Connect with us

ዶ/ር ደብረጽዮን አስጠነቀቁ፡- “…በማን ምን እየተፈጸመ እንዳለ እውነታውን ለሕዝብ እንናገራለን”

ዶ/ር ደብረጽዮን አስጠነቀቁ፡- "…በማን ምን እየተፈጸመ እንዳለ እውነታውን ለሕዝብ እንናገራለን"
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ዶ/ር ደብረጽዮን አስጠነቀቁ፡- “…በማን ምን እየተፈጸመ እንዳለ እውነታውን ለሕዝብ እንናገራለን”

“ህገ መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓትን ማዳን!” በሚል መሪ ቃል 2ኛው አገር አቀፍ ታሪካዊ የምክክር መድረክ በመቐለ ከተማ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የህወሓት ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር ያስተላለፉት መልዕክት እነሆ፡፡

***

ከሁሉ አስቀድሜ “ህገ መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓትን ማዳን!” በሚል መሪ ቃል

የሚካሄደውን 2ኛው አገር አቀፍ ታሪካዊ የምክክር መድረክ አገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ ለማላቀቅ

በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የመፍትሄ አካል ለመሆን ውይይቱ በሚካሄድበት ትግራይ መቐለ ከተማ በመገኘታችሁ በመላው የትግራይ ህዝብ ስም፣ በትግራይ ክልል መንግስትና በራሴ ስም እንኳን በደህና መጣችሁ ለማለት እፈልጋለሁ።

ከመጀመርያው መድረክ ልምድ በመውሰድና በማዳበር የዚሁ መድረክ ተሳታፊዎች ከዘጠኙ ክልሎች፣ 2 ከተሞችና ከፌደራል ያካተተ፥ የተሳታፊ ፓርቲዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት ዘርፈ ብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎም ላቅ ያለበት እንዲሆን ተደርጓል። በዚሁ መድረክ የተገኛችሁ ተሳታፊዎች ብዙ ውጣ ውረዶችና ጫናዎች ተቋቁማችሁ በመድረኩ የግድ መሳተፍ አለብን ብላችሁ በመምጣታችሁ ቁርጠኝነትን ለሁላችንም ስላስተማራችሁ የላቀ ምስጋና ይድረሳችሁ። በሌላ በኩል የመድረኩ አስፈላጊነት ተቀብላችሁና አምናችሁ ሳለ በጫናና በተለያዩ ምክንያቶች የቀራችሁ ባላችሁበትም ሆናችሁ በመድረኩ የሚደረሱ ድምዳሜዎችና ስምምነቶች በመተግበር አጋርነታችሁ እንደምታሳዩና በቀጣይ በሚዘጋጁ መድረኮች ተሳትፎኣችሁ እውን እንደሚሆን እንተማመናለን።

በመጀመርያው አገር አቀፍ መድረክ የተመረጡ የኮሚቴ አባላት ቀጣይ መድረኮችና ስራዎች በተደራጀ አግባብ ለማካሄድ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በባለቤትነትና በከፍተኛ ተነሳሽነት ባደረጉት ርብርብና ትግል እነሆ ሁለተኛው መድረክ በተሻለ ዝግጅትና ተሳትፎ እውን ሆኗል። በመሆኑም የኮሚቴው አባላት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት በመወጣታቸው ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል።

የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት ራስ በራስ፣ ሃገርን ደግሞ በጋራ በማስተዳደር መርህ ዜጎችና ቡድኖች የጋራ ጉዳያቸውን በሚመለከት በፌደራል መንግስት እንዲተዳደሩና በየኣከባብያቸው ደግሞ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን ስርአት በነፃነት ያቀዳጀ ነው። በመሆኑም ከመነሻው የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ለማረጋገጥ ያለመ፣ ህዝባዊ ውግንና ያለው፣ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገና ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የመነጨ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ ክልሎች ከአገሪቱ ህግ የተጣጣመ የየራሳቸው ህግና የየራሳቸው ምክር ቤት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ስለሆነም ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዲኖረው እድል የሰጠ ነው።

በዚሁ አጋጣሚ 14ኛው የብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች በዓል ህገ መንግስታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም በሚል መሪ ቃል የሚከበርበት ሳምንት በመሆኑ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።

በአሁኑ ጊዜ የሚታዩት በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መበራከታቸው እንደዚሁም በዜጎች ህይወት ላይ ስጋት እየጨመረ የመጣው በፌድራል ስርዓት በመመራታችን ሳይሆን ህገመንግስቱን ካለማክበርና የህግ የበላይነትን ካለማረጋገጥ መሆኑ በውል መረዳት ይገባል፡፡ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገው የአገራችን ፌዴራል ስርዓት አሉታዊና አዎንታዊ ገጽታዎች እንዳሉት ግን የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን አወንታዊ ገጽታውን በማጠናከር አሉታዊ ገጽታው ላይ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ህብረብሄራዊ ፌዴራሊዝምን ማስቀጠል አማራጭ አይኖረውም፡፡ ህገመንግስቱንም ቢሆን በተደጋጋሚ እንደተገለፀው ህገ መንግስታዊ መንገድ ተከትሎ ማሻሻል፥ መቀየር ይቻላል። ይገባልም።

ይሁን እንጂ አሁን በግላጭ እየተደረገ ያለው የፓለቲካ እንቅስቃሴ ህዝብን ማእከል ያላደረገ፣ የብሄሮች፣ ብሄሮችንና የህዝቦችን እኩልነት ያላከበረ፣ ጠቅላይ በሆነ አስተሳሰብ የተቃኘ ከመሆኑ ባሻገር ሁሉንም የአገራችን ህዝቦች የማያካትት በተለይ አርሶ አደሩን ያገለለ ነው። የሁሉም ህዝቦች ፍላጎት የማያስተናግድ የጠቅላይነት አስተሳሰብ አገሪቱ ወደ ከፋ ሁከት ብጥብጥና መበተን እንደሚያመራት ጥርጥር የለውም ፡፡ ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት ውስጣዊ ሁኔታችን ስታይ በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ ሃይሎች በተተበተበ አገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭነታችን እያየለ መጥቷል፡፡ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነው ሰላምም የደፈረሰበት፥ የህግ በላይነት የማይከበርበት፥ አገሪቱ ሕገ መንግስት በግላጭ የሚጣስበት፥ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በኣገራችን በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የዜጎች መብቶች በአደባባይና በስፋት እየተጣሱ የሚታዩበት፥ ዜጋው በነፃ ተንቀሳቅሶ ለመስራት፥ ሃብት ለማፍራት የተቸገረበት፥ ከዛም አልፎ ለጥቃት የተጋለጠበት፥ ወቅት ላይ እንገኛለን። የአገሪቱ ኢኮኖሚም በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ባጭሩ አሁንም አገራችን በፈታኝ፥ አደገኛና አስፈሪ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ቆም ብለን የቱን መንገድ ብንከተል ይሻላል? ምን ብናደርግ አገራችንን ከዚህ አጣብቅኝ ማላቀቅ እንችላለን? የሚሉ ጥያቄዎችን በመመለስ አገራችን ከተጨማሪ ጉዳትና ጥፋት ማዳን እንደምንችል መገንዘብ ይገባናል።

አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችለንን መንገድ ለመምረጥ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ወሳኝ ወቅት ሁሉም አገር ወዳድ አንድ ሃሳብ በመያዝ የተቀናጀ ስራ መስራት የግድ ይላል፡፡ ይህንን ኣስከፊና ኣደገኛ ሁኔታ ለህዝቦች የሂወት መጥፋት፣ ጉስቁልና፣ የወደፊት ተስፋ ማጣት፣ ሌሎችም ችግሮች እንዲጋለጥ ከማድረጉም በላይ በዚሁ ሂደት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በመናድ የከፋ እልቂት እንዳይፈጠር በሁሉም ዜጋ ስጋት እያየለ መጥቷል። ስለሆነም አገራችን ከገባችበት አዘቅ፣ ለማውጣትና እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ ለመቀጠል የሚያስችለንን መንገድ ለመምረጥ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል፡፡ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ በመፍታት ሰላም የሰፈነባት፥ ህዝቦቿ እንደታሪካቸው በመከባበር የሚኖሩባት፥ ስርአት ያላት አገር እንድትሆን ሁላችን ድርሻችን መጫወት አለብን።

ይህ መድረክ ፓርቲዎች ይሁኑ ግለሰቦች የመሰላቸውን ሃሳብ በማንሸራሸር ትግል የሚያካሂዱበት እንጂ ሃሳብ ወደ መድረክ እንዳይቀርብ፥ ልዩነቶች ታፍነው እንዲቀሩ የሚደረግበት ባለመሆኑ መድረኩ የፖለቲካ አጀንዳዎች በሰላም፥ በሕጋዊ መንገድና በስርዓት በማካሄድ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን የሚያጠናክር አጋዥ የፖለቲካ መድረክ ነው። እንደዚህ ዓይነት መድረክ በአገራዊ ጉዳዮች የተለያዩ ሃሳቦችን በማራመድና በመወያየት ሁሉም ወይም አብዛኛው ወደ ሚያስማማበት ድምዳሜ በመድረስ የአገራችንን ፓለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ እርምጃ ነው። ይህ ውይይት ተከታታይ መድረኮች በማካሄድ የአገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች ከመፍታት አንፃር የበኩሉን ታሪካዊ ሚና እንደሚጫወት እናምናለን።

ይሁን እንጂ የተለየ ሃሳብ የሚፈሩ፥ በውይይት፥ በመድረክ የማያምኑ ደካሞች በዚህ መድረክ ፓርቲዎችና ግለሰቦች እንዳይሳተፉ በተለያየ መልኩና አግባብ ጫናዎች በማካሄድ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው አሳይተዋል። ይህ ጫናና ፀረ ዴሞክራስያዊ ተግባር መወገዝ ያለበት እና ህዝቡ በሕገ መንግስቱ የተጎናፀፈውን መብት የረገጠ አፋኝ ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ መቆምና ስርአት መያዝ ይገባዋል። ሃሳብ በሃሳብ መግጠም እንጂ አስተዳደራዊ በሆኑ ጫናዎች ልዩነቶች እንዳይወጡ፥ እንዲቀበሩ እየተደረጉ ያሉ የሃሳብ ደካሞች ተግባር መቆም አለበት። አለም አንድ መንደር በሆነበት ጎረቤታሞችም እንዳይገናኙ የሚከለክሉ የአለማችን ጉደኞች ከድርጊታቸው ቢቆጠብ ይሻላቸዋል። ካልሆነ በየአካባቢው እየተከናወነ ያለው ዘርፈ ብዙ ጫና የት፥ በማን ምን እንደተፈፀመ ለህዝቡ እውነታው እንደምናወጣ ከወዲሁ ይታወቅ።

ይህ መድረክ በተለየ ታሪካዊ ኣጋጣሚ እየተካሄድ ያለ፥ ከሁሉም በላይ ግን የአገራችን ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ተገቢ ምላሽ የሚጠይቅ ቁልፍ የአገራችን ጥያቄ በሆነበት ጊዜ እንገኛለን። የውጭ ጠላቶቻችን የአገራችን መዳከም ብቻ ሳይሆን መበታተን የግድ አስፈላጊ ነው ብለው በግላጭ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም በዚሁ መድረክ ያለንበትን ሁኔታ በመገንዘብ፥ ካለፈው ተምረን ቀጣይ የኢትዮጵያ ጉዞ የተቃና እንዲሆን ጠቃሚ ድምዳሜዎች የምንደርስበት፥ ስለሆነም ሁላችን ታሪክ ለመስራት ዝግጁ እንደምንሆን ትልቅ እምነት አለኝ።

የውይይት መድረኩ ህዝብ የሚጠብቀው ለውጥ ለማረጋገጥ የራሱን ድርሻ እንደሚጫወት፥ ለአገራችን ብሄር፥ ብሄረሰብና ህዝቦች የሚጠቅም፥ የራሱ በጎ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ታሪካዊ መድረክ እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ አለን። ስለሆነም በዚሁ መድረክ ተሳታፊ የሆናቹህና ሌሎች በተለያየ ችግር መሳተፍ ያልቻላቹህ በቀጣይ መድረኮች በንቃት በመሳተፍ ታሪካዊ ድርሻችሁን እንደምትወጡ ተስፋችን የላቀ ነው። በመደማመጥና በመደጋገፍ በአገራችን እየታዩ ያሉ ችግሮች ተገቢው መፍትሄ በመንደፍ ከወቅታዊ ችግሮች በመውጣት የተረጋጋና አስተማማኝ ፖለቲካዊ ሁኔታ እስከምንደርስ ቀጣይ ርብርብ እንደምናደርግ ተስፋችን የላቀ ነው።

በመጨረሻም በዚህ መድረክ አገርን የሚጠቅም አሁን እየታየ ያለውን የፖለቲካ ዝንፈት የሚያስተካክል መፍትሄ ላይ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ። የመቀሌ ቆይታችሁም ያማረ እና ፍሬያማ እንደሚሆን በመተማመን፣ መልካሙን ሁሉ እመኛሎህ።

ገለቶማ፥ አመሰግናለሁ፥ የቐንየለይ!

ህዳር 23 2012 ዓ/ም

(ምንጭ፡-ትግራይ ኤክስፕረስ)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top