Connect with us

ዘረኝነትን የማሸነፍ ተስፋ – በዶ/ር ኤርሲዶ መጽሐፍ (ኑሮማፕ)

ዘረኝነትን የማሸነፍ ተስፋ - በዶ/ር ኤርሲዶ መጽሐፍ (ኑሮማፕ)
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ዘረኝነትን የማሸነፍ ተስፋ – በዶ/ር ኤርሲዶ መጽሐፍ (ኑሮማፕ)

ነውረኛውን ዘረኝነት ከስሩ ለመንቀል እንፈልጋለን? ወይስ ከዘግናኝ መዘዞቹ ለማምለጥ ብቻ?
አንድ ወንጀለኛ ወጣት፣ አንዱን ጎልማሳ ደበደበው (በዞን አንድ)፡፡ በሌላ ዞን ደግሞ፣ አንድ ወንጀለኛ ጎልማሳ፣ መንገድ ላይ ያጋጠመውን ወጣት ገደለ (በዞን ሁለት)፡፡

ተስፋ ባለው አገር ምን ይባላል? ‹‹ወንጀለኞቹ ግለሰቦች፣ በሕጋዊ ስርዓት ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ተዳኝተው፣ እንደየ ጥፋታቸው መጠን መቀጣት አለባቸው›› ይባላል፡፡

ተስፋ የሌለውና ዘረኝነትን መከላከል ያቃተው አገር ውስጥስ ምን ይወራል? በጅምላ፣ ‹‹የወጣቶች እና የጎልማሶች ግጭት በውይይትና በእርቅ ይፈታ›› ተብሎ ይወራል፡፡

የኢትዮጵያ አዝማሚያ ወደ የትኛው ያዘነብላል? የትኛውን ትመስላለች? ተስፋ ያላት ወይስ የሌላት አገር? ‹‹ኑሮማፕ›› ከተሰኘው የዶ/ር ኤርሲዶ መጽሐፍ ጥቂት ሀሳቦችን እንመልከት፡፡
አንዱ ትልቅ አሳ፣ ትንሹን አሳ ይበላዋል – ዋጥ ነው፡፡
ጥቂት ትንንሽ አሳዎች፣ ተረባርበው ትልቁን አሳ እየነከሱ ይቦጭቁታል፡፡

በአሳዎች አገር፣ ‹‹መብላላትኮ የሕይወት እውነታ ነው›› ይባላል፡፡ ደግሞም ያለምክንያት ዝም ተብሎ የተነገረ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዛሬ ዛሬ፣ በየእለቱ የምናየው ነገር ነው – ‹‹ትልቆ››፣ ‹‹ትንሾ›› ተባብለው በዘር መቧደንና መበላላት ተለምዷል! ይሄ ሆኗል አሳዛኝ ታሪካቸው! ይሄው ሆኗል የመከራ አኗኗራቸው!

በፊት በፊት ግን፣ ኑሮ እንዲህ አልነበረም፡፡ የድሮው ታሪክ የዚህ ተቃራኒ ነበር፡፡
የአንድነት መንፈስ – የብርሃን፣ የበረከት፣ የሕይወት መንፈስ ነው፡፡

ድሮ ድሮ፤…ምስጋናና አድናቆት፣ ለጥንቶቹ ቀደምት ጀግኖች ይሁንና፣ በእነሱ ጥረት የመጣው ታላቅ የስልጣኔ ለውጥ፣ መላውን ባሕር አዳርሶ፣ ከመሀል እስከ ዳር በመስፈኑ፣ አሳ አሳን የማይበላበት መልካም ዘመን ተጀመረ:: ከዚያ ወዲህ፣ ለብዙ ዘመናት ባህር ውስጥ፣ ዕፀዋት ተክለው እያበቀሉና እያጨዱ በስኬት ኖረዋል፡፡

በእርግጥ ስኬታቸው እውን የሆነው… እውቀትን በመሻት፣ አላማን በመምረጥና ብቃትን በመውደድ ነው፡፡ እነዚህን የብርሃን፣ የበረከትና የሕይወት መንገዶችን አዳምሮና አዋህዶ በቅጡ ባቀናበረ አቅጣጫ ስለተጓዙ ተሳካላቸው – የድሮ የጥንቱ የስልጣኔ አቅጣጫ ጠቀማቸው። እንዴት በሉ፡፡

… እውኑን ተፈጥሮ በአእምሮ እያስተዋሉና እያገናዘቡ እውቀትን መጨበጥ በመቻላቸው ነው የተሳካላቸው፡፡
‹‹ሕይወትን በየጊዜው ማበልፀግ›› የሚል የተባረከ አላማ በመያዝም፣ ብዙ ለማምረት ወስነው፣ በብርታት ተግተው ስለሰሩም ነው የተሳካላቸው፡፡ አዎ፤ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ አልሆነላቸው፡፡ አዎ፤ ብዙ ስህተት፣ ብዙ ፈተና፣ ብዙ ድካም አጋጥሟቸዋል። ነገር ግን በግልና በህብረት ባደረጉት ጥረት ውጤት ማግኘታቸው አልቀረም፡፡ ምግብ አምርተዋል፡፡ ኑሯቸው ተሻሽሏል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ እዚያው በዚያው ለምርታማነት የሚጠቅም ‹‹ትልቅ ሃብት›› እየገነቡ ነበር፡፡
ትልቁ ሀብት ምን መሳላችሁ? ‹‹ብቃት›› ልትሉት ትችላላችሁ፡፡

አንደኛ፣ በተሞክሮና በምርምር ስህተታቸው እየታረመ፣ አስተዋይነትና እውቀት እያደገ መጣ:: ሁለተኛ፣ ለስራ ሲተጉ፣ የሙያ ልምድ አዳበሩ፡፡

ሶስተኛ፣ የእውቀት፣ የአላማና የሙያ ፍቅር በውስጣቸው እየለመለመ፣ ጽናትና በራስ የመተማመን መንፈስን ገነቡ፡፡
ብቃታቸው ሲጨምር ይበልጥ ምርታማ እየሆኑ፣ ምርታማነትም ብቃታቸውን እያሳደገላቸው፣ የስኬት ምህዋር ፈጥረዋል:: እናም፣ ሕይወታቸው በየጊዜው እየበለፀገ በደስታ ይኖራሉ፡፡ ታዲያ የዘረኝነትና የመበላላት አስቀያሚ ታሪክ ከየት መጣ?
ለብዙ ዘመናት የስኬት መንገዳቸው አልተለወጠም፡፡ ሕይወት በየጊዜው የምትበለፅግ አስደሳች ነበረች፡፡ ፈጽሞ የምግብ ችግር አልነበረም፡፡ እንዲያውም በግል ትርፍ ስለሚያመርቱ፣ ለሌሎችም ጭምር የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡

የአንዱ አሳ ድንቅ ስኬት፣ ለሌሎች አሳዎች ፈርቀዳጅ ይሆንላቸዋል – ‹‹ለኑሯችን መልካም አማራጮችን የከፈተልን የተባረከ አሳ ነው›› እያሉ ያመሰግኑታል፡፡

(‹‹ራስ ወዳድ›› ብለው አያወግዙትም:: አይመቀኙትም፡፡ ‹‹የሱ ስኬት የሁላችንም ስኬት ነው›› ብለው ንብረቱ የጋርዮሽ እንዲሆን አይወርሱትም፡፡ አይዘርፉትም፡፡)

የአንዱ አሳ ድንቅ ብቃት፣ ለሌሎች አሳዎች አርአያ ይሆንላቸዋል – ‹‹የሕይወት ጣዕምን በእውን እያሳየ መንፈሳችንን የሚያነቃቃልን፣ የተከበረ የጀግንነት አርአያችን ነው›› ብለው ያድንቁታል፡፡

(ዘር አይቆጥሩም፡፡ እያንዳንዱን አሳ እንደየ ስኬቱ ማመስገን፣ እንደየ ጥፋቱ መዳኘት፣ እንደየ ብቃቱ ማድነቅ… እንዲህ ዓይነት የእውነት፣ የቅንነትና የፍትህ ባሕል ነበር፤ ‹‹የአንድነት›› መንፈስ ተብሎ የሚታሰበው፡፡)

የአንዱን አሳ ብቃት አድንቀው፣ በአርአያነቱም ተነቃቅተው፣ የየግል ብቃታቸውን ለመገንባት የሚተጉ ብዙ አሳዎች ይታዩ ነበር – በያኔው የስልጣኔ ዘመን፡፡

(የዘር ሐረግ እየቆጠሩ ወይም በብሄረሰብ (በብሔረ አሳ) ለመቧደን፣ ‹‹ዘመዳችን ነው››፣ ‹‹የሰፈራችን አሳ ነው›› በማለት፣ በሌላ አሳ የግል ብቃት ለመኩራት፣ የሌላ አሳ የግል ብቃትን ‹‹የጋራ›› ለማድረግ አይሞክሩም ነበር፡፡ የግል ጥፋትን በሌሎች ላይ የመጫንና የማጋራት ዘረኝነትም አልነበረም፡፡

አሁን አሁን ግን የስልጣኔ ኑሮ የለም፡፡ የድሮው የስልጣኔ ታሪክም ተረስቷል፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ፣ ሌላ አዲስ ለውጥ መጣ፡፡ የለውጡ አይነትና መዘዙ… ብዙ ነው፡፡ አንዱን ለውጥ እንይ፡፡) አሳዎች እንደ ልባቸው ተዘዋውረው የሚመገቡባቸው የጋራ የአትክልት ማሳዎች እንዲቋቋሙ ተደረገ፡፡ ቀስ በቀስም ብዙ አሳዎች ዕፀዋት መትከል እያቆሙ፣ የግል ማሳዎች እየጠፉና በጋራ ማሳዎች እየተተኩ መጡ፡፡ በቃ፣ የጋራ ማሳዎች ውስጥ ገብተው እየበሉ ሲዝናኑ ይውላሉ፡፡ ትምህርትም ሆነ ስራ፣ እየተረሳ ነው::

ግን ችግር የለም፡፡ ለጊዜው ምግብ ሞልቷል፡፡ የድሮው ስልጣኔ እየተሸረሸረ ቢሆንም፣ በአንድ ጀንበር አልጠፋም፡፡ በቀለምና በቅርፅ የሚለያዩ ብዙ አይነት አሳዎች፣ እንደ አንድ ትልቅ ደስተኛ ቤተሰብ ነበር የሚኖሩት፡፡ የቀለምም ሆነ የቅርፅ ልዩነት ወይም ሌላ ማንኛውም የዘር ልዩነት ለአሳዎች ትርጉም አልነበረውም፡፡ የድሮው የስልጣኔ ባህል እየሳሳ ቢሆንም፣ ገና አልከሰመም፡፡
ሕጻናት (ቄሳርና በርጊ) የትልቅና የትንሽ አሳ ዘር ተወላጆች ቢሆኑም፣ ከጓደኞቻቸው ጋር አብረው ነው የሚጫወቱት፡፡

አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸውም፣ በልጅነታቸው ዘወትር አብረው ነበር የሚጫወቱት፤ ወደ ትምህርት ቤትም የሚሄዱት፡፡
የዛሬ ሕጻናት፤ እነ ቄሳርና በርጊ ግን፣ እድሜያቸው ከደረሰ በኋላም፣ ትምህርት ቤት ሄደው እውቀትን አይማሩም፡፡ የጋራ ማሳ ውስጥ ሲበሉና ሲጫወቱ ይውላሉ፡፡ እድሜያቸው ከፍ ሲልም እየተጋቡ ይወልዳሉ፤ ይዋለዳሉ፡፡

አሳዎች እውቀትን መማር አቁመዋል:: መዋለድ ግን አላቆሙም፡፡ ቁጥር ማባዛት አይችሉም፡፡ መባዛት ግን አላቃታቸውም:: ማምረት መስራት አቁመዋል፡፡ መብላት ግን የግድ ነው፡፡

ድሮ ድሮ፣ አሰላስሎ ማገናዘብ፣ በአላማ ወስኖ መስራት፣ አምርቶ መብላት… ለየብቻ ተነጣጥለው የሚታዩ አልነበሩም፤ እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው፡፡

ዛሬ ግን፤ ብዙዎቹ አሳዎች፣ አንድ ነገር ብቻ (መብላት ብቻ) ነው በቁንጽል የሚታያቸው:: ‹‹የቁንጽል እስረኛ›› ሆነዋል፡፡ ሌላው ሌላው ሁሉ አይታያቸውም፤ እየሸመጠጡ መብላት ብቻ ሆኗል፡፡ ምግብ የጠፋ ጊዜስ?

ወይስ፣ ዛሬውኑ አሁኑኑ መብላታቸው ብቻ፣ ለዚህች ቅፅበት መጥገባቸው ብቻ ነው የሚታያቸው? ‹‹የቅፅበት እስረኛ›› ሆነዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ትናንትንና ነገን አሻግረው አያዩም፡፡

ለዛሬ መጥገብን ብቻ እያዩ፣ የተመናመነውን ተክል በሽሚያ ቀድሞ ለመብላት ይራኮታሉ፡፡
የአሳዎቹ ቁጥር ደግሞ፣ እጥፍ ድርብ እየሆነ ነው፡፡
በዚህ መሀል፣ የዘረኝነት ቅስቀሳ ተጨመረበት፡፡
አብዛኛው የዳር ተመልካች፣ ሲሆን፣ ጥቂት ዘረኞች ገነኑ፡፡

የቄሳር አያት፣ ‹‹ትንንሾቹ አሳዎች በዝተው ተባዝተውና ከድርሻቸው በላይ ምግብ እየበሉ ነው›› አለ – ትልልቅ አሳዎችን ሰብስቦ ለመቀስቀስና ለማቧደን፡፡

የበርጊ አያት ደግሞ፣ ትንንሽ አሳዎችን ለማቧደን፣ ‹‹ትላልቆቹ አሳዎች እያንዳንዳቸው ብዙ ምግብ ይጠቀማሉ›› ብሎ ተናገረ፡፡
ቢሆንም፤ አብዛኛው አሳ በዘር አልተቧደነም:: ነገር ግን ዘረኝነትን መከላከል አቃተው፡፡ በአንድ በኩል ‹‹ትንሾ››፣ በሌላ በኩል ‹‹ትልቆ›› በሚል የተቧደኑ ጥቂት ነውጠኛ አሳዎች፣ አንዱ ሌላውን በመወንጀልና በማውገዝ መግነን ጀመሩ፡፡
አብዛኛው አሳ በዝምታ ይታዘባል፡፡

በሁለት ጎራ የተቧደኑት ጥቂት ነውጠኛ አሳዎች ግን፣ አገር ባሕሩን በቅስቀሳ እየናጡት ነው፡፡
የአንዱ ቡድን ነውጠኛ መሪ፣ ከነጭፍራዎቹ ወቀሳ ሲሰነዝር፣ በምላሹ የሌላኛው ቡድን አውራም፣ ከነተከታዮቹ ውንጀላ ይወረውራል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው ነውጠኛ መሪ፣ በመረረ ውንጀላ አፀፋ ይመልሳል፡፡
የመልስ መልስ፣ የአፀፋ አፀፋ እያሉ… መናቆርና መተጋተግ ነው፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ፣ አሳዎች ደስተኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ከስጋትና ከችግር ነፃ የነበረው የአሳዎች ኑሮ፣ ‹‹በአንዴ›› ተመሳቀለ፡፡ ‹‹በአንዴ›› የተመሳቀለ ይመስላል እንጂ፣ ከቀን ቀን ከሳምንት ሳምንት ችግር እየተባባሰና እየተበራከተ ቆይቶ ነው ድንገት ገሃድ የወጣው፡፡ አሁን አሳዎቹ ያለ ስጋት በፍቅርና በነፃነት መንቀሳቀስ አቁመዋል። በቅርፅና በቀለም (በዘር) የተለየ አሳ ሲያጋጥማቸው፣ በስጋት የሚመለከቱና የሚጠረጥሩ ሆነዋል – ብዙዎቹ አሳዎች፡፡

የባሰባቸው ደግሞ አሉ! ቢተዋወቁም ባይተዋወቁም፣ በዘር የተለየ አሳ ሲያጋጥማቸው፣ ምንም ሆነ ምን፣ ‹‹ጠላታችን ነው›› ወይም ‹‹የጠላት ወገን ነው›› እያሉ በጭፍን ይፈርጃሉ:: በዘር የሚመሳሰል አሳ ሲያገኙ ደግሞ፣ ጥሩም ይሁን ክፉ፣ ‹‹ወዳጃችን ነው››፣ ‹‹የኛ ዘመድ ነው››፣ ‹‹የኛ ወገን ነው›› ይሉታል፡፡

ይሄ፤ በአሳዎች ዘንድ እየገነነ የመጣና ቀድሞ ያልነበረ፣ የጭፍንነት፣ የጥፋትና የክፋት አስተሳሰብ ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ተስፋፍቶ ልማድ ሆነ፡፡ ቀጥሎም ባህል ሆኖ አረፈው፡፡ በመጨረሻም የተፈጥሮ ሕግ እየመሰለ መጣ፡፡

አንዳንድ ነውጠኛ ትላልቅ አሳዎች፤ ትንንሽ አሳዎችን ለማጥቃት ወሰኑ፡፡ የአካላቸውን ግዝፈትና የጡንቻቸውን እብጠት በመጠቀም፤ ትንንሽ አሳዎችን አስፈራሯቸው፡፡ ከዚያስ ምን ተብሎ ተወራ? ‹‹እከሌ የሚባል አሳ ጥፋት ፈፀመ›› ተብሎ አልተወራም፡፡ በጅምላ፣ ‹‹ትልልቅ አሳዎች ወጉን›› ተባለ፡፡

የተወሰኑ ነውጠኛ ትንንሽ አሳዎች፣ በንዴትና በእልህ፣ አፀፋ ለመመለስ ተሰባስበው፤ ጥምረት ፈጠሩ፡፡ በግዙፍነቱና በጡንቻው ተመክቶ የነቆራቸውን አሳ ለይተው ባያውቁትም፣ መንገድ ላይ ያገኙትን ማንኛውንም ትልቅ አሳ ለማጥቃትና ለመበቀል ሲወስኑ፣ እንደሚሳካላቸው አልተጠራጠሩም፡፡ ‹‹ብዛታችን መመኪያችን ነው›› የሚል መፈክር ይዘዋል፡፡

አድፍጠው ሲጠብቁ የነበሩ ጥቂት ትንንሽ አሳዎች፣ ወጥመድ ውስጥ የገባው ትልቅ አሳ ላይ ተረባርበው ሰፈሩበት፡፡ እየተጯጯሁ ከአቅጣጫው ይቦጫጭቁታል። አሳው ትልቅ መሆኑ ብቻ በቂ ነው፡፡ ፀባዩ ጥሩም ይሁን መጥፎ ልዩነት የለውም፡፡ ጠላት ነው ተብሎ በጭፍን ተፈርጇል፡፡ አንደኛውን ገድለው ሲጨርሱ እንደገና ሌላ ትልቅ አሳ ወጥመድ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ተረባርበው እየነከሱ ይገድሉታል፡፡
ገደሏቸው!?

ወሬው በአጭር ጊዜ አገር ባህሩን አዳረሰው:: ወሬውን የሰሙ አንዳንድ ነውጠኛ ትልልቅ አሳዎች፣ ለቅስቀሳ የሚመች እድል አገኙ፡፡ ‹‹ወንጀሉን የፈፀሙት እነማን ናቸው?›› ብለው ለማጣራት አልሞከሩም። በጅምላ፣ ትንንሽ አሳዎች ላይ የጥላቻ ቅስቀሳና የጥቃት ዘመቻ አቀጣጠሉ፡፡ ከእንግዲህ ክንፋቸውን አጣጥፈው እንደማይቀመጡም ዝተዋል፡፡

‹‹ትንንሾቹ አሳዎች እንዲህ ሲያሸብሩን በዝምታ አናልፍም፡፡ በሽብር ጥቃት እየሰጋን አንኖርም” አሉ ዘረኝነትን የሚያራግቡ ጥቂት ነውጠኛ ትልልቅ አሳዎች፡፡

አብዛኛው አሳ፣ ከዳር ሆኖ ይመለከታል፡፡ በዘር ተቧድነው ባህር ምድሩን ለሚያናውጡ ተቀናቃኝ ጎራዎች ተመቻቸው፡፡ እንዴት?
“እኔ የሌለው እኛ” – በጣም አደገኛ የዘረኝነት መሳሪያ ነው፡፡
በብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት ወይም በዘር፣ በሃይማኖት ተከታይነት ወይም በሰፈር ነዋሪነት እየተቧደነ፣ ፀብና ግጭት የሚፈጥር ሰው፣ ሁለት መንገዶችን ይጠቀማል፡፡

ቱጃር ባለሀብት፤ ትልቅ ባለሥልጣን፤ ተሸላሚ ምሁር፤ ጥበበኛ ባለሙያ፤ ሻምፒዮና አትሌት፤ ቆንጆ ወይዘሪት፤ ዝነኛ ዘፋኝ፤ ሲያይ… ‹‹ዘመዳችን ነው፤ የሰፈራችን ልጅ ነች፤ የኛ ብሄር ተወላጅ ነው፤ የኛ ሃይማኖት ተከታይ ነች…›› በማለት ይናገራል፡፡ ስኬት በዘርና በዝምድና የሚተላለፍ ይመስል፡፡ የሌሎች ሰዎችን ስኬት ለመጋራት፤ ‹‹ስኬታቸው ውስጥ እኔም አለሁበት፤ የጋራችን ነው›› ለማለት ነው ፍላጎቱ:: የሰዎችን ስኬትና ጥንካሬ ሲያይ፣ ‹‹የኔም ነው፤ አለሁበት›› ይላል፡፡

የራሱ ጥፋትና ድክመት ሲኖርስ? ‹‹የናንተም ነው፤ አላችሁበት›› ይላል፡፡ ብዙውን ጊዜ የቡድን ፀብ እንደዚህ ነው የሚፈጠረው፡፡
በግል ተጣልቶ፤ ተደባድቦ፤ ንብረት ሰብሮ ሲያበቃ፤ ሃላፊነቱን በግል ለመሸከም፣ መዘዙን በግል ለመወጣት አይፈልግም። ‹‹የእገሌ ብሄር ተወላጅ ነኝ፤ የእንትን ሃይማኖት ተከታይ ነኝ፤ እናንተም አላችሁበት፤ የጋራችን ነው›› በማለት የራሱን ጥፋት በደፈናው የጋራ እንዲሆን ያደርጋል።

አስር ሆነው ከተፈነካከቱና ከተወጋጉ በኋላ፣ ወይም መንገደኞችን ከዘረፉና ካቆሰሉ በኋላ፣ ጥፋታቸውን በየራሳቸው መወጣት አይፈልጉም፡፡ ‹‹የእገሌ ብሄረሰብ፤ የእንትን ሃይማኖት ነን፡፡ እናንተም አላችሁበት፤ የጋራችን ነው›› ይላሉ፡፡

ይህንን በዘር የማቧደንና በመንጋ የማንጋጋት አጥፊ መንገድ ካልተቃወምንና ካላስተካከልን፤ የክፋት ሰለባ መሆናችን አይቀርም፡፡
ዘረኝነት ወይም የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አንድ ምሳሌ ቢሆንም፤ በሃይማኖት ተከታይነት ማቧደንና ማንኛውም አይነት ሃይማኖታዊ ፖለቲካም የዚያኑ ያህል አገርን የሚያጠፋ በሽታ ነው፡፡ ለምን?

አይተነው በማናውቀው አንድ ሰው ጥፋት የተነሳ፣ በሌለንበትና ባልነበርንበት ክስተት፣ የጥፋቱ ተጋሪ እና ተጠያቂ እንድንሆን እንገደዳለን፡፡ ወንጀለኛው፤ ‹‹እንደናንተ የእገሌ ብሄር ተወላጅ ነኝ፤ እንደናንተ የእንትን ሃይማኖት አባል ነኝ›› በማለት የግል ጥፋቱን ‹‹በጋራ›› እንድንሸከምለት ነዋ በዘር የሚያቧድነን:: ለዚህም ነው፤ ‹‹እኔ የሌለው እኛ አደገኛ!›› የሚሆነው፡፡
[ኑሮማፕ የተሰኘው መጽሐፍ በዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ፣ ከዮሐንስ ሰ. ጋር ተዘጋጅቶ የቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡] ምንጭ:-አድስ አድማስ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top