Connect with us

”ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የተሰኘ አገራዊ ፕሮግራም በይፋ ሊጀመር ነው

”ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የተሰኘ አገራዊ ፕሮግራም በይፋ ሊጀመር ነው

ኢኮኖሚ

”ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የተሰኘ አገራዊ ፕሮግራም በይፋ ሊጀመር ነው

ለአገራችን ወጣቶች የተሻለ ተጠቃሚነት በጎ አንድምታ እንዳለው የታመነበት ”ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” የተሰኘ አገራዊ ፕሮግራም በይፋ ለማስጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፕሮግራሙ መጀመርን አስመልክቶ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ያለም ጸጋይ “ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” በዋናነት የወጣቶችን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ትስስር ከማሳደግ ጎን ለጎን ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ብሎም ለአገራቸውና ለአህጉራቸው አፍሪካ ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና ገንቢ አስተዋጽኣቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከወጣቶች ስብዕና ልማት፣ ከስራ ፈጠራ፣ ከበጎ ፈቃደኝነትና ማህበራዊ አገልግሎት፣ ከሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ምርምርና ስርጸት ጋር የተያያዙና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ ሃሳቦችን ማዕከል አድርጎ የሚተገበር በመሆኑ እነዚህን አስመልክተው የተነደፉ የመንግስት ፖሊሲ ዓላማዎች ስራ ላይ እንዲውሉና የሚፈለገውንም ውጤት እንዲያመጡ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግና በአስፈጻሚ አካላት ዘንድም የተሻለ መነቃቃት እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ የተነሳበት ዓላማ እውን እንዲሆን የአገራችን ወጣቶችን ጨምሮ ወጣቶችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ ማህበረሰብ – ተኮር ድርጅቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል ሴክተሮች፣ መላው ህብረተሰብና በጋራ እንዲረባረቡ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ያለም ጸጋይ ጥሪ አቀርበዋል፡፡

ዩዝ ኮኔክት ፕሮግራም የዩዝ ኮኔክት አፍሪካ ኢኒሼቲቭ አካል መሆኑን የገለጹት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም በሩዋንዳ መንግስት በተለይም በአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ፖል ካጋሚ አስተባባሪነትና በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) አጋርነት መጀመሩንና በአሁኑ ወቅትም 14 የአፍሪካ አገራት እየተገበሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያም ተሞክሮውን በመውሰድ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመና የአገራችን ወጣቶችን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ ፕሮግራሙን ለመተግበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን አስገንዝበዋል፡፡ ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገርም ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት አግባብ እቅድ እንደሚዘጋጅ፣ አፈጻጸሙንም የሚከታተል ስትሪንግ ኮሚቴ በየደረጃው እንደሚቋቋምና በፕሮግራሙ ዙሪያ የህብረተሰቡን የመረጃ ተደራሽነት ለማሳደግ ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

“ዩዝ ኮኔክት ኢትዮጵያ” ፕሮግራም ከታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በይፋ እንደሚጀመር የጠቆሙት ሚኒስትሯ በቀጣይም በጽንሰ-ሃሳቡና በዓላማው ዙሪያ ወጣቱንም ሆነ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላትንና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያግዙ ሰፋፊ የግንዛቤና ንቅናቄ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

በCenter for African Leadership Studies X Hub Addis ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነቱ ፕሮግራም ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን የመንግስት አካላትን፣ የማህበራዊ ጥናት ፖሊሲ አርቃቂዎችን፣ ስራ ፈጣሪዎችን፣ ባለሃብቶችን፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችንና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ሙያተኞችን በአንድ የሚያስተሳስርና የሚያገናኝ መድረክ መሆኑን ገልጸው ይህም በወጣቶች አጀንዳዎች ዙሪያ ችግር ፈቺ የሆኑ ሃሳቦችን በማፍለቅና ጠቃሚ ልምዶችን በመለዋወጥ የአስተሳሰብና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ ትብብርንና ህብረ – ሀይልን ለማጠናከር፣ ሀብትን ለማሰባሰብ፣ ፈጠራንና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት እንዲሁም አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን ለማስረጽ ሰፊ እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡(ምንጭ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር )

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top