ፓለቲካ
የ‹መደመር› ፓስፖርት ኢትዮጵያዊ ነው?
የ‹መደመር› ፓስፖርት ኢትዮጵያዊ ነው?
(ያየሰው ሽመልስ በፍትሕ መጽሔት ላይ እንደፃፈው)
ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ መጽሐፋቸውን በመንግሥት መገናኛብዙሃን በቀጥታ ስርጭት፣በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ ከተሞች፣በመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲመረቅ ያደረጉት ልክ የዛሬ ወር ነበር፡፡በመጽሐፋቸው ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግርም ‹‹ከቻላችሁ ማባዛት የሚል መጽሐፍ ፃፉ፤የኔን መጽሐፍም ተቹት› ብለው ተናግረዋል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡በአንድ በኩል መሪ መጽሐፍ ሲጽፍ አስደሳች ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ‹ተቹኝ› ብሎ ጥሪ ማቅረብ ጠቃሚ ነው፡፡ሲቀጥልም ከዚህ ከተካረረ አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ወደ ሀሳብ ነክ ጉዳይ እንድንገባ የሚያደርግ በመሆኑ አንብቦ መወያየቱ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡
ይህ የእኔ ሒስም አምዱን የሚመስል እንዲሆን ይሞከራል፡፡በመደመር መጽሐፍ ላይ የተካተቱ የርዕዮትዓለማዊ የትመጣነትን መመርመርና የውጭ ግንኙነትን በሚመለከት የቀረበውን ምዕራፍ መመልከት ላይ ያተኩራል፡፡
ርዕዮተዓለምና መጽሐፉ
ፀሐፊው ለኢትዮጵያ አንድነት ደግ ልብ እንዳላቸው ያስታውቃል፡፡ትውፊታዊ የሆነ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ቅልጥ ያለ የሥልጣን ፍላጎት (ሥልጣንን መመኘት በዘመናዊ ዓለም እጅግ ተገቢ ጉዳይ መሆኑን ያስተውሏል) እንዳላቸው ያሳብቃል፡፡በተለይ ደግሞ ወታደራዊ ሕይወታቸው ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልፀዋል፡፡ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ጥቅም ላይ ውለው ‹አገር ያበላሹ› ርዕዮተዓለሞች ተችተዋል፡፡
‹‹ከባሕር ማዶ የጎረፉትን ሐሳቦች በቀጥታ አምጥተን ሕዝቡን በመጋት አገራዊ ስካር ውስጥ ገባን፡፡ዞር ብለን ስናየው ትርጉም በማይሰጡና ፈገግ በሚያደርጉ ጉዳዮች እርስበርስ ስንራኮትና ስንጋደል አሳለፍን፣መድሀኒት ይሆናል ብለን ከውጭ የወሰድነው ርዕዮተዓለም እርሱ ራሱ የሌላ በሽታ ምክንያት ሆነ፡፡ርዕዮተዓለሞችን በእኛ ሀገር ሁኔታ ለመተርጎም የተደረገው ጥረት፣በእኛ ልክ ያልተገዛን ጫማ የመጫማት ያክል ነበር›› እያሉ ከተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ቀድሞ አለቆቻቸው ዘመን ድረስ ያለውን ዘመን ያብጠለጥላሉ፡፡እንዲህ ያሉ የርዕዮተዓለም ጉዳዮችን በሃያ ሶስት ገፆች (13-34) ጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመጤ ርዕዮቶች፣በማይገባት (ገ ጠብቃም ላልታም ትነበብ) ርዕዮተ ዓለም ስትመራ መኖሯን ይኮንናሉ፡፡በርግጥ የመደመር ደራሲ እንዳሉት የኢትዮጵያ ርዕዮተዓለሞች መጤ ናቸው? እንዴት? በመጽሐፋቸው ላይ ‹‹ሀገር በቀል እሳቤዎች ከግምት ውስጥ መግባት ነበረባቸው›› የሚሉት ሀሳብ እስካሁን አልተሞከረም? ወዘተ የሚሉትን ጉዳዮች እናጠይቅ፡፡
የርዕዮቶች ተቃርኖ
የመደመር ደራሲ ‹‹በርዕዮተዓለም ውይይቶች ውስጥ የሊብራሊዝምና ሶሻሊዝም ተቃርኖ ጎልቶ የሚነሳ ጉዳይ ነው›› ብለው በመደምደም ይጀምራሉ፡፡በርግጥ ይህ ስህተተኛ ማጠቃለያ ነው፡፡ በፖለቲካል-ኢኮኖሚ አካዴሚ ውስጥ በርካታ ርዕዮቶች መከራከሪያ ናቸው፡፡
በቅድሚያ ግን ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ምንድን ነው የሚለውን እንመልከት፡፡ይህ ጽንሰ ሐሣብ ወደ አካዳሚ ውስጥ ገብቶ መጠናት የጀመረው ከ1996/97 (እ.ኤ.አ) ወዲህ ነው፡፡በታይላንድ የሚኖሩ ኢንቨስተሮችና የምንዛሬ ነጋዴዎች፣ትርፋማነታቸው እያሽቆለቆለ ሲመጣና በሀብታቸው የደህንነት ስጋት ሲገጥማቸው ይዘውት የመጡትን ሀብት ጠራርገው ወጡ፡፡በመቀጠል በተለምዶ ‹‹የኤስያ የኢኮኖሚ ቀውስ›› የሚባለው አደጋ ተከሰተ፡፡ከዚያም ቀደም ብሎ በመካከለኛው ምሥራቅ (በሌላኛው የኤስያ ክፍል) በአረብ እስራኤል ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መጠን አሻቀበ፡፡ይህ ደግሞ በብዙ አገሮች የፖለቲካ አመጽ ግብዓት ሆነ፡፡በኢትዮጵያም በ1966 በተካሄደው አዝጋሚ አብዮት (ቃሉ የጆን ማርካኪስ ነው) ላይ የታክሲ ሾፌሮች የተሳተፉት በዚሁ ጦርነት ምክንያት በነዳጅ ዋጋ ላይ 10 ሳንቲም ተጨምሮ ነው፡፡
በነዚህ ሁለት ተመጋጋቢ ክስተቶች የአካዳሚክ ሰዎች ጉዳዮን ወደ ሳይንሳዊ ትንተና አስገቡት፡፡GLOBAL
POLITICAL ECONOMY EVOLUTION & DYNAMICS የሚል መጽሐፍ ያስነበቡት ሮበርትና ዊልያምስ ‹‹ይህንን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ወደ አካዳሚ ውስጥ ገባ፤ከዚያም ፖለቲካል ኢኮኖሚ አንዱ በአንዱ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ የሚመረምር የትምህርት መስክ ሆነ›› ይላሉ፡፡በወቅቱም ቀውሱ የተከሰተው በመንግሥት የፖሊሲ ችግርና በራሱ በገበያ ኢኮኖሚ ስህተት ነው የሚሉ ልሂቃን ተከራከሩ፡፡ጉዳዩ ከሊብራሊዝም፣መርካንታሊዝምና ከሌሎች ኢዝሞች አንፃር መተንተን ጀመረ፡፡የመተንተኛ ዲሲፒሊኑ ‹ፖለቲካል ኢኮኖሚ› ተባለ፡፡
በሚላናክና ፋይን የተፃፈው‹‹From political economics to Economics›› መጽሐፍ ደግሞ ‹‹በቤተሰብ፣በሕብረተሰብ ክፍሎችና በአገራት መካከል የሚታየውን የኢኮኖሚ ፣የኅብረተሰብ፣የፖለቲካና የባሕል ግንኙነት የሚተንትን ሳይንስ›› እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡
የመደመር ደራሲ ትኩረታቸውን ነባሩን የኢትዮጵያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መተቸት ላይ ቢያደርጉም ከላይ ስለተጠቀሰው ጽንሰ-ሐሳብ ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡ለዚያም ይመስላል ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን እያምታቱ የፃፉትና ዓለም እየተከራከረ ያለው በሶሻሊዝምና ሊብራሊዝም ላይ አተኩሮ እንደሆነ የገለፁት፡፡ይሁን እንጂ አሁን ዓለም ላይ ገዥ ሆነው የቀረቡት ሃልዮቶች ሶሻል ዴሞክራሲ፣ኒዮ-ሊብራሊዝም፣ልማታዊ መንግሥትና በጣም በጥቂት አገሮች ሶሻሊዝም ናቸው፡፡በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ የዓለም አገራት በሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮት የሚመሩ ናቸው፡፡በብዙ አገሮች (ኢትዮጵያን ጨምሮ) ሶሻል ዴሞክራሲ ያዋጣል ብለው ለሥልጣን እየታገሉ ያሉ ፓርቲዎች አሉ፡፡በፓርላማዎችም ውስጥ መቀመጫ አላቸው፡፡
ሁሉም የዓለም አገራት በሚባል ደረጃ ልማታዊ የመንግሥትን ሞዴል (በኢኮኖሚው ውስጥ መንግሥት ጣልቃ ይግባ የሚል ርዕዮት ነው) በተለያየ ደረጃ እየተገበሩት ነው፡፡ሌላው ቀርቶ አሜሪካ (በተለይ ከ2008 እ.ኤ.አ ወዲህ) ይህንን ሞዴል ገቢራዊ ከማድረግ ውጭ አማራጭ እንደሌለ ገብቷት ቀጥላበታለች፡፡ሶሻሊስት መንግሥታት ደግሞ ከጣት ቁጥር አያልፉም፡፡
አብዛኞቹ የዓለም አገራት ፖለቲካዊ ሊብራሊዝምን ተግብረው፣ኢኮኖሚያቸውን በካፒታሊዝም ውስጥ እንዲያልፍ እያደረጉ ናቸው፡፡ሊብራሊዝም የፖለቲካ ቲዎሪ ሲሆን ሰዎች ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሊኖራቸው ስለሚገባ ነፃነት የሚተነትን ነው፡፡ ነፃነት ሲባል የማመን፣የመናገር፣የመፃፍ፣የመደራጀት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ካፒታሊዝም ደግሞ በነፃ ገበያ ውስጥ ሰዎችና የግል ቢዝነስ ቡድኖች ስለሚያፈሩት ሀብት የሚከራከር ነው፡፡ለዚህ ሥርዓት ደግሞ ግለሰቦችና ገበያ ባለሚና ናቸው፡፡
መደመር ግራ የተጋባው እዚህ ጋር ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትንታኔውን ከኢኮኖሚው ሃልዮት ጋር ያምታታዋል፡፡‹‹የሊብራል ፍልስፍና ቀደምት ጠንሳሾች ለሰው ልጆች ግለሰባዊ ነፃነት ቅድሚያ የሚሰጡና የሰውን ልጅን የማያቋረጥ የፍጆታ ጥም በማርካት ላይ ያተኮሩ›› ነበሩ ይልና ያደበላልቃል፡፡
በዚሁ ገጽ ላይ የቀረበው ሌላ የተምታታ ነገር ደግሞ ‹‹ዙፋን የተቆናጠጡ ኃይሎች የጦር ኃይላቸውን መከታ በማድረግ የዜጎችን ሀብት የሚያጋብሱና የዜጎችን የብልጽግና ጥረት የሚገድቡ በመሆናቸው›› ሊብራሊዝም መተግበር እንደጀመረ የሚገልፀው ነው፡፡ይሁን እንጂ ይህ ትርጓሜ የሚሠራው ለሊብራሊዝም ሳይሆን ለሪያሊዝም ነው፡፡‹ጠብመንጃ የሁሉም ነገር ማሸነፊያ ነው› ብለው የሚያምኑት ሪያሊስቶች ናቸው፡፡
መደመር ርዕዮተዓለማዊ ጥራት የሌለው ድርሳን የሚያደርገው ሌላው አጋጣሚ ደግሞ ሶሻሊዝምንና ማርክሲዝምን እያፈራረቀ ለአንድ ዓይነት ትርጓሜ መጠቀሙ ነው፡፡ሆኖም ሁለቱ የተለያዩ ኢዝሞች ናቸው፡፡ሶሻሊዝም በማኅበራዊ ጋርዮሽ የሚመጣን ሥርዓት ተከትሎ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥልጣንን ለታችኛው መደብ የሚያጎናጽፍ ትንተና ነው፡፡ለዚህም የግል ባለሀብት የሚመሠርታቸው ኢንተርፕራይዞች አላስፈላጊ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ዋነኛው ሀብት በመንግሥት አከፋፋይነት የሚመራ ነው ብሎም ያምናል፡፡
ማርክሲዝም ደግሞ ለኅብረተሰብአዊ ለውጥና አብዮታዊ ሽግግር ሳይንሳዊ ትንተናን ያስቀመጠ፣በዋናነት የከተማ ወዛደሮች የሥልጣን ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ የቀመረ ጽንሰ-ሐሳብ ነው፡፡የመደመር ደራሲ ግን ሁለቱን አንድ አድርገው የተረዷቸው ይመስላል፡፡ይህም ሳያንስ የተማሪዎች ንቅናቄን፣‹‹ችግራችን ምን እንደሆነ ያልተረዳ›› እንደሆነ በመጥቀስ፣‹‹የሀገራችን ወጣት ለአፍ ማሟሻ ያህል የሶሻሊዝም ዳንኪራ ሲመታ›› እንደኖረ ገልፀዋል፡፡እዚህ ጋር የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን Socialist Utopia መጽሐፍ ዋቢ በማድረግ፣የተማሪዎቹ ንቅናቄ ተራ ልፈፋና ‹ዳንኪራ መምታት› እንዳልሆነ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ተማሪዎቹ ይዘዋቸው የተነሱት ጥያቄዎች፣መሬት ላራሹ፣የብሔሮች እኩልነትና ሕዝባዊ መንግሥት ናቸው፡፡እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ በአግባቡ የተተነተኑ፣ ከኢትዮጵያ አንፃር ተለይተው የቀረቡ ነበሩ፡፡በዚህም በመንግሥት ላይ በማመጽና በመዝመት ቢያንስ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደርን የመሬቱ ባለቤት፣ብሔሮችን ደግሞ ባለመብት አድርጓል፡፡እዚህ ጋር ያለው የደራሲው ደፋር ድምዳሜም በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሠረተ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
የተማሪዎቹን ጥያቄ አገራዊ ሁኔታን ያላገናዘበና ‹‹የሕዝባችንን ችግር ከፈረንጆቹ ማሕቀፎች ወጥተን ማሰላሰል አልቻለም›› የሚለው ‹መደመር›፣ እንደገና ይቆይና ‹‹ፌደራላዊ ሥርዓታችን የሀገራችንን ብሔረሰቦች የራስን ቋንቋና ባህል የመጠቀምና የማሳደግ መብታቸው ተከብሯል›› ይላል፡፡ይህ ግን ‹አገራዊ ሁኔታን አላገናዘቡም› ተብለው በመጽሐፉ የተተቹት ተማሪዎች ይጠይቁት የነበረ ጥያቄ ነው፡፡
እንዲህ ባሉ አለመጣጣሞች ውስጥ የተፃፈውና ስለ ርዕዮቶች ያልጠሩና የሚጣረሱ ሀሳቦችን ያነሳው ምዕራፍ ሁለት ቀጣይ ትኩረቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡አብዮታዊ ዴሞክራሲንም እንዲሁ ‹የተገለበጠ› ፈረንጅ ወለድ ርዕዮት መሆኑን ያነሳል-መጽሐፉ፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲና የመደመር ‹ቀመር›
በመጽሐፍ ምረቃው ዕለት ካርል ማርክስን (በእርሳቸው አጠራር ማርክ) እና ቪላዲሚር ሌኒን ‹ደንቆሮ› ሲሉ ያጣጣሉት የመደመር ፀሐፊ፣ መጽሐፋቸው ዳስ ካፒታልንም ሆነ በርካታ የሌኒን ትንተናዎችን የሚያስንቅ እንደሚሆን ቢገመት የሚጠበቅ ነው፡፡ዓለምን ለሁለት ከፍለው ዛሬ ድረስ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አድሏዊነት፣በብሔሮች ነፃነትና በማንነት ፖለቲካ ላይ የማይሞት አጀንዳንና ትንተናን ትተው የሄዱ አሳቢያንን ካራከሱ፣የተሻለና የበለጠ ይዘት ያለው መጽሐፍ እንዲጠበቅባቸው ያደርጋል፡፡አብዮታዊ ዴሞክራሲን የፈጠረው ሌኒን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ይሁን እንጂ ስህተት ነው፡፡
ለጊዜው ድርሰታቸውን በነ ዳስ ካፒታል ደረጃ መተቸቱን እናቆየው፡፡ትኩረታችንን አገር በቀል ነው ያሉትን መደመርን እናድርግ፡፡ከዚያ በፊት ደግሞ ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመጽሐፉ ላይ የተተረከውን እንመልከተው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ‹ከውጭ የተገለበጠ› መሆኑን ያነሱና እንደገና ‹‹አብዛኛው ሕዝቧ በግብርና ለሚተዳደረው ኢትዮጵያ፣አርሶ አደርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ መሥመር መሆኑ ጠንካራ ጎኑ ነው›› ይላሉ፡፡ይሁን እንጂ ከአገራዊ ሁኔታ አንፃር ያልተቃኘ ብለው ሲከስሱት ቆይተው ‹አብዛኛውን ሕዝብ› ማዕከል ማድረጉን በመጥቀስ ሀገራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ እንደሆነ ቋንቋውን ቀይረው ይጽፉልናል፡፡ርዕዮቱ በኢትዮጵያ ህልው የሆነውም ከደርግ ውድቀት በኋላ እንደሆነ ያስነብቡናል፡፡መደመርን ደግሞ ‹‹ከችግር ትንተና አንፃር አገር በቀል፣ለችግር መፍትሔ ደግሞ ከሀገር ውስጥም ከውጭም የሚወስድ ነው›› ይላሉ፡፡እንግዲህ በዚህ ትርጓሜ አንድን ርዕዮተዓለም አገር በቀል የሚያሰኘው የችግር ትንተናው ነው ማለት ነው፡፡ጉዳዩ ከትግበራ አንፃር ሳይሆን ከንድፈ ሀሳብ አኳያ የሚታይ መሆኑንም ይጠቁማል፡፡
ስለዚህ ከአሁን በፊት ኢትዮጵያ የተከተለቻቸው ርዕዮቶች አገራዊ ችግርን አልተነተኑም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ግን ቢያንስ የተማሪዎች ንቅናቄ መሠረታዊውን የኢትዮጵያ ጥያቄ ያነገበ መሆኑን ከላይ ማብራራት ተችሏል፡፡ይህንን ይዘን ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እናዝግም፡፡ለዚህም የኢሕአዴግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ካጠኑ ሰዎችና በቀድሞ የ‹መደመር› ደራሲ አለቆች የተፃፉ ትንታኔዎችን በማነፃፀር የመጽሐፉን ግኝቶች እንመልከት፡፡
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲው መምህር ሀብታሙ ግርማ REVOLUTIONARY DEMOCRACY IN
ETHIOPIA ፡Origin, Evolution and Development›› በሚል ያወጣውን መጽሐፍ እናስቀድም፡፡ደራሲው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1970ዎቹ (እ.ኤ.አ) እንደሆነ ይጠቅስና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አባት የቻይናው ማኦ እንደሆነ ያስታውሳል፡፡በተለይም የቻይናን አርሶ አደር ማዕከል ባደረገ ትንተና ገቢራዊ የሆነው የማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ማኦይዝም እስከመባል ደርሷል ይልና፣የሌኒን ሥራ የነበረው ይህንን ለአርሶ አደር የተተገበረ ርዕዮት ለከተማ ወዛደር ማዋል ላይ ያተኮረ እንደነበር ያወሳል፡፡የኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ከዚህ ከማኦ ፍልስፍና የተቀዳና ገበሬን ማዕከል አድርጎ ፖለቲካል-ኢኮኖሚን መተግበር ዓላማው ያደረገ እንደሆነ ይገልፃል-መምህሩ፡፡
ኢሕአዴጎች ደጋግመው የሚገልፁትም ከዚህ ጋር የሚመጋገብ ነው፡፡‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ከከፋ ድኅነትና ከአምባገነናዊ አገዛዝ በፍጥነት መውጫ መሣሪያ ነው› ይላሉ፡፡በ1997 ዓ.ም ‹ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ የፃፉት ሰነድ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣በነፃ ኢኮኖሚ ዙሪያ ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ፣…ችግሮችን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል አቅጣጫ ነው›› ይላል፡፡‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ድህነትን በመዋጋት ዴሞክራሲን እውን በማድረግ ከአስከፊ ውርደትን በአፋጣኝ የመላቀቅ አላማን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚረባረብ›› ተደርጎ ከአገራዊ ሁኔታ አንፃር እንደተተነተነ ይገልፃል፡፡
እዚህ ጋር አንድ ማስተዋል ያለብን ነጥብ አለ፡፡ኢሕአዴጎች በፃፉትና በተነተኑት ልክ ‹ፈጣን ልማት፣ዘላቂ ሠላምና አስተማማኝ ዴሞክራሲ› አምጥተዋል፤አላመጡም የሚለውን ክርክር እንተወውና ‹‹ከችግር ትንተና አንፃር አገር በቀል›› የሚለውን የ‹መደመር› ቀመር እንጠቀም፡፡ከዚያም በትንታኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አገር በቀል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን እንመልከት፡፡ቀጥለንም ‹በርግጥ የችግር ትንተና አገራዊ፣መፍትሔው ደግሞ ውጫዊ የሆነ ርዕዮተዓለም፣አገር በቀል ይባላልን?›› ስንል እንጠይቅ፡፡
የቀድሞው የኢሕአዴግ ሹም አለምነው መኮንን ‹‹ፖለቲካ ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ ሕዳሴ›› በሚለው መጽሐፋቸው፣አብዮታዊ ዴሞክራሲ የስሙን አወዛጋቢነት ወደጎን በማለት ለኢትዮጵያ እንዲሆን ተደርጎ መተርጎሙን ይገልፃሉ፡፡‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ የውጭ ጣልቃ ገብነትን፣ኋላቀርነትንና ፀረ-ዴሞክራሲን፣ለኢፍትሐዊ የሕብረተሰብ ግንኙነት ምክንያት የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ያወግዛል›› ሲሉ ይገልጹና ድሃውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በፍጥነት እንደሚያሳድግ፣የአርሶ አደሩን ሕይወት በርብርብ እንደሚቀይርና ጎጂ ድርጊቶችን በአስቸኳይ እንደሚያቃልል ያስረዳሉ፡፡ይህ ጉዞም አብዮታዊ እንደሚያደርገው ያነሳሉ፡፡
በአቶ መለስ ዜናዊ እንደተፃፈ የሚነገርለትና በ‹መደመር› መጽሐፍ ውስጥ በዋቢ መጽሐፍነት በመጨረሻው ገጽ የተገለፀው ‹የተሐድሶው መስመርና የኢትዮጵያ ሕዳሴ› የሚለው ድርሳን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሶስት ተልዕኮዎችን እንደተሸከመ ይገልፃል፡፡
‹‹ልማትን እንደህልውና ጥያቄ የሚያይ፣ከባለሃብቱ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ነፃ መሆንና የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነት እንዲኖረው መፍጠር›› የሚሉት ናቸው፡፡ይቀጥልናም ‹‹መንግሥታችን ልማት የሕልውና ጥያቄ ነው ብሎ የሚያምነው ሕዝቡን ወይም ማንኛውንም የውጭ ኃይል ስለፈራ ወይም ስለጠረጠረ አይደለም፡፡ድህነታችንና፣የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እጦት ሊበትነንና እርስበርሳችን ሊያናቁረን ይችላል ብሎ ከጎረቤት አገሮችና ከሌሎች በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ልምድ በመነሳት ስለደመደመ ነው፡፡ስለሆነም…ፈጣን ልማት ካላረጋገጥን (አብዮታዊ) ሕዝቡ ተስፋ እንዲሰንቅ ካላደረግን በአገራችን አርማጌዶን ይከሰታል፤እርስበርሳችን እንባላለን›› ይላል፡፡
እንግዲህ አንድን ርዕዮተዓለም አገር በቀል የሚያሰኘው፣አገራዊ የችግር ትንተናው ከሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን ችግር በአስፈሪ አደጋ በሚገባ አብራርቶታል፡፡የኢትዮጵያን ጥያቄዎች አልፋና ኦሜጋ ሠላም፣ልማትና ዴሞክራሲ እንደሆኑ በብዙ ድርሰቶች ጽፏል፡፡ዳሩ ግን የመደመር መጽሐፍ እንዳለው የአንድ ርዕዮት አገር በቀልነት የሚረጋገጠው አገራዊ ችግርን በመተንነተኑ አይደለም፡፡በዚህማ አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚበልጣት አልነበረም፡፡ከአሁን በፊት በየትኛውም የአካዳሚ ዲስፒሊን አንድ ሃልዮት አገሪቱን መስሎ ስለ ተተነተነ ብቻ አገር በቀል ተብሎ አያውቅም፡፡ሊሆንም አይችልም፡፡ስለዚህ መደመር ልክ እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አገር በቀል አይደለም!
መደመር እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ?
መደመር ‹‹የሕዝባችንን ሥነልቦናና የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ በልካችን የተሰፋ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል›› ቢልም ይህንን ‹በልካችን የሚያስፈልገንን ዴሞክራሲ›› አይገልጽም፡፡ነባሩን ርዕዮትና ልሂቅ በሚገባ ቢያብጠለጥልም ለ80 ሚሊዮን አርሶ አደር፣ለ30 ሚሊዮን ከድህነት ወለል በታች ለሚሆር ምስኪን፣ለሚሊዮን ሥራ አጦች፣ለድሃ ከተሜ የሚሆን የማኅበራዊ ዋስትናና የድህነት ማምለጫ አማራጭ አላስቀመጠም፡፡‹የትንተናው አገራዊነት፣አገር በቀል ያሰኘዋል› ቢልም ቢያንስ አሀዛዊ መረጃዎችን በማጣቀስ የፃፈው ትንተና የለም (ስለ ኢኮኖሚ በሚያትተው ገጽ ላይ ከሰፈሩት ሶስት አንቀፆች ውጭ)፡፡
ይህ ‹እሳቤ› አምና በአዲስ ራዕይ ላይ ‹የኢሕአዴግን ርዕዮት አይተካም› ተብሎ ቢፃፍም፣ከሳምንታት በፊት በወጣው የኦዲፒ መግለጫ ግን መደመር አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንደሚተካ ተገልጧል፡፡ይሁን እንጂ የቀደመው ኢሕአዴግ እጅግ ጠርናፊ በሆነ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ተግብሮ አፋኝ መንግሥት እንደፈጠረው ሁሉ፣ሥልጣን ከታች ይመነጫል ብሎ የሚያስበውን ፌደራላዊ አወቃቀር በተፃረረ ሁኔታ ከላይ ወደ ታች በማዘዝ ለአሃዳዊነት የቀረበ ሥርዓት እንዳነበረው ሁሉ፣ከሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ በተቃራኒ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን የይስሙላ እንዳደረገው ሁሉ መደመርም ከቡድናዊ ፈላጭ ቆራጭነት ወደ ግለሰባዊ የምታሸጋግረን ድልድይ ትመስላለች፡፡ምናልባትም አገር በቀልነቷ የሚረጋገጠውም በግለሰባዊ አምልኮ ላይ የምትገነባ አገርን ከፈጠረች ብቻ ነው፡፡ለዚህም ጉዞው ተጀምሯል፡፡
ልክ ጋዳፊ አረንጓዴው መጽሐፍ የተሰኘውን ድርሰቱን እያንዳንዱ ሊቢያዊ እንዲማረው በየትምኅርት ቤቱ እንዳከፋፈለው ሁሉ፣የሊቢያ ሕፃናት በየሣምንቱ እንዲማሩት እንደተገደዱት ሁሉ፣ቴሌቭዥንና ሬዲዮኖች ስለ እርሱ እንዲያወሩለት እንደተደረገው ሁሉ፣መደመርም በመንግሥት ወጪ ተመርቆና ተከፋፍሎ፣በመንግሥት ባለሥልጣናት አማካኝነት በየቦታው ሪቫን ተቆርጦለት፣በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እየተለፈፈለት ነው፡፡በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም መጽሐፉን ይዞ ለውይይት መቀመጥ ተጀምሯል፡፡የውጭ ጉዳዩንና የመደመርን ሐሳብ በሚቀጥለው ሳምንት እንመለስበት?!
