Connect with us

ምርጫ ቦርድ ለብልፅግና ፓርቲ ዕውቅና ሰጠ

ምርጫ ቦርድ ለብልፅግና ፓርቲ ዕውቅና ሰጠ
Photo: Facebook

ዜና

ምርጫ ቦርድ ለብልፅግና ፓርቲ ዕውቅና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእውቅና ጥያቄ እና፣ የፓርቲ መለያ ሰንደቅ አላማ የማጸደቅ ጥያቄን ያቀረቡ ፓርቲዎችን ጉዳይ አይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚህም መሰረት

የኢህአዴግ አባል የነበሩ ሶስት ፓርቲዎች እና ሌሎች አምስት ፓርቲዎች በጋራ ራሳቸውን በማክሰም ብልጽግና ፓርቲን መመስረታቸውን በማሳወቅ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጣቸው ህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በጽሁፍ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረቡ ሲሆን ቦርዱም ጥያቄያቸውን በፓለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ 1162/2011 መሰረት መርምሮ ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት ቦርዱ የእውቅና ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ በተጨማሪ መሟላት ያለባቸውን ሰነዶች በታህሳስ 01 ቀን 2012 ዓ.ም በመጠየቅ በጥያቄውም መሰረት ታህሳስ 06 ቀን 2012 ዓ.ም የጥያቄዎቹ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሟልተው መቅረባቸውን በማረጋገጡ ብልጽግና ፓርቲን ለመመስረት

1. የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ( ኦዴፓ)፣
2.የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን)፣
3.የሃረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣
4.አማራ ዴሞክራያዊ ፓርቲ ( አዴፓ) ፣
5. የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ)፣
6. የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ፣
7.የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋህአዴን)
8.የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ቤጉህዴፓ)

በተናጠል በጠቅላላ ጉባኤያቸው ውሳኔ መሰረት አድርገው ውህደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም የወሰኑት ውሳኔዎች እንዲሁም ውህደቱን ለመመስረት ያደረጉትን ስምምነት በሙሉ ህጉን ተከትሎ የተፈጸመ በመሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት ውህዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሰረት በተመዘገበ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ ያስገኘውን ሃብትና ንብረት እና እዳ የሚያሳይ የሂሳብ ሪፓርት ለቦርዱ እንዲያቀርብ በውሳኔው ውስጥ ተካቷል፡፡

በተያያዘ ዜና የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ በምዝገባ ወቅት ያቀረበው ሰንደቅ አላማ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ይመሳሰላል በሚል በቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይመሳሰል በመግለጽ ልዮነቱን አብራርቶ ቦርዱ እንዲቀበለው ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ቦርዱ በሁለቱ ሰንደቅ አላማዎች መካከል አለ የተባለውን ልዩነት መርምሮ የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ የጠቀሳቸው ልዮነቶች ለማስተዋል የሚያስቸግሩ በመሆናቸው እና ድምጽ ሰጭዎችን የሚያምታቱ ሆነው ስለሚገኙ ሰንደቅ አላማውን ቀይሮ በማቅረብ ምዝገባውን እንዲያጠናቅቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም እናት ፓርቲ በሚል አገር አቀፍ ፓርቲ ለማቋቋም በሂደት ላይ ያለ ፓርቲ በአዋጅ 1162/ 2011 መሰረት ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን ጊዜያዊ ሰርተፍኬት መውሰጃ መስፈርት በማሟላቱ እናት ፓርቲ የጊዜያዊ እውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ቦርዱ ወስኗል፡፡

(ምንጭ:-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top