Connect with us

የአስም በሽታ ምንድነው? እንዴት መከላካል ይቻላል?

የአስም በሽታ ምንድነው? ምክንያቱስ፣ ምልክቶቹስ፣ እንዴት መከላካል ይቻላል?
Photo: Intra Med

ጤና

የአስም በሽታ ምንድነው? እንዴት መከላካል ይቻላል?

የአስም በሽታ ምንድነው? ምክንያቱስ፣ ምልክቶቹስ፣ እንዴት መከላካል ይቻላል? ለሚሉና ለተያያዥ ጥያቄዎች ምላሽ እንሆ

አስም ክረምቱ አልፍ መስከረም እና ጥቅምት አካባቢ የአስም በሽታ የሚበረታበት ወቅት ነው:: የዚህ በሽታ ስርጭት በአገራችን ውስጥ በትክክል ባይታወቅም በአሜሪካ ግን ከአጠቃላይ የአገሪቷ ህዝብ ውስጥ 7% የሚሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው አነስተኛ ያልሆኑ ሰዎችም በዚህ በሽታ ምክንያት በየዓመቱ ህይወታቸው ይቀጠፋል፡፡

የአስም በሽታ ምንድነው? የዚህ በሽታ አምጪ ምክንያትስ ምንድነው?

የአስም በሽታ አየርን ወደ ሳምባ የሚወስድ የአየር ቧምቧን እና በሳምባ ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ የአየር ቱቦዎችን የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚከሰተው የእነዚህ የአየር ቱቦዎች/ ቧምቧዎች ስፋት (ዲያሜትር) ሲቀንስና አየርን በትክክል ማመላለስ ሲያቅታቸው ነው፡፡ የእነዚህ የአየር ቧምቧዎች ስፋትም የሚቀንሰው አለርጂ (allergy) ሲኖረው እና ወፍራም ፈሳሽ (Mucus) ጤናማ ሰው ከሚያመነጨው በላይ ሲያመነጩ ነው፡፡ የአየር ቧምቧ ሲጠብ እና በዚህ ወፍራም ፈሳሽ (Mucus) ሲሞላ አየር ወደ ውስጥ መግባት እና መውጣት አይችልም። ከዚህም የተነሳ በዚህ ችግር የተያዙ ሰዎች የተለያዩ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ፡፡

ለአስም በሽታ ያጋልጣሉ ከሚባሉ ነገሮች መካከል፣

በአስም በሽታ የተያዘ የስጋ ዝምድና መኖር ሌሎች አለርጂ በሽታዎች መኖር (እንደ የቆዳ እና የሳይነስ አለርጂዎች) የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ መጨመር፣ ሲጋራ ማጨስ እና ሲጋራ በሚያጨሱ ሰዎች አጠገብ በመገኘት ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ (Passive Smokers) በሥራ ላይም ሆነ በሌላ ምክንያት ከተለያዩ ፋብሪካዎች ለሚመነጩ ኬሚካሎች መጋለጥ

የበሽታው ምልክቶች፣

ከዚህ በሽታ ምልክቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ሳል (በተለይ ማታ ማታ እና በብርድ ወይም በቅዝቃዜ ጊዜ)፣ አየር ሲተነፍሱ የማንኮራፋት ድምፅ ማሰማት፣ መተንፈስ አለመቻል ወይም የአተነፋፈስ መቆራረጥ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የዚህ በሽታ አስከፊነት ከሰው ሰው ይለያያል፡፡በአንዳንድ ሰዎች ላይ ቀላል ሆኖ ትናንሽ ምልክቶችን ብቻ የሚያሳይ ሲሆን በሌሎች ላይ ደግሞ መተንፈስ አቅቷቸው ከመደበኛ ሥራቸው እስከ መቅረትና ሕይወት እስከመቅጠፍ የሚያደርስ ነው። ይህ የአስም በሽታ የሚያሳየው ምልክት ብዙውን ጊዜ ቀጣይነት ያለው ሳይሆን በመሀል እረፍት እየሰጠ ሌላ ጊዜ እየባሰ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምልክቱ እየቀነሰ የሚታይ ነው፡፡

የአስም በሽታና ሊያስነሱ የሚችሉ ሁኔታዎች፣

የአየር ቧምቧዎችንም ከሰውነታችን አካላት ውስጥ አንዱ በመሆናቸው ወደ ሰውነታችን ባዕድ ነገሮች ሲገቡ የመቆጣት ባህሪ ያሳያሉ፡፡ በተለይም ደግሞ የአስም በሽታ ያለባቸው ሰዎች ወደ ሰውነታቸው ባዕድ ነገሮች ሲገባ የአየር ቧምቧቸው ይቆጣል፤ የመተንፈሻ አካል ይጠባል፤ አክታ መሳይ ነገር ይለቃል።

ሰውነታቸው የሚከላከሏቸው ወይም የሚጠሏቸው ነገሮች አለርጂ ይባላሉ። የጤናማ ሰዎች የአየር ቧምቧ አለርጂ ቢያጋጥመውም ምንም አይነት የቁጣ ወይም የመለወጥ ነገር አያሳዩም ፡፡ የአስም በሽታ ያለባቸው ሰዎች አካል ግን ይቆጣል፤ በበሽተኛው ላይም ህመም ያስከትላል፡፡

ሰውነታችንን ከሚያስቆጡ ነገሮች ውስጥ ጥቂቶቹ፣ ቀዝቃዛ አየር፣ ደረቅ አየር፣ ልዩ ልዩ የአበባ ብናኞች እና በአየር ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን ነገሮች፣ ከባድ ሽታ (ጠረን ወይም ጥሩ መዓዛ)፣ ሲጋራ ማጨስ ወይም ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ፣ አቧራ፣ እንደ ሳል እና የሳምባ ኢንፌክሽን ያሉ የአየር ቧምቧን የሚያጠቁ በሽታዎች፣ የአእምሮ ጭንቀት (stress)፣ የሚነድ ማገዶ ጭስ፣ የቤት እንስሳት ጠረን፣ ለሌሎች በሽታዎች የሚሰጡ አንዳንድ መድኃኒቶች፣ የአካል እንቅስቃሴ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ይህንን በሽታ እንዴት መከላከል ይቻላል?

የአስም በሽታ የሚያስነሱ ነገሮችን ማንሳት ያስፈለገበትእና መከላከሉ ላይ ትኩረት የተደረገበት ዋነኛው ምክንያት በሽታውን የሚፈውስ ፍቱን መድኃኒት ባለመገኘቱ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን በሽታው እንዳይነሳ እና ሰውን እንዳይጎዳ ማድረግ ይቻላል፡፡ በሽታው ከመቀስቀሱ በፊት ከሚደረግ ጥንቃቄ ባሻገር ከተነሳም በኋላ ለአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ የአስም ምልክቶችን የሚቆጣጠሩ መድኃኒቶች (controllers) አሉ፡፡

እነዚህ መድኃኒቶች በአይነታቸው እንደ በሽታው ክብደት የሚለያዩ እና በቀጣይነት ወይም በሽታው በሰውየው ላይ በሚነሳበት ጊዜ ብቻ የሚወሰዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የአስም በሽታ ከጤና ባለሙያ የሚታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ በመውሰድ በሽታውን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ከእነዚህ መድኃኒቶች በተጨማሪ በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች በሽታውን የሚያስነሱባቸው ነገሮችን ካወቁ እነዛን ነገሮች ማስወገድ ወይም በዛ አካባቢ መገኘት የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ፡ – በሽታው ቀዝቃዛ አየር የሚጠላ ከሆነ በአፍ ላይ ሻሽ ወይም ሌላ መልበሻ አፍ ላይ አድርጎ መጓዝ በጣም ይረዳል። በሽታውን የሚያስነሳብን ነገር አውቀን እራሳችን ከሚያስነሳው ነገር መከላከል/መጠበቅ፤ ከባድ መድኃኒት ከመውሰድ እና ሆስፒታል ከመተኛት ህመምተኛውን ይታደገዋል። ህመምተኛው ሲጋራ የሚያጨስ ከሆነ መተው እንደዚሁም ሲጋራን ከሚያጨሱ ሰዎች መራቅ አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ምን እንደሚያስነሳባቸው ስለማያውቁ በሽታውን ከሚቀሰቅስባቸው ነገር ለመራቅ ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡

የአስም በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው መተላለፍ ይችላልን?

በማህበረሰቡ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የአስም በሽታ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በሳል ይተላለፋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ ስህተት ሲሆን የአስም በሽታ ከአንድ ህመምተኛ ወደ ሌላ ሰው በማንኛውም መንገድ አይተላለፍም፡፡ በደም ስር (Ge¬netics) ግን በተወሰነ ያህሉ ከወላጅ ወደ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን አባት እና እናት የአስም በሽታ ሲኖርባቸው ልጃቸው በበሽታው ይያዛል ማለት ሳይሆን ይህ ህጻን ይበልጥ ለአስም በሽታ የመጋለጡ እድል ከፍተኛ ነው ማለት ነው፡፡

ከአስም በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ምንድናቸው?

የአስም በሽታ ለሌለባቸው ሰዎች እንደ ቀላል ሊታዩ የሚችሉ እንደ ሳል (ጉንፋን) ያሉ የአየር ቧንቧዎች ኢንፌክሽኖች የአስም በሽታ ያለበትን ሰው የያዙ እንደሆነ በጣም ጠንተውበት በአስጊ ደረጃ ላይ ማድረስ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚሆነውም የአስም በሽታ የሚቀስቅስ/ እንዲከፋ የሚያደርግ ችግር ስላለባቸው ነው፡፡

የአስም በሽታ በህክምና ባለሙያ የተሰጠውን የአስም መድኃኒት በአግባቡ አለመውሰድ ወይም ሐኪም ቤት ሄዶ አለመታከም በደቂቃዎች ወይም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የአተነፋፈስ ሥርዓት እንዲዳከምና ታማሚው በበሽታው እንዲሰቃይ ያደርጋል፡፡አልፎ ተርፎም በቀላሉ ነፍስ ሊቀጥፍ ይችላል፡፡

ስለዚህ የአስም በሽታ ምልክቶችን በሰውነት ላይ ካዩ ወደ ሐኪም ቤት በመሄድ አስፈላጊውን ህክምና በማግኘት እነዚህን ችግሮች ማስወገድ ይቻላል፡፡

ምንጭ አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ .ም

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top