Connect with us

ፎቆቹን አስመልሱልን፤ ፀብ አጫሪዎችንም ቅጡልን

ፎቆቹን አስመልሱልን፤ ፀብ አጫሪዎችንም ቅጡልን

ህግና ስርዓት

ፎቆቹን አስመልሱልን፤ ፀብ አጫሪዎችንም ቅጡልን

ፎቆቹን አስመልሱልን፤ ፀብ አጫሪዎችንም ቅጡልን | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

የጠቅላይሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ የሠላም ኖቤል በተሸለሙ ማግስት የመጣ በመሆኑ ትርጉም አለው፡፡ አብዛኞቹ የፓርላማ
አባላትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠላም ኖቤል በመሸለማቸው ያላቸውን ደስታ በመግለጽ የሠላምና መረጋጋት ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ውለዋል፡፡

አብዛኞቹ ጥያቄዎች ሥለ ሠላምና ደኅንነት ቢሆንም ስለ ምርጫ ያላቸውን አቋም ግን ግልጽ ያደረጉበት መሆኑ የተለየ
ያደርገዋል፡፡ምርጫው መካሄድ አለበት የሚለውን በዋናነት ሕወሓት ብቻ ሲያቀነቅነው የነበረውን ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫውን አስፈላጊነት በማብራራት ምርጫው እንዲካሄድ ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፓርላማ አባላትን አቅም በማሳደግ ጥሩ ጥሩ እጩዎችን ማቅረብ እንደሚገባ ካነሱ በኋላ ‹‹ይህንን አድርገን ወደ ምርጫ ካልገባን አደገኛ ነገር ሊፈጠር ይችላል›› ያሏት ነገር ግን ትጎረብጣለች፡፡ምናልባት የኢሕአዴግን ሽንፈት ሊሆን ይችላል አደገኛ ሊሆን ይችላል ያሉት፡፡፡ይህ በጭራሽ የማይሆን ነገር ነው፡፡ኢሕአዴግ ተሸነፈ ማለት በጭራሽ አደገኛ ነገር ተፈጠረ ማለት አይደለም፡፡

ከዚያ በመቀጠል ትኩረት የሚስበው ነገር ስለ ውጭ አገር ዜጎችና የሚዲያ ባለቤቶች የተናገሩት ነገር ነው፡፡‹‹አማርኛም
ተናገራችሁ ኦሮምኛ ሕግ ለማስከበር እንገደዳለን›› ያሏቸው እነዚህ ሰዎች፣ሠላም ሲጠፋ ዘወር ብለው የሚበጠብጡ፣ሠላም
ሲገኝ ደግሞ ከእኛ ጋር የሚሆኑ ናቸው ብለው አምርረው ተችተዋቸዋል፡፡ይህ ንግግራቸው ባሳለፍነው ዓመት በጅማ በተካሄደው የኦሕዴድ የመጨረሻ ጉባኤ ላይ ከተናገሩት፣ ‹‹ቀን ቀን ከእኛ ጋር እየዋሉ ማታማታ ከሌላው ጋር የሚያሹ አሉ፡፡ከእኛ ጋር ያልሆነ የእኛ አይደለም›› ካሉት ጋር በደንብ ይገጥማል፡፡

የኢትዮጵያን ፖለቲካ የውጭ አገር ዜግነት ይዘው በየሚዲያው እየበጠበጡት ነው ሲሉም ነው የተቹት፡፡ማንን ማለታቸው እንደሆነ
ግን ግልጽ አላደረጉም፡፡ከንግግራቸው መረዳት የሚቻለው ግን ትኩረታቸው እንደ አቶ ጃዋር መሐመድ ካሉ ፖለቲከኞች ጋር የተገናኘ ይመስላል፡፡

ሌላኛው ጉዳይ ስለ ሠላም ሲያነሱ፣ ‹‹እየበጠበጡን ያሉት ከአርባ ዓመት በፊት ጀምሮ በፖለቲካ ውስጥ ያሉና ዛሬም ድረስ
በተለያዩ ፓርቲዎች ላይ ሊቀመንበር ላይ የተቀመጡ ሰዎች ናቸው›› ብለዋል፡፡ይህንን ንግግራቸውን ተከትሎ ላሰበ ሰው ባለፉት
አርባ ዓመታት ፖለቲካው ላይ ያለና አሁንም ‹ሊቀመንበር› የሆነ (እርሳቸው ቼር ማን ነው ያሉት) ሰው ማግኘት
አይቻልም፡፡

ምናልባት በዚህ አርባ ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ፓርቲዎች ከአባልነት እስከ አመራርነት ያደጉና በአሁኑ ሰዓት ወደ
ሊቀመንበር ያደጉ አዛውንት ፖለቲከኞች ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)፣ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ ዳውድ ኢብሳ፣መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣
ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ከአባልነት ወደ ሊቀመንበርነት ያደጉ ፖለቲከኞች ደግሞ ራሳቸው ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ፣ደብረጽዮን (ዶ/ር)፣ ደመቀ መኮንን፣ወዘተ ናቸው፡፡ታዲያ የትኛውን ማለታቸው ነው? የትኛውስ ነው አገር እየበጠበጠ ያለው?

ከዚህ ጥያቄ ቀጥሎ የሚነሳው ሀሳብ ታዲያ መንግሥት እነዚህን ሰዎች ለማስተካከል ምን እርምጃ ወሰደ ወይም ሊወስድ ነው
የሚለው ነው፡፡ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ባይሎጂ ያረግፋቸዋል›› በማለት እነዚህን ሰዎች ሞት ሲወስዳቸው ሠላም
እንደሚመጣ ነግረውናል፡፡

ይህ ተገቢ አገላለጽ አይመስልም፡፡በአንድ በኩል መንግሥት አጥፊዎችን እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ ሕግ ያለው አካል ነው፡፡ታዲያ መንግሥት እራሱ ማስተካከል የሚገባውን ችግር ባዮሎጂ እንዲፈታው ስለምን ይጠብቃል ?

ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት ማንንም ቢሆን ጥፋት ካለበት በሕግ ጥላ ስር አውሎ ሕዝብን ከሠላም ማጣት እንዲታደግ ማድረግ
አለበት፡፡ይህንን ሳያደርግ ከቀረም ተጠያቂ ነው፡፡እንዴት አገር የሚበጠብጠው አካል ይህንን ያህል እየታወቀ ዝም ተብሎ ‹ሞት
እስኪወስደው› ይጠበቃል?

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባሳለፍነው ሳምንት መጽሐፋቸው ሲመረቅ፣‹‹አሜሪካና ዱባይ ፎቅ የደረደሩ›› ሰዎች እንዳሉ ሲናገሩ
ተደምጠዋል፡፡የመጨረሻውን የመንግሥት ሥልጣን ይዞ እንዲህ ዓይነት ንግግር በመናገር ሕዝብን ወደተራ አሉባልታ
ከማውረድ፣እርሳቸው ሆምጠጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ፎቅ ሲደረድር የሚውል ሹመኛ ካለ፣ ይህ አንደኛ ተጠያቂ ቢሆንም ፎቅ ሲደረድር ዝም ብሎ የተመለከተ መንግሥትም ግን ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡ይህንን ነገር ማስተካከል እንደሚገባ መታወቅ አለበት፡፡

እናም ጥያቄው አንድ ነው፡፡ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ሆይ መንግሥትዎ ብዙ የታጠቀና ብዙ ሀብት ያለው ነው፡፡ይህንን ሥልጣንዎን ተጠቅመው አገር በጥባጮቹንና ፎቅ ደርዳሪዎቹን እሰሩልን፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top