Connect with us

የዐቢይ እና የጃዋር ጫማ የመለካካት ፖለቲካ በስንት ጋሎን ደም ይቆማል?

የዐቢይ እና የጃዋር ጫማ የመለካካት ፖለቲካ በስንት ጋሎን ደም ይቆማል?
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

የዐቢይ እና የጃዋር ጫማ የመለካካት ፖለቲካ በስንት ጋሎን ደም ይቆማል?

የዐቢይ እና የጃዋር ጫማ የመለካካት ፖለቲካ በስንት ጋሎን ደም ይቆማል? | (ማስረሻ ማሞ)

ቋንቋን መሠረት አድርጎ በዘውግ ላይ የተሰፋው ፖለቲካ መዘዙ እጅግ በጣም ብዙ እንደሚኾን ማውራት ከጀመርን አምስት ዐሥርተ ዓመታት ኾኖናል። ይኼን መሰሉ ፖለቲካ የሚጎፈንናቸው ሰዎች ጭምር አውቀውትም ይኹን ሳያውቁት ሐሳቡ ተቀንብቦ የተሰካካባቸውን ቃላቶች ጥቅም ላይ በማዋል አላስፈላጊ የኾነ ፖለቲካዊ ውለታ እየዋሉ ነው፤ በዚህም ፖለቲካው በድቡሽት ላይ ሳይኾን በዐለት ላይ የተቸከለ ያስመስሉታል። ይህ የሚኾነው በማወቅ ሳይኾን ለማወቅ ባለመጠየቅ ይመስለኛል።

የዚህ ፖለቲካ አራማጆች ፖለቲካውን “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ” ወይም ደግሞ “የብሔር ፌዴራሊዝም” በሚል ቃል ለማስዋብ ይሞክራሉ። ብዙዎቻችንም ለቃላት ትርጓሜ ግድ ሳይሰጠን የተባለውን እንደወረደ ተቀብለን እናስተጋባለን፤ ተቀብሎ የማስተጋባት የዘር ውርዴ ያለብን ይመስል! የምናስተጋባው ሐሳቡን አንቀበልም በሚል ሰበብ ቢኾንም፤ ቃሉ ለማይገባቸው እና ለማይመጥናቸው የፖለቲካ ኀይሎች አላስፈላጊ ውለታ እንውልላቸዋለን።

ብዙዎቻችን “የብሔር ፖለቲካ አንወድም” እንላለን፤ እንደሚያንገፈግፈን እና እንደሚያቅለሸልሸንም እንናገራለን። ነገር ግን ለአፍታ ቆም ብለን “ብሔር ማለት ምን ማለት ነው?” ብለን አንጠይቅም። በርግጥስ ብሔር የሚለው ቃል _ ቋንቋ ትራሱ ለኾኑት ቦትላኪ ፖለቲከኞች ይመጥናል ወይ? ብለንም አንጠይቅም።

ብሔር ማለት አገር ማለት ነው። አገር ማለት የራሱ የኾነ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ፣ ግዛት(ድንበር)፣ ታሪክ፣ ዘውግ ወይም ደግሞ የጋራ የኾነ ሥነ ልቡናዊ ባህልን የሚካፈል የተረጋጋ ማኅበረሰብን ያቀፈ ሕዝብ የሚኖርበት መልከዐ ምድር ማለት ነው። እኛ ግን ብሔርን ወይም ደግሞ አገርን ከሚማግሩት አንዱ ለኾነው ዘውግ “ብሔር” የሚል ስያሜ በመስጠት ከፍተኛ የኾነ የፖለቲካ አረንቋ ውስጥ ገብተናል።

ይኼ ከሃምሳ ዓመት ወዲህ የመጣው የዘውግ ፖለቲካ አዳዲስ ምናባዊ ትርክቶችን በመንተራስ “ያልነበሩ አገሮችን” የነበሩ በማስመሰል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ውዥንብር አስታቅፎናል፤ “አላ’ንድ የላት ጥርስ በዘነዘና ትነቀስ” እንደሚባለው ያለንን ወደማሳጣት እያንደረደረን ይገኛል። ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ በተለያየ ባሕልና እምነት ውስጥ የሚኖር ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገር (እንደ መልከዐ ምድሩ ጠባዩና ባሕርይውም የተለያየ) ማኅበረሰብ ነበረ እንጂ፤ አሮሞ የሚባል ብሔር ወይም ኦሮሞያ የሚባል አገር አልነበረም።

በተመሳሳይ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ በተለያየ ባሕልና እምነት ውስጥ የሚኖር አማርኛ ቋንቋ የሚናገር (እንደ መልከዐ ምድሩ ጠባዩና ባሕርይውም የተለያየ) ማኅበረሰብ ነበረ እንጂ አማራ የሚባል ብሔር ወይም አገር አልነበረም። እንደ መልከዐ ምድሩ ዐይነት ጠባዩና ባሕርይው የተለያየ የትግርኛ ቋንቋ የሚናገር ማኅበረሰብ ነበር እንጂ ትግሬ የሚባል ብሔር ወይም አገር አልነበረም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሰማንያ ዘለቆቹን ዘውጎች መዘርዘሩ የአንባቢን ጊዜ መብላት ስለኾነ እነዚህን ሦስቱን በምሳሌነት ወስዶ ማሳየቱ በቂ ይመስለኛል።

ሰማንያ ዘለቅ ዘውጎች ባሉበት አገር ላይ ያልነበረን ነገር እንደነበረ አድርጎ ለማሳየት የግድ ምናባዊ ትርክት ስለሚያስፈልግ፤ ምናባዊ ትርክት ተፈጠረ። ይኼን ምናባዊ ትርክት ለየት የሚለው በቁርሾ፣ በቂምና በበቀል ሸራ ላይ የተሳለ በመኾኑ ነው። “ተጨቋኝ ዘውጎች” ነበሩ የሚል የሐሰት ሥዕል ሲሳል “ጨቋኝ ዘውግ” መኖሩም አብሮ ተቀልሟል። ለሺሕ ዓመታት በጭቆና አለንጋ ሲገረፉ የኖሩ፣ በግፍ በትር ሲነረቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገሩ፣ በችጋር ወላፈን ሲለበለቡ የከረሙ እና በድህነት አረንቋ ውስጥ የተጣሉ፤ ጉዳዩ የማይመለከታቸው የዘውጉ አባላት “የጨቋኝ ዘውግ” ታርጋ ተለጥፎባቸዋል።

የዘውግ ፖለቲካ አስቀያሚ ገጽታው ጭቆናውን ሲፈጽሙ የነበሩትን ጨቋኝ የገዢ መደብ አባላት ከኀላፊነት እና ከተጠያቂነት ነጻ እያወጣ (አንዳንዴም ጀግና እያሰኘ) በአጠቃላዩ የዘውግ አባላት ላይ የጥላቻ፣ የቂም እና የበቀል ማኅተም እያሰረ፤ ዕድል ፈንታቸውን ለሽብር፣ ለስጋት እና ለሰቀቀን አሳልፎ መስጠቱ ነው።

ሕወሓት፣ ሻዕቢያ እና ኦነግ “የአማራ ጭቆና” ብለው የፈጠሩት ትርክት ለ27 ዓመታት ያተረፈልን ነገር ቢኖር እስር ቤቶችን በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች እንዲሞሉ ማድረግ ነው። “የአማራ ጭቆና” ትርክት “በትግሬ ጭቆና” ትርክት ተተካ። 27 ዓመቱ ባከተመ በማግሥቱ ማዕከላዊ መንግሥቱ “ለኦሮሞ እንታገላለን” በሚሉ ፖለቲከኞች ቁጥጥር ስር ሲገባ ትርክቱ ወደ “ኦሮሞ ጭቆና” ተሻገረ። “የተረኝነት ስሜት አለ” የሚል አዲስ ፖለቲካል ተርሚኖሎጂ ተፈጠረ። ይኼ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የዘውግ ፖለቲካ እስካለ ድረስ መካሰሱ ይቀጥላል። ምክንያቱም በዘውግ ፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ የሚለካው እና የሚመዘነው በሠራው ሥራ እና ባመነጨው የሐሳብ ልዕልና ሳይኾን ሳይንሳዊ ማረጋገጫ በሌለው “የዘውግ አጥንት” ቆጠራ በመኾኑ ነው። ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እስካለ ድረስ ይኼን መሰሉ ክስና አቤቱታ ከውጪ መምጣቱ የማይቀር ነው።

አሁን ያለንበት ችግር ግን የውጪው ብቻ አይደለም። “ለኦሮሞ ዘውግ ጥቅም” ነው የታገልኹት በሚሉ መካከል የተፈጠረው ጫማ የመለካካት ፖለቲካ አገሪቱ ብዙ ጋሎን ደም በምስ እንድታቀርብ እያደረጋት ነው። እናም የዘውግ ፖለቲካ ጫዎታው ሄዶ ሄዶ በዐቢይ እና በጃዋር ጫማ የመለካካት ፉክክር ውስጥ ወድቋል። ይኼ የጫማ መለካካት ፖለቲካ በስንት ጋሎን ደም ይቆማል?

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top