ሀዋሳ (ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም) በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ላይ የሰብዓዊ መብት ሁኔታን አስመልክቶ የወጣ አጭር ቅድመ መግለጫ፤
ምንም እንኳን ምርጫው የተካሄደው በአጭር ጊዜ ሰሌዳ እና በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ባለበት ወቅት ቢሆንም፤ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ሲዳማ ዞን የተካሄደው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሰላማዊ የነበር ከመሆኑም ባሻገር በምርጫ ቀን የተከሰተ ከባድ ችግር አልነበረም፡፡
ሲዳማ አዲስ የክልል መስተዳድር መሆን ወይም የደቡብ ክልል መስተዳድር አካል ሆኖ መቀጠልን ለመወሰን በተዘጋጀው በዚህ ታሪካዊ ህዝበ ውሳኔ ላይ ለመሳተፍ በርካታ ሰዎች በብዙ ምርጫ ጣቢያዎች ለረጅም ሰዓታት በትዕግሥት ጠብቀው ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኢሰመኮ ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ያሰማራው 20 አባላት ያሉት የሰብአዊ መብት ክትትል ቡድን በኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የተመራ ነበር፡፡ የክትትል ቡድኑ በምርጫው ቀን በ 5 የከተማ አስተዳደሮች እና 15 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ከ 100 በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን ተመልክቷል፡፡
የኮሚሽኑ ምርጫ ክትትል ቡድን በቅድመ-ምርጫው ወቅትም ተጨማሪ በርካታ የምርጫ ጣቢያዎችን ተመልክቷል፡፡ ይህ የቅድሚያ መግለጫ በእነዚሁ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ላይ ብቻ በመመርኮዝ ስለ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እና አንዳንድ ቁልፍ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን የሚገልጽ እንጂ የተሟላ የምርጫው አጠቃላይ ግምገማ አይደለም፡፡
የቅድመ-ምርጫ እና ምርጫው የተካሄደበት ዕለት ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰላም የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የኢሰመኮ የሰብዓዊ መብት የክትትል ቡድን በምርጫው ቀን አነስተኛ ጉድለቶች ብቻ እንደነበሩ ሪፖርት አድርጓል፡፡ የድህረ ምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብት አከባበርን ሁኔታን ለመከታተል ያመች ዘንድ የኢሰመኮ የታዛቢዎች ቡድን በሲዳማ ዞን ይቆያሉ፡፡ የምርጫው ውጤት አጠቃላይ ድምር እና የቀረቡ ቅሬታዎች ካሉ የማጣራቱ ሥራ እንደተጠናቀቀ፤ የምርጫው ውጤት በመጪው ቀናቶች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ይፋ የሚሆን ይሆናል፡፡
ቁልፍ ግኝቶች
የመራጮች ምዝገባ በቅድመ-ምርጫው ወቅት
የመራጮች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑና 2.3 ሚሊዮን ያህል መራጮች መመዝገባቸው ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የኢሰመኮ ክትትል ቡድን ለመራጭነት ዕድሚያቸው ያልደረሰ የሚመስሉ ነገር ግን ለአካለ መጠን የደረሱ መሆኑን የሚያመለክት መታወቂያ ካርድ ያላቸው የተወሰኑ ወጣቶች የተመለከተ ሲሆን፤ ይህም ለምርጫ ቦርድ ሥራ ልዩ ተግዳሮት መሆኑን ተገንዝቧል ፡፡
ደህንነት በሁሉም ደረጃ ያሉ የክልልና የፌዴራል ባለስልጣናት እና የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለምርጫው አስፈላጊ የሆነው የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ እንዲፈጠር በጥሩ ሁኔታ መስራታቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫውን ሒደት የሚያውኩ የተወሰኑ የሕግ መጣስ ክስተቶች የነበሩና ይኸውም በሕግ አስከባሪ አካሎች ቁጥጥር ስር ከመሆኑ በስተቀር፤ የጸጥታና ደህንነት ችግር አልነበረም፡፡
የምርጫ ቅስቀሳ ሁኔታ
የምርጫ ቅስቀሳው አዲስ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት እንዲቋቋም በሚጠይቀው የሻፌታ ቡድን ከፍተኛ የበላይነት የተሞላ ነበር፡፡ ሲዳማ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት አካል ሆኖ እንዲቀጥል የቀረበው የአማራጩ የጎጆ ቡድን የምርጫ መረጃ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በቴሌቭዥንና ሬዲዮ በተመደበለት ሰዓቶች ከመደመጡ በስተቀር፤ የምርጫ ቅስቀሳ አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡
በአንጻሩ የሻፌታ ቡድን በሰላማዊ ሠልፍ፣ በስብሰባዎች፣ በጐዳናዎች እና ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር ጭምር ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል፤ እንዲሁም በሲዳማ ዞን መንገዶች እና አደባባዮች ልዩ ልዩ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶችን ሰቅለዋል፡፡ እነዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮችም የምርጫ ቅስቀሳው ጊዜ ከአለፈ በኋላም በየመንገዱ ይታዩ ነበር።
የኢሰመኮ የክትትል ቡድን አባላት በጎበኙት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የተወሰኑ የወጣት ቡድኖች ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፉ ሰዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ለአማራጩ የጎጆ ቡድን የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ የተከለከለ ነገር ባይኖርም፣ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ለኢሰመኮ ታዛቢዎች እንደገለጹት፤ በሲዳማ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ አማራጩን ሐሳብ በይፋ ለመቀስቀስ ስጋት እና ፍራቻ ነበር፡፡
የጎጆን አማራጭ ሊያቀርብ ይችላል ተብሎ የተጠበቀው በመጀመሪያ ያቀረበው የደቡብ ክልል መስተዳድር የምርጫ ቅስቀሳ አላደርገም፡፡ የሲዳማ ዞን አስተዳደር በአንጻሩ የሻፌታ ምርጫ ቅስቀሳን ድጋፍ የሰጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ለአማራጭ ሐሳብ የፖለቲካ ምህዳሩ ለማንኛውም ሰው ክፍት መሆኑን ገልጿል፡፡ በቅድመ-ምርጫ ወቅት ሀሳብ የመግለፅ፣ የመሰብሰብ ነጻነት እና የመንቀሳቀስ ነጻነት ላይ ምንም ዓይነት ገደብ አልተደረገም። የምርጫ አስተዳደር አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጨናነቀ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሰላማዊ ምርጫን ለማደራጀት እና ለማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ የሚከተሉትን ጨምሮ አነስተኛ የሥነ ሥርዓት ችግሮች ታይቷል፡፡
• ብዛት ያላቸው መራጮች የተመዘገቡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሥራ አፈጻጻም አስቸጋሪ መሆኑ፤ (በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከ 2000 የሚበልጡ መራጮች ተመዝግበዋል፣ ቢያንስ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 5675 መራጮች መመዝገባቸውን የኢሰመኮ የክትትል ቡድን ተመልክቷል)
• የተሟላ ምርጫ አስፈጻሚዎች የሌላቸው የምርጫ ጣቢያዎች፤ (በኢሰመኮ ታዛቢዎች የተጎበኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች 1 ወይም 2 ብቻ የምርጫ አስፈጻሚዎች ነበሯቸው)
• እንደ የድምፅ መስጫ ሳጥን፣ የምርጫ ወረቀቶች እና ቀለም ያሉ የምርጫ ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት መኖር (የኢሰመኮ ታዛቢዎች በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቦርድ የጐደሉ የምርጫ ቁሳቁስ በሟሟላት ምላሽ እንደሰጠ ተመልክተዋል)
• አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመሆን (የኢሰመኮ ታዛቢዎች የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የተንቀሳቃሽ ወንበር መግቢያ (ራምፕ) ያላቸው እንደሆኑ ተመልክተዋል)
• በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መግባት
• ድምጽ በሚስጥራዊነት ለመስጠት በበቂ ሁኔታ የተከለለ ምስጢራዊ ቦታ አለመኖር
• የድምፅ አሰጣጥን በሚመለከት ለመራጮች ተገቢውን መመሪያ ወይም መረጃ አለመስጠት፣
• የምርጫ ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያው ውጭ መሆን፣
• የተወሰኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች ኦፊሴላዊውን የአማርኛ ቋንቋ የማይናገሩ ስለነበሩ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻላቸው፡፡
የሕግ ማዕቀፍ አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አንድ የምርጫ ጣቢያ ለ1500 ሰዎች እንደሚያገለግል ይደነግጋል፡፡ ይህ ቁጥር ከአለም አቀፍ ደረጃ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ ከሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ተሞክሮ አንጻር ሲታይም ይህን ያህል መጠን ያለው የምርጫ ጣቢያ በአግባቡ ሥራውን ለማከናወን አስቸጋሪ መሆኑ ታይቷል፡፡ በአጠቃላይ በምርጫ ወቅት አንድ የምርጫ ጣቢያ 5 የምርጫ አስፈጻሚዎች የሚኖሩት ቢሆንም እና የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥርን ለመጨመር ሀብት የሚጠይቅ ቢሆንም የምርጫ ቦርድ ይህን አንቀጽ በመፈተሽ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሰው ብዛት ከ 750 እስከ 1000 ብቻ በማድረግ ሊያሻሽለው ይገባል፡፡