Connect with us

ዝምታ ምንድነው? ስምምነት ወይስ ተቃውሞ?

ዝምታ ምንድነው? ስምምነት ወይስ ተቃውሞ?
Photo: AFP

ህግና ስርዓት

ዝምታ ምንድነው? ስምምነት ወይስ ተቃውሞ?

ዝምታ ምንድነው? ስምምነት ወይስ ተቃውሞ?
(ጫሊ በላይነህ)

የአክቲቪስትና የሚዲያ ባለሀብት ጀዋር መሐመድ የተከበብኩኝ ጥሪ ተቀብለው ካለፈው ረቡዕ ዕለት ጀምሮ አደባባይ የወጡ ወጣቶች አመጽ ጋር ተያይዞ 67 ሰዎች መሞታቸውን እንደዋዛ ሰማን፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮምሽነር ከፍያለው ተፈራ ለሬውተርስ የዜና አገልግሎት ትላንት እንደተናገሩት ካለፈው ዕረቡ ዕለት ጀምሮ በተቀሰቀሰው አመጽ በድምሩ 67 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 49 ያህሉ በድንጋይ ተወግረው የሞቱ፣ 13 ቱ ደግሞ በጥይት የተገደሉ ናቸው፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ አምስት ያህሉ ፖሊሶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ የደረሰው የንብረት ውድመትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ይኽ የእብደት ውጤት.. ገናና ታሪክ፣ ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የመቻቻልና የመከባበር፣ የአብሮነት ባህል እሴት ባላት ሀገር መፈጸሙ እጅግ…እጅግ ያሳዝናል፤ ያማል፡፡ ወገን በገዛ ሀገሩ በየጎዳናው እንደእባብ ተቀጥቅጦ ሲገደል ማየትም፣ መስማትም እጅግ ያሳዝናል፣ያማል፡፡ ከምንም በላይ መንግሥት እንደጀዋር መሐመድ ያለ ጽንፈኞች እና በቄሮ ስም የሚንቀሳቀሱ ነፍስ ገዳዮችን መንግሥታችን በጉያው አቅፎ እሹሩሩ ማብዛቱ ያማል፤ ያሳፍራልም፡፡ ይባስ ብሎ የንጹሀን ወነድሞቻችን ቀብር እንኳን ሳይፈጸም ወንጀለኞችን «ወንድማችን» እያሉ የሚያንቆለጻጽሱና እግር የሚልሱ ሹማምንትን መስማት፣ ማየት ይቀፋል፡፡
መንግሥት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ያልቻለው ለምንድነው?

መልሱ ብዙ ምርምር አይፈልግም፤ ያው ከንቱ ፍርሃትና ሥጋት ነው፡፡ ነገሩ መብሰልሽ ላይቀር ማገዶ ፈጀሽ እንዳለው ሰው መሆኑ ነው፡፡ ትላንት ከሰዓት በኃላ እንዲህ ሆነ፡፡ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና አገልጋዮችዋ ላይ እየደረሰ ያለው የግፍ ጥቃት ጉዳይ መነሻ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች ከምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ እና የሰላም ሚኒስትርዋ ሙፈሪያት ካሚል፣ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች ጋር ምክክር ነበራቸው፡፡ አባቶች «ሕግና ሥርዓት የማስከበር አቅም አላችሁ ወይ?» በሚል ባለሥልጣናቱን በጥያቄ አፋጠጧቸው፡፡

ባለሥልጣናቱ «አዎን አለን፡፡ በአንድ ጀምበር ሰጥ ለጥ ማድረግም የመጣንበት መንገድ ነበር» ሲሉ መለሱ፡፡ «ግን ግን… ይኽን ያለፍንበት አስቀያሚ መንገድ መልሰን ልንሄድበት አልፈለግንም ነበር፡፡ አሁን ግን ትግዕስታችን አልቋል፡፡…አባቶች እንደምታውቁት ብዙ ስራ አጥ ወጣት አለን፡፡ ይህን ኃይል ጽንፈኞቹ በቀላሉ እየዘወሩት መሆኑ አንድ ችግር ነው፡፡…ለልጅ ሁለት ሶስቴ ዕድል ይሰጣል፡፡ ዕድል ስጡን፣ እንስተካክላለን» ማለታቸው ተሰምቷል፡፡(በጥቅሱ ውስጥ የተቀመጠው ሀሳብ ቃል በቃል የተወሰደ አይደለም) ነገርግን ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈው ማክስኞ ዕለት ፓርላማ ተገኝተው ለዘብ ያለ የማስጠንቀቂያ ንግግር ባደረጉ በ24 ሰአታት ልዩነት ደም አፋሳሽ ነውጥ መፈጠሩ ለሰሚው ግራ ነበር፡፡ እሳቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡፡ “የውጭ አገር ዜጋ የሆናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች ስትፈልጉና ሰላም ሲሆን እዚህ ተጫውታችሁ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት ሁለት አገር ያላችሁ ሰዎች ትግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው።……. በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላምና ህልውና ላይ ከመጣ አማርኛ ብትናገሩም ኦሮምኛም ብትናገሩም እርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መሆኑን በጥንቃቄ መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል።”

ግን ጥያቄው ትግዕስቱና የእርምጃ እንወስዳለን ቀረርቶ ማሰማቱ አልበዛም ወይ የሚል ነው፡፡ ሰው ተወልዶ ባደገበት ሀገር መጤ ተብሎ ሲታረድ፣ አስከሬኑ መሬት ለመሬት ሲጎተት፣ ንብረት በእሳት ሲጋይ… መንግስት ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆነው እስከመቼ ነው? የእናንተ ትግዕስት ተሟጦ ወደቆራጥ እርምጃ እንድትገቡ ስንት ሰው እስኪሞት እንጠብቅ የሚለውን የብዙ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው፡፡

ምናልባትም ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ በሰሞኑ የንጹሀን ግድያ እጃቸው ያለበትን ሰዎች ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ በትግዕስት ስም ይህን ከባድ ወንጀል በዝምታ ሊያልፈው አስቦም ከሆነ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከብዙሀኑ ልብ ተፍቆ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይኽ ያልተገባ ዝምታ ምናልባትም የሌላኛው መንግሥት አሸናፊነት በአደባባይ መመስከር ሊሆን ይችላል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ተስፋ እንዲቆርጥና የራሱን እርምጃ እንዲወስድ መግፋትም ይሆናል፡፡ ያልተገባ ዝምታ ለጽንፈኞችም ትልቅ የአሸናፊነት አቅም ይሰጣል፡፡ ከምንም በላይ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመንን ይሸረሽራል፡፡ ቢረፍድም ለወንጀል አድራጎት መንግሥታዊ ሽፋንና እገዛ በመስጠት ከፍተኛ አመራሮችን ያስጠይቃል፡፡

በመጨረሻም የምወደው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የተናገረውን በመጥቀስ ልሰናበት፡፡ «እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ በኦሮሞ ሰም ከሰውነት ወርዶ የሚንቀሳቀስ ሰው ሳይ እናደዳለዂ፡፡…ትላንት ነጻ አውጥቼአለሁ፣ዛሬ ልዝረፍህ፣ ንብረትህን ላውድም፣ መንገድ ልዝጋ… ያ ካልሆነ ዘቅዝቄ አሰቅልሃለሁ የሚል ቡድን በፍጹም የኦሮሞ ሕዝብ ወኪል ሊሆን አይችልም፡፡»
አበቃሁ፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top