፋጩ ባለመደረጉ ሀይልን የመጠቀም ሁኔታዎች መታየታቸውን ተናግረዋል፡፡ መጠላላት፣ መገዳደልና ቂም እንዲበራከት ሆኗል፡፡ ስለሆነም ሚዲያው በተራራቀ ጫፍ ላይ ያሉ ሀሳቦችን እንዲፋጩ ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ሀሳቦች ሲፋጩ አካላት አይጋጩም ብለዋል፡፡

ይህንን ለማድረግ ሚዲያው ሀሳብ የመቅረጽ የማመንጨት፣ የማስተማር ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ኃላፊነት መወጣት በእጅጉ የሚያስፈልግበት ወቅት አሁን ነው ብለዋል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሃሳብ ላይ መመካከርና መነጋገር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ህብረተሰቡን በሰከነ ሁኔታ መደማመጥ በሚያስችል መልኩ ማስተማር የሚያስፈልግበት ወቅት ነው ብለዋል አቶ ንጉሱ፡፡

የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም በሚዲያዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ አቅም መገንባት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ባለስልጣኑ ሚዲያዎችን አቅም ለማጠናከር በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

መሻሻል የሚገባቸው ህጎችም በማሻሻል ረገድም ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ መንግሥት የቤት ሥራውን ከጨረሰ በኋላ ሚዲያዎችን አደብ የማስገዛት ሥራዎችም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደምም ለተለያዩ ሚዲያዎች እስከ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቅሰዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው የሙያ ስነ ምግባሩን ተከትሎ የሚሰራ ጠንካራ ሚዲያ ለመፍጠር የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

(ምንጭ፡-አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2012)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top