Connect with us

የጨጓራ ባክቴሪያ እንዴት ይከሰታል? ምልክቶቹና ሕክምናውስ ምንድነው?

የጨጓራ ባክቴሪያ እንዴት ይከሰታል? ምልክቶቹና ሕክምናውስ ምንድነው?
Photo: Facebook

ጤና

የጨጓራ ባክቴሪያ እንዴት ይከሰታል? ምልክቶቹና ሕክምናውስ ምንድነው?

የጨጓራ ባክቴሪያ ወይም ሄሊኮባክተር ፓይሎሪ( Helicobacter pylori (H. pylori)) የባክቴሪያ አባል ሲሆን ወደ ሰውነታችን በመግባት በምግብ ጉዞ መንገድና ጨጓራ ውስጥ መኖር የሚችል ነው::

እነኝህ ባክቴሪያዎች መላ ሳይባሉ ለብዙ ዓመት ከቆዩ አልሰር የተባለ ቁስለት በጨጓራ ላይና በትንሹ አንጀት የላይኛው ክፍል እንዲፈጠር ያደርጋሉ:: ሂደቱ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ላይ ካንሰር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል::

በጨጓራ ባክቴሪያ መለከፍ በብዙዎች ላይ የሚያጋጥም የተለመደ በሽታ ነው፤ ከዓለም ሁለት ሦስተኛ በሚሆኑት ሕዝቦች ውስጥ ይህ ባክቴሪያ በሰውነታቸው ውስጥ ይገኛል፤ ባክቴሪያው አንዳንድ ሰዎች ላይ ምንም ምልክት የማያሳይ፣ የቁስለት ሁኔታም የማይፈጥር ቢሆንም ብዙዎችን ለሕመም ይዳርጋል::

ባክቴሪያው ሕመምተኛ የሚያደርገን እንዴት ነው?
ሐኪሞችና ተመራማሪዎች ለብዙ ዐስርት ዓመታት በጨጓራ ላይ ቁስለት የሚፈጠረው ከውጥረትና ጭንቀት ጋር በተያያዘ፣ ቅመም በበዛቸው ምግቦች፣ ሲጋራ በማጤስና በሌሎች ጎጂ ልማዶች የተነሳ ነው ብለው ያምኑ ነበር፤ ነገር ግን በ1982 ይህንን ባክቴሪያ ሲያገኙ በብዙ ሰዎች ጨጓራ ላይ ቁስለት ይፈጥር የነበረው እርሱ እንደሆነ ደረሱበት::

የጨጓራ ባክቴሪያ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በጨጓራ ንብርብር አካል ላይ ጥቃት በመፈፀም ጨጓራችንን ተጋላጭ ያደርገዋል፤ ምክንያቱም ጨጓራችን ምግብ ለመፍጨት አሲድ ይጠቀማል፤ ይህ አሲድ በጨጓራ አካል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚያደርገው የጨጓራ ንብርብር አካል ነው::

ይህ አካል ከተሸረሸረ፤ ጫጓራችን ለአሲዱ የተጋለጠ ስለሚሆን ከፍተኛ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል:: ጉዳቱ የደም መፍሰስ ጨምሮ አካሉ እንዲያመረቅዝ ወይም እንዲቆስል፤ እንዲሁም የበላነው ነገር እንዳይፈጭና እንዳይረጋ ሊያደርግ ይችላል፤ በዚህ ሁኔታም ሕመሙ መፍትሔ ካላገኘ ወደ ተወሳሰበ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል::
ይህ ባክቴሪያ እንዴት ሊይዘን ይችላል?

የጨጓራ ባክቴሪያ ከምንበላው ምግብ፣ ከምንጠጣው ውሃና ከምንጠቀማቸው በባክቴሪያው ከተበከሉ ቁሶች ሊያገኘን ይችላል:: በሽታው አብዛኛውን ጊዜ ፅዳት በሚጎድልባቸው አካባቢዎች የሚከሰት ሲሆን ባክቴሪያው በምራቅ ንክኪና ባክቴሪያው ካለበት ሰው ጋር በሚኖር የፈሳሽ ንክኪ ሊተላለፍብን ይችላል:: በሽታው ታዳጊ በሚባሉ አገሮች በስፋት የሚከሰት ነው::

አብዛኛውን ጊዜ ባክቴሪያው በኛ የሚጠለለው በልጅነት ጊዜ ሲሆን ምልክት መታየት የሚጀምረው ግን ለዓመታት ከቆየ በኋላ ነው:: ይሁን እንጂ አብዛኛው ባክቴሪያው ያለባቸው ሰዎች ቁስለት አያጋጥማቸውም:: ተመራማሪዎች የጨጓራ ባክቴሪያ አንዳንዶች ላይ ለምን ቁስለት ፈጥሮ እንደሚጠና ሌሎች ላይ ደግሞ ያን ያህል ችግር የማይፈጥረው ለምን እደሆነ የደረሱበት አይመስልም::

የጨጓራ ባክቴሪያ እንደለከፈን የሚታዩ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በባክቴሪያው አማካኝነት በጨጓራችን ላይ ቁስለት ከተፈጠረብን፣ የማቃጠልና የመደንዘዝ ስሜት በሆዳችን የላይኛው ክፍል ሊሰማን ይችላል፤ ይህ ስሜት ሄድ መጣ የሚል ሊሆን ይችላል፤ በተለይ ሆዳችን ባዶ በሚሆንበት ሰዓት ማለትም በመደበኛ የምንመገብባቸው ሰዓታት መሃል እና በሌሊት ጊዜ ሕመሙ በደንብ ሊሰማን ይችላል::

የሕመሙ ቆይታም ከደቂቃዎች እስከ ሰዓታት የሚቆይ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ምግብ እንደበላን፣ በተለይ ወተት እንደጠጣን እና ፀረ አሲድ መድኃኒቶችን እንደወሰድን ሕመሙ ጋብ ይላል:: በአጠቃላይ የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡-
• የሆድ መነፋት፣
• ግሳት፣
• የረሃብ ስሜት አለመሰማት፣
• ማቅለሽለሽ፣
• ማስመለስ፣
• ያለምክንያት ክብደት መቀነስ ሊታዩ ይችላሉ::
በጨጓራ ውስጥ የሚያጋጥም ቁስለት ደም ወደ ከርሳችንና አንጀታችን እንዲፈስ ሊያደርግ ይችላል፤ ከባድ የሚባል የጤና ችግርም ሊፈጥርብን ይችላል:: በመሆኑም የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩን ወደ ሕክምና በመሄድ የምንገኝበትን ሁኔታ መመርመር አለብን::
• የሰገራ መጥቆርና ደም መቀላቀል ካለ፣
• ለመተንፈስ መቸገር ካጋጠመን፣
• ያለስራ የመልፈስፈስና የድካም ስሜት ከተጫነን፣
• የቆዳ መገርጣትና ራስን የመሳት ሁኔታ ከታየብን፣
• የተፈጨ ቡና የመሰለ ነገር የሚያስመልሰን ከሆነ፣
• ከባድ የሆድ ህመም ካለን የጨጓራ ባክቴሪያ ሊሆን ስለሚችል መታየት አለብን::

አልፎ አልፎ ደግሞ የጨጓራ ባክቴሪያ የጨጓራ ካንሰር ሊያስከትል ይችላል፤ እንዲያ ሲሆን በመጀመሪያ አንዳንድ ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፤ ለምሳሌ ማቃር ሊበዛን ይችላል:: በመቀጠል ግን የሆድ ሕመምና ማበጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ያለመራብ ስሜት፣ ትንሽ ከተመገብን በኋላ በጣም የጠገብን የሚመስለን ስሜት መሰማት፣ ማስመለስና ምክንያቱ ያልታወቀ የክብደት መቀነስ ሊታይብን ይችላል::

በሕክምና ተቋም ለምርመራ ስንሄድ የጠቀስናቸው ምልክቶች ካልታዩብን የጨጓራ ባክቴሪያ ምርመራ ላይታዘዝልን ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት ባክቴሪያው ለክፎን የሚውቅ ከነበረ፣ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ከጨጓራ ባክቴሪያ ውጪ ለሕመም ማስታገሻ የሚወሰዱ እንደ አስፕሪን ያሉ መድኃኒቶች በጨጓራ ንብርብር ላይ ተመሳሳይ ጉዳት ሊያደርሱብን ይችላሉ፤ በመሆኑም ትክክለኛው የጨጓራ ሕመም የፈጠረብንን ነገር ለመለየት ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው::

ምርመራ
ምርመራ ላይ ሐኪሞች የሕክምና የኋላ ታሪክን በመጠየቅ ይጀምራሉ፤ የሚሰሙ ስሜቶችን፣ የወሰድናቸው መድኃኒቶች ካሉም ምን? ምን? እንደሆኑ ልንጠየቅ እንችላለን፤ በተጨማሪም ሆዳችንን በመጫን የእብጠት ወይም የሕመም ስሜት መኖርን በአካላዊ ምርመራ ሊያዩን ይችላሉ፤ በመቀጠልም የደምና የሰገራ ወይም ደግሞ የትንፋሽ ምርመራ እንድናደርግ ልንጠየቅ እንችላለን::

የትንፋሽ ምርመራ
የጨጓራ ባክቴሪያ መኖርና አለመኖሩን ለመለየት የዩሪያ ትንፋሽ ምርመራ( Urea breath test) ይደረጋል፤ በትንፋሽ ምርመራው ዩሪያ የተባለ ውህድ ፈሳሽ እንድንጠጣ ይደረጋል፤ በመቀጠልም ወደ ከረጢት ውስጥ እንድንተነፍስ ይደረግና ሊታይ ወደ ላብራቶሪ ይላካል፤ ባክቴሪያው በሰውነታችን ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ዩሪያውን ወደ ካርበን ዳይኦክሳድ ይቀይረዋል፤ በላብራቶሪ ፍተሻ ትንፋሻችን ከሚታወቀው ልኬት በተለየ መጠኑ የበዛ የካርበን ዳይኦክሳድ ጋዝ ካለ የባክቴሪያው መኖርን ያሳያል::

የቁስለት ሁኔታ ካለብን
በጨጓራችን ውስጥ ቁስለት መኖሩን ሐኪሞች ከጠረጠሩ የኢንዶስኮፒ ምርመራ ያደርጉልናል፤ ኢንዶስኮፒ ማለት ካሜራ የተገጠመለት ትቦ ሲሆን የውስጥ ጨጓራ አካላትን በምስል ሊያሳይ የሚችል መመርመሪያ መሳሪያ ነው:: ይህ ትቦ በአፋችን አድርጎ እስከ አንጀት ዘልቆ መግባት የሚችል ነው:: በዚህ መሳሪያ ለምርመራ የሚሆን ቅንጣትም ከውስጥ አካል መውሰድ ይቻላል::

በተጨማሪም የሲቲ ስካን፣ የኤም አር አይና በጨረር አመንጪ ቁስ የተደገፈ የራጅ ፎቶ በመነሳት ጥልቀት ያለው ምርመራ ሊደረግልን ይችላል:: የካንሰር ሁኔታ እንደተፈጠረም በዚው ሊታይ ይችላል:: የካንሰር ገጠመኝ ለመኖሩ በተጨማሪ የደም ማነስ ምርመራ ደደረጋል፤ የካንሰር ዕጢ ከተፈጠረ የመድማት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፤ ይህ ሁኔታም የቀይ የደም ሕዋስ በሰውነት ውስጥ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ በዚህ መንገድ ሊታይ ይችላል:: እንዲሁም በዐይን ለማይታይ የመድማት ሁኔታ ካለ በላቦራቶሪ እንዲመረመር ይደረጋል::

ሕክምና
በጨጓራ ባክቴሪያው አማካኝነት ያጋጠመን ቁስለት ካለ ባክቴሪያዎቹን የሚገድል ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት ወይም ከዛም በላይ የሚቆይ የመድኃኒት ሕክምና ሊሰጠን ይችላል፤ ቁስለቱ እንዲድንም ሌሎች መድኃኒቶች አብረው ይታዘዙልናል:: በዚህም መሰረት የተለያዩ መድኃኒቶችን በመቀላቀል ሊታዘዝልን ይችላል:: ይኸውም፡-
• አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች( amoxi¬cillin, clarithromycin (Biaxin), met¬ronidazole (Flagyl), tetracycline (Sumycin), or tinidazole (Tin-damax))፣ ባክቴሪያዎቹን ለመግደል ከተጠቀሱት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ ይታዘዝልናል::

• በጨጓራ ውስጥ አሲድ የሚረጩትን ጥቃቅን ቧንቧዎች በመዝጋት አሲድ የሚቀንሱ መድኃኒቶችን( dexlansoprazole (Dexilant), esomeprazole (Nex¬ium), lansoprazole (Prevacid), omeprazole (Prilosec), pantopra¬zole (Protonix), or rabeprazole (Aciphex)) አብረው ይታዘዛሉ::

• ጨጓራችን ብዙ አሲድ እንዲያመነጭ የሚያደርገውን ሂስታሚን የተባለውን ውሁድ መመረት የሚቀንሱ መድኃኒቶች( cimetidine (Tagamet), fa-motidine (Fluxid, Pepcid), nizatidine (Axid), or ran¬itidine (Zantac)) ጨምረው ሊያዙልን ይችላሉ::

በዚህ ሕክምና በቀን እስከ 14 የሚደርሱ መድኃኒቶችን ለሳምንታት እንድንውጥ ሊታዘዝልን ይችላል፤ 14 ኪኒኖችን በቀን መዋጥ ብዙ ይመስላል፤ ነገር ግን ይህንን ሕክምና ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ለምሳሌ የታዘዘልንን የአንቲባዮቲክ መድኃኒት በስርዓቱ በታዘዘው መንገድ ካልወሰድን፣ ባክቴሪያው ሳይጠፋም ቀርቶ መድኃኒቱን ልናለማምደው እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ቀጣይ የባክቴሪያ ልክፍቶች ሲያጋጥሙን ለማከም አስቸጋሪ ያደርገዋል:: የመድኃኒት ሕክምናውን ካደረግን በኋላ ባክቴሪያው ለመጥፋቱ ድጋሚ የሰገራና የትንፋሽ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል::

ምክር
የጨጓራ ባክቴሪያን ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ ሌሎች ጀርሞችን ለመከላከል ከምንወስደው የጥንቃቄ እርምጃ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይኸውም እጅን በሳሙና ከምግብ በፊትና ከመፀዳጃ ቤት መልስ በደንብ መታጠብ፣ በፅዱ ሁኔታ ያልተዘጋጀ ወይም የቀረበ ምግብና መጠጥ አለመጠቀም፣ ያልበሰሉ ምግቦችን አለመጠቀም ናቸው:: እንዲሁም ጭንቀትና ውጥረት፣ ቅመም የበዛባቸው ምግቦችና ሲጋራ ማጨስ ለጨጓራ ቁስለት የማይዳርጉን ቢሆንም ሁኔታውን ግን ሊያባብሱ ስለሚችሉ ቢያንስ ከቁስለት እስከምንድን ድረስ መጠቀም ወይም ማድረግ የለብንም::

ከዳንን በኋላ ምን እናድርግ?
አብዛኞቹ የጨጓራ ቁስለቶች ከሳምንታት ሕክምና በኋላ ይድናሉ፤ የጨጓራ ቁስለት ከዚህ በፊት አጋጥሞን ከሆነ፣ እንደ አስፕሪን ያሉ ለሕመም ማስታገሻ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን መውሰድ የለብንም፤ ምክንያቱም እነኝህ መድኃኒቶች የጨጓራችንን ድርብርብ አካል በመጉዳት ለአሲድ ተጋላጭ ሊያደርጉን ይችላሉ::

ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም የዘመን ሐኪም ዓምድ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top