Connect with us

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተሰጠ የፕሬስ መግለጫ

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በአሜሪካ መንግስት ጋባዥነት በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በተደረገ የምክክር ስብሰባ ላይ ተሳትፏል።

ኢትዮጵያ በስብሰባው የተሳተፈችው በአሜሪካ መንግስት በተደረገ ግብዣ መሰረት ሲሆን ጥሪው ምክክር እና ሂደቱን የማስቀጠል አልሞ የተዘጋጀ ነው። በዚሁ አጋጣሚ የአሜሪካ መንግስት በግድቡ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ በሚል ይህን መድረክ በማመቻቸት ላደረገው አጋርነት የኢፌዴሪ መንግስት ያመሰግናል።

ምክክሩ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ነበር። የመጀመሪያው ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ. ትራምፕ ጋር በነጩ ቤተ-መንግስት የተደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን መኒቺን እና የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር የተደረገ ነው።

በምክክሩ ወቅት በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተደረጉ ገንቢ ውይይቶችን እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለሶስትዮሽ ድርድሩ አለመቀጠል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበዋል። ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውሃ መብት እንዳላትም አስገንዝባለች። ኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ያክል የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኝ ህዝቧን ተደራሽ ለማድረግ እና ለድህነት ቅነሳ ጥረቷ እንጂ ማንንም አካል የመጉዳት አላማ እንደሌለት አስረድታለች። ኢትዮጵያ ለሶስትዮሽ ውይይቱ አሁንም ትልቅ ግምት እንደምትሰጥ፣ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ማናቸውም አለመግባባቶች በቴክኒክ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክክር ብቻ እንደሚፈቱም እንደምታምን፣ ጉዳዩን ኢ-ምክንያታዊ ያልሆነ የፖለቲካ ይዘት ማላበስም ለአገራቱ እንደማይጠቅም አስገንዝባለች። ይህም በተሳታፊዎቹ ዘንድ የነበረውን ብዥታ ግልጽ እንዲሆንና የኢትዮጵያ አቋም ገንቢ መሆኑን እንዲገነዘቡ አስችሏል።

በተደረገው ውይይት መሰረትም የሶስቱ አገራት ሚኒስትሮች በታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላል ዙሪያ ገንቢ፣ ቀጣይነት ያለውና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስማምተዋል። በተጨማሪም የቴክኒክ ውይይቱ እንዲቀጥል እንዲሁም ለቴክኒክ ኮሚቴው ድጋፍ ለማድረግ እና በሚኒስትሮች ደረጃ ያለው ውይይት በ2015ቱ የመርሆዎች ስምምነት መሰረት እንዲቀጥልም ከመግባባት ላይ ተደርሷል። አሜሪካ እና የአለም ባንክ የቴክኒክ ውይይቱ እንዲቀጥል ማበረታታቸውንና በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶችም በታዛቢነት የሚሳተፉ ይሆናል። ምናልባት በቀጣይ የሚደረጉ ውይይቶች ለመጨረሻ ውሳኔ ባያደርሱ እ.ኤ.አ በ2015 በተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት (Declarations of Principles) ሶስቱም አገራት በሚያደርጉት ውሳኔ ሊመረጥ እንደሚችልም መግባባት ላይ ተደርሷል።

የግብጽና የኢትዮጵያ መሪዎች በቅርቡ በሩሲያ ተካሂደ በነበረው የሩስያ-አፍሪካ ጉባኤ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት በሰጡት መመሪያ መሰረት በዚህ ስብሰባም ተጠናክሮ ስምምነት የተደረገበት የሶስቱ አገራት ብሔራዊ የቴክኒክ ቡድን ገንቢ ወደ ሆነ ምክክር እንዲመለስ ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች። ለዚህም የሶስቱን አገራት ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ ለስብሰባ ጠርታለች።
በመጨረሻም ውይይቱ በዚሁ የትብብር መንፈስ እንደሚቀጥል እምነታችን መሆኑን እየገለጽን ሁላችንም አሸናፊ ልንሆን ወደምንችልበት መድረክ ትኩረት እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ምንጭ:- ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top