Connect with us

ትምህርት ሚኒስቴር በአንዳንድ ዩኒቨርሰቲዎች ትምህርት መቋረጡን አረጋገጠ

ትምህርት ሚኒስቴር በአንዳንድ ዩኒቨርሰቲዎች ትምህርት መቋረጡን አረጋገጠ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ትምህርት ሚኒስቴር በአንዳንድ ዩኒቨርሰቲዎች ትምህርት መቋረጡን አረጋገጠ

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአንዳንድ ዩኒቨርሰቲዎች ትምህርት መቋረጡን አረጋገጠ

– የአስተዳደር አካላት እና የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ከተማሪዎች ጋር እየመከሩ ነው

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት በወልድያ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን እና በሌሎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛ ትምህርት ተቋረጠ፡፡

የወልድያውን ክስተት ተከትሎም በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የችግር ምልክቶች መታየታቸውን እና ተማሪዎች እርስበርስ የተገጩበት እና ጉዳት የደረሰባቸው ሁኔታ መፈጠሩን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በዚህም ክስተት ምክንያት በወልድያ፣ መቱ፣ ጅማ፣ ኦዳ ቡልቱም እና መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ተቋርጧል ነው ያሉት።

ተማሪዎቹ አደጋ ሊመጣ ይችላል በሚል በትውልድ አካባቢያቸው ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ሄደው መማር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ገልጸዋል።

በነዚህ ዩኒቨርስቲዎች መማር ማስተማር አይኑር እንጂ በተማሪዎችና በየአካባቢው መስተደዳር እንዲሁም በመምህራን መካከል ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ችግሩ እንዲባባስ እና ተማሪዎች እንዲረበሹ የሚያደርጉ፣ ተማሪ የሚመስሉ ግን የተማሪ ሥራ የማይሰሩ አካላት መኖራቸውን ገልጸው፣ ከትናንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ የፌደራልና የክልል ፀጥታ መዋቅር እነዚህን አካላት የመለየት እና በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እንደዚህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ በማህበራዊ ሚዲያዎች በአመዛኙ የተዛቡ መረጃዎች እየተሰራጩ በመሆኑ ዋና የሚባሉት የመገናኛ ብዙኃን ይህንን በመረዳት በኃላፊነት መሥራት እና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ተማሪዎች ከዶርም ውጪ እንዲያድሩ፣ እንዳይረጋጉ፣ በሃይማኖት ተቋማት አካባቢዎች እንዲሰባሰቡ፣ ምግብ እንዳይበሉ፣ ምግብ እንዲደፉ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር እንዲጋጩ የሚቀሰቅሱ አካላት እንዳሉ እና እነዚህን አካላት በመለየት በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩንም አክለዋል።

የተማሪ መታወቂያ እየሰረቁ ተማሪ መስለው ወደ ግቢ የሚመጡ፣ የተማሪ መታወቂያ ፎርጅድ አሰርተው የሚሰጡ፣ በገንዘብ የሚደግፉ፣ ተማሪዎችን እንዳይረጋጉ በማድረግ ኅብረተሰቡን ወደስሜት የሚወስዱ እና ሁከት ውስጥ እንዲገባ የሚያድርጉ አካላት እጆቻቸውን ከተማሪዎች ላይ እንዲያነሱም አሳስበዋል።

መንግሥት በዩኒቨርስቲዎች ያለውን አሁናዊ ሁኔታ ለማረጋጋት እና ሕግን ለማስከበር በቂ ዝግጅት ማድረጉን እና ኃይል ማሰማራቱንም ገልጸዋል።

ትምህርት በቆመባቸው ዩኒቨርስቲዎች የፀጥታ መዋቅሩን ጨምሮ የአካባቢው አስተዳደር አካላት እና የዩኒቨርስቲው አመራሮች ከተማሪዎች ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ተማሪዎች በስነልቦና እንዲረጋጉም እንደየእምነቶቻቸው የሃይማኖት አባቶች ተገኝተው እየመከሩ እና እየገሰፁ ወደትምህርታቸው እንዲመለሱ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በየአካባቢያችን ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ይቀበሉናል ብለው የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የሚያታልሉ እና ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጥለው እንዲሄዱ የሚያነሳሱ አካላት አሉ፤ ይህ ግን ፈፅሞ ሊሆን ስለማይችል በተቋሞቻቸው ተረጋግተው ያለባቸው ችግሮች ተፈተውላቸው መማር ማስተማሩ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብለዋል።

የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ሥራ ላይ ያሉትን የክልል እና የፌደራል መንግስት የፀጥታ መዋቅሮችን አመስግነው፣ ይህ ጉዳይ እንዲፈጠርና እንዲባባስ የሚሰሩ አካላት ከዚህ በላይ አደጋ አድርሰው ኢትዮጵያውያን እናቶች እንዲያዝኑ ለማድረግ የሰሩት ስራ ያልተሳካው በነሱ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሚዲያ አካላትም ትክክለኛውን፣ መሬት ላይ ያለውን እውነት ከዩኒቨርስቲዎች እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ በመውሰድ ወላጆችንም ተማሪዎችንም የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ አደራ ብለዋል፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top