Connect with us

አሰቃቂው የአባትና ልጅ ግድያ

አሰቃቂው የአባትና ልጅ ግድያ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

አሰቃቂው የአባትና ልጅ ግድያ

አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ “ጠባቂዎቼ ሊወሰዱብኝ ነው” የሚል መልዕክት በማህበራዊ ድረ ገፁ ማስተላለፉን ተከትሎ ከፍተኛ ግጭትና ጥቃት ከተፈፀመባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው ኮፈሌ ወረዳ፣ አባትና ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይና በዱላ ተደብድበው ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው በሞተር ሳይክል በመንገድ ላይ መጎተቱን ቤተሰቦቻቸው ይገልጻሉ፡፡

የ60 ዓመቱ ሟች አቶ ታምራት ፀጋዬ በዚያው በኮፈሌ ወረዳ ተወልደው ያደጉ ሲሆኑ፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ንግድ ላይ ተሰማርተው በትጋት በመስራት ብዙ ሃብትና ንብረት ያፈሩ የታወቁ ኢንቨስተር ለመሆን እንደበቁ ይነገርላቸዋል፡፡

አብሯቸው በድንጋይ ተወግሮና በፌሮ ብረት ተቀጥቅጦ የተገደለው ልጃቸው ሄኖክ ታምራት ደግሞ በትምህርቱ ማስተርስ ዲግሪ ያለውና በአዋሽ ባንክ ለረጅም ጊዜ ካገለገለ በኋላ ከአባቱ ጋር በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርቶ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ከተፈፀመ በኋላም የሟቾችን አስከሬን በአካባቢው ለመቅበር ባለመቻሉ፣ በአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ብርታት ወደ አዳማ ተልኮ፣ ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የቀብር ስነ ሥርአታቸው መፈፀሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሟቾች በኮፈሌ ከተማ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያፈሯቸው ከፍተኛ ግምት ያላቸው ንብረቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡ የእነሱ ንብረት ብቻ ሳይሆን የአቶ ታምራት እህት ግሮሠሪና የለስላሳ መጠጥ ማከፋፈያ መጋዘን እንዲሁም የጭነት አይሱዙ መውደሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሟች አቶ ታምራት ከወደሙባቸው ንብረቶች መካከል አይሱዙ ተሽከርካሪና ሁለት የቤት አውቶሞቢሎች፣ አንድ ሆቴል ከእነ መኝታ ክፍሎቹ፣ አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር፣ አንድ ቪላ መኖሪያ ቤት፣ የእህል ወፍጮ ቤት፣ የእህል መጋዘንና የቆዳ መጋዘን ይገኙባቸዋል ተብሏል:: የሟች ልጃቸው ሄኖክ ታምራት በሻሸመኔ ከተማ የሚገኝ መኖሪያ ቤት እንዲሁም አንድ የቤት መኪናው እንደ ተቃጠሉም ታውቋል፡፡

ጥቃት አድራሾቹ በሺዎች የሚቆጠሩና በቡድን ሆነው ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ የገለፁት ቤተሰቦች በከፍተኛ ድምፅ ‹‹ታምራት! ታምራት!›› እያሉ ወደ ሟች መኖሪያ ቤት እንዳመሩና በመጀመሪያ ልጃቸውን፣ ቀጥሎም አባትየውን በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ በድንጋይና በፌሮ ቀጥቅጠው እንደገደሏቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚያም አስከሬኑን በሰንሰለት አስረው በሞተር ሳይክል እየጎተቱ ከተማዋን ሲዞሩ እንደዋሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አባትና ልጁን ከገደሉ በኋላ ‹ሁለት በአንድ! ሁለት በአንድ!› እያሉ ሲጨፍሩ ነበር›› ያሉት የሟቾች ቤተሰቦች፤ የልጁን አስክሬን ለማቃጠልም ሙከራ አድርገው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

‹‹ከአንዱ ቀበሌ ወደ አንዱ ቀበሌ፣ የሟቾች መኖሪያ ቤት ከሚገኝበት ቆሬ ሰፈር እስከ ሻሸመኔ መውጫ፣ ከሻሸመኔ መውጫ እስከ ባሌ መውጫ ድረስ አስክሬናቸው በሞተር ሲጎተት ነበር›› ብለዋል የሟቾች ቤተሰቦች፡፡

‹‹ወላጆቻችን ተወልደው ባደጉበትና እኛም ተወልደን ባደግንበት አገር፣ እንዲህ ስንደረግ ሕዝብ ምን ይፋረደን ይሆን? ኢትዮጵያም ምን ትፈርደን ይሆን? መንግስት ምን ይፈርደን ይሆን?›› ያሉት ቤተሰቦች፤ በብዙ ጥረትና ልፋት ያፈራነውን ንብረትም በሙሉ በአንድ ጀንበር አጥተን ተቀምጠናል ሲሉ በምሬትና በቁጭት ይናገራሉ፡፡

አባትና ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደላቸውም ባሻገር ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቤተሰቡ ንብረት መውደሙንና ይሄን ተከትሎም 80 የሚደርሱ ሰራተኞችም መበተናቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹የሰው ቤት በአሽከርነት ሰርተን፣ በጥረታችን ዛሬ ባለንብረት የሆንን ሰዎች፣ ይህ ሁሉ መአት የወረደብን ምን በደል ሰርተን ነው? በደላችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይይልን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዳኘን›› በማለት የሟች ቤተሰቦች በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ተማፅነዋል፡፡

በከተማዋ የነበሩት የሟች አቶ ታምራት እህት በበኩላቸው፣ በጎረቤቶቻቸው እርዳታ ከጥቃቱ ተርፈው በሌሊት ወደ አዳማ መሸኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከጥቃቱ የተረፉትም በጭድ ክምር ውስጥ ጎረቤቶቻቸው ደብቀዋቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርጊቱን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ መታሰራቸውንና እነሱም ቢሆኑ እንዲፈቱ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን በመጠቆምም፣ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በአንክሮ እንዲከታተሉላቸው ጠይቀዋል፡፡

የደረሰባቸውን ጥቃትና በደልም በተመለከተ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በደብዳቤ መግለጻቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ድርጊቱ በእጅጉ ክፉ ጠባሳ ጥሎብናል የሚሉት ቤተሰቦቻቸው፤ መንግስት እውነተኛ ፍትህ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top