Connect with us

ከጸጥታ ሥጋት ጋር ተያይዞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ትምህርት ተቋርጧል

ከጸጥታ ሥጋት ጋር ተያይዞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ትምህርት ተቋርጧል
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ከጸጥታ ሥጋት ጋር ተያይዞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ትምህርት ተቋርጧል

በምክንያት አልባ ስጋት የፀጥታ ችግር በሌለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ቤታቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳሳዩ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ሚዲያዎች በተማሪዎች ላይ ስጋት እንዲያድር ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በዩኒቨርሲቲው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አለመኖሩን ተናግራል፡፡ የተቋሙን ሠላም ለማወክ የሚሠሩ አካላት መኖራቸውን ያመላከቱት ዶክተር አስራት የፀጥታ አካላቱ ይህንን በመረዳት በንቃት እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡም ከተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት የፀጥታ ችግር ሊፈጥሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር በትጋት እየተሠራ መሆኑን ነው ዶክተር አስራት የተናገሩት፡፡

ምንም እንኳን በዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ችግር ባይፈጠርም ከኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲውን የተቀላቀሉ ተማሪዎች በስጋት ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግን ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርስ በማግባባት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ቅኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎችን ከስጋት ነፃ ለማድረግ የፀጥታ አካላት የተጠናከረ የጥበቃ ሥራ እያከናውኑ እንደሚገኙ ነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ያስታወቁት፡፡

በተማሪዎች ዘንድ በተፈጠረው ስጋት ምክንያት ከአምስቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች መካከል በአንዱ ሙሉ በሙሉ፤ በሁለቱ ደግሞ ደግሞ በከፊል ትምህርት ተቋርጧል፡፡ የተፈጠረውን ስጋት በማስወገድ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ‹‹ተማሪዎች በውይይቱ ችግር ሊከሰት ይችላል ከሚል ስጋት የተነሳ ዩኒቨርሲቲውን ለቅቀው ለመውጣት ማሰባቸውን ነግረውናል›› ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት በተማሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ዩኒቨርሲቲው ተግቶ እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የመገናኛ ብዙኃን የአዘጋገብ ሁኔታ ለተቋማት ሠላም መደፍረስ የጎላ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች ችግሮች በተከሰቱ ጊዜ ሀገራዊ አንድነትን ከሚያመጡ ይልቅ ሕዝብን ቅራኔ ውስጥ የሚያስገባና ግጭት የሚቀሰቅስ መረጃ እያሠራጩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም ተማሪዎች ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለመውጣት የሚፈልጉት በሠላም መደፍረስ ምክንያት እንደሆነ አድርገው ሲያሰራጩ የነበሩ አንዳንድ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም እልቂት ሊያመጣ የሚችል መረጃ ያሰራጩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡም የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፤ ‹‹የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እርስ በእርሳቸው ተያያዥነት ያላቸው በመሆኑ አንዱ ተቋም ሲነካ ተፅዕኖው በሌሎቹም ላይ መንጸባረቁ አይቀርም›› በማለትም ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ በሁሉም ተቋማት ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲሰፍን በትጋት መሥራት እንደሚገባ ነው ዶክተር አስራት የተናገሩት፡፡ ለዚህም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ዶክተር አስራት ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም የነበራቸው መቀራረብ እና አብሮነት መቀነሱ ተገልጿል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው እንደተናገሩት የተማሪዎችን አንድነት እና ፍቅር ወደ ነበረበት በመመለስ ሠላማዊ የመማር ማስተማሩን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ አስተማማኝ የጥበቃ ሥራ በፀጥታ አካላት እያከናወነ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርም የተማሪዎች የስጋት ምንጭ ባይታወቅም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ችግሩ ጎልቶ እየተስተዋለ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሚኒስትሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክተር ደቻሳ ጉርሙ ትናንት በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ የሠላም መደፍረስ በሁለት ተማሪዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ከመድረሱ በቀር በዩኒቨርሲቲዎች አዲስ የተፈጠረ ክስተት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ችግሩ በተፈጠረባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ዳሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ተማሪዎችን ማረጋጋት አስፈላጊ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና የቦርድ ሰብሳቢዎች ከተማሪዎች እና ከየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከፀጥታ አካላት፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ተፈጥሮባቸው በነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች በተደረገ ውይይት ውጥረቱ እየረገበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ በቋሚነት ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በተማሪዎች ቅን ልቦና በመሆኑ የየዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የችግሮችን መንስኤ በመለየት መፍትሔያቸውን መፈለግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡(ምንጭ :-አማራ መገናኛ ብዙሀን)

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top