Connect with us

የዐቢይ አሕመድና የኤል ሲሲ ውይይት

የዐቢይ አሕመድና የኤል ሲሲ ውይይት
Photo: Twitter

ፓለቲካ

የዐቢይ አሕመድና የኤል ሲሲ ውይይት

Nulla pariatur. Excepteur sint occaecat cupidatat non proident, sunt in culpa.

የዐቢይ አሕመድና የኤል ሲሲ ውይይት
(በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

ሰሞኑን ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይና የግብጹ ፕሬዚዳንት በሥልክ መነጋገራቸውን መገናኛብዙሃን ዘግበዋል፡፡የውይይታቸውን ይዘት ባናውቀውና ባንሰማውም በቅርቡ ሁለቱ መሪዎች ለመገናኘት ተቀጣጥረዋል፡፡የአገሪቱ መንግሥት ለፓርላማው ባቀረቡት ማብራሪያ ግን ኢትዮጵያን በጦር እስከ መፈተን የሚደርስ አማራጭ እንደሚኖር የሚጠቁም ሽለላ አሰምተዋል፡፡ይህ የሆነው የካርቱሙና የካይሮው ውይይት ከከሸፈ በኋላ ነበር፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ባሳለፍነው እሁድ የታተመው የፎርቹን ጋዜጣ የሕዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅም በ1300 ሜጋ ዋት መቀነሱን ዘገበ፡፡

በ74ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ የግብጹ ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ያደረጉት ንግግር በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር የግብጽን ጥቅም ካላስጠበቀ የአባይ ተፋሰስ አገራትን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚያሰጋ አደጋ እንደሚመጣ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ግብጽ ከሲዊዝ ቦይ እስከ ቀይ ባሕር ድረስ፣ ከሲናይ በረሃ እስከ ሳህል ቀጣና ያላትን የተሰሚነት መንገድ ይዘው ነው ኤል ሲሲ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ግድብ ዙሪያ ጣልቃ ካልገባ አደገኛ ነገር እንደሚከሰት የዛቱት፡፡

ይህ አንድ የዲፕሎማሲ ቅደም ተከተልን ከሚያውቅና የተጠና የውጭ ግንኙነት ሥራ ከሚሠራ መሪ የሚጠበቅ ነው፡፡ መድረኩንም በሚገባ ተጠቅመውበታል፡፡በአንድ በኩል 193 አገራት በአንድ አዳራሽ ውስጥ የተገኙበት በመሆኑ ላልሰሙት እንዲሰሙ፣ፍላጎት ላላቸው ደግሞ ጣልቃ እንዲገቡ ለማድገር ‹ጋብዘውበታል›፡፡ጉዳዩ በዚህ መድረክ ከተሳተፉት ሁሉም አገራት በተጨማሪ፣በበርካታ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ያገኘ ነው፡፡ስለዚህ ግድቡን ዓለማቀፋዊ ገጽታ እንዲላበስ አድርጋዋለች፡፡ ይህም ቢያንስ የሁለት አገራት አለያም የሶስት አገራት ከበዛ ደግሞ የአንድ ቀጣና አገራት ጉዳይ መሆን ሲገባው የ193 አገራት አጀንዳ በማድረግ ማራገብ ችለዋል፡፡የዋይታውስ መግለጫ የዚህ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ዝርዝሩን ዝቅ ብለን እንመለስበታለን፡፡

ሁለተኛው ኤል ሲሲ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ያስተላለፉት መልዕክት ‹ሕዳሴ ግድብ የ100 ሚሊዮንን ግብፃዊያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤ይህንን ግድብ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያም ቀጣናውን ወደ ቀውስ ልታስገባው ነው፡፡ለዚህም ኃላፊነት እንደማንወስድ ከወድሁ እወቁት› የሚል ነው፡፡እናም ይህንን አጀንዳ ዓለማቀፋዊ ገጽታ በማላበስ የአንዲት የግብጽ ጉዳይ ሳይሆን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ አጀንዳ አደረጉት፡፡ፕሮጀክቱ የትብብርና የጋራ ብልጽግና መሣሪያ ነው የሚለውን የኢትዮጵያን አቋምም የአለመግባባትና የልዩነት ምንጭ አድርገው ሳሉት፡፡

ለዚያም ነው በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንና በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ይቺን የኤል ሲሲን ንግግር ማራገብ የተጀመረው፡፡ስመ ጥር መገናኛ ብዙሃንም ‹‹Sisi Calls For International Interference With Renaissance Dam Negotiations›› እያሉ ዜናውን አሠራጩት፡፡‹‹ኤል ሲሲ በሕዳሴ ግድብ ላይ ዓለማቀፍ ጣልቃ ገብነት ጠየቁ›› እንደማለት፡፡
በሶስተኛ ደረጃም ለኢትዮጵያ የልማት ሥራ ድጋፍ ለሚያደርጉ ዓለማቀፍ ተቋማት የሚሰጠው አሉታዊ ትርጉም ትንሽ አይደለም፡፡በአባይ ወንዝ ላይ ለሚሠራ ድልድይም ሆነ በወንዙ ገባሮች ላይ ለሚሠሩ ሌሎች የልማት ሥራዎች የሚሰጥ ድጋፍ ካለ እንዲዘገይ ወይም እንዲቀር ሊያደርግ ይችላል፡፡የሁለቱም አገራት (የግብጽም የኢትዮጵያም) ወዳጅ የሆኑ ለጋሽ ተቋማትና መንግሥታት በዚህ ውዝግብ ውስጥ መግባት ስለማይፈልጉ እንዲቆም ያደርጋል፡፡

የዋይታውስ ‹ትዕዛዝ›
ግብጽ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ ካቀረበች በኋላ በካርቱም የተካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ይህ ከመሆኑ ዋዜማ ላይ ግን የዶናልድ ትራምፕ ቤተመንግሥት መግለጫ አወጣ፡፡አስገራሚው ነገር ደግሞ መግለጫው የግብጽን አቋም ይዞ መውጣቱ ነው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ሶስቱ አገራት (ግብጽ፣ኢትዮጵያና ሱዳን) የሚያደርጉትን ድርድር ጠቃቅሶ ‹‹ለጋራ ጥቅም ሲባል፣በውሀ አሞላልና በግድቡ አስተዳደር ላይ›› ከመስማማት እንዲደርሱ እንደሚደግፍ ይገልፃል፡፡

ነጥቡ ያለው እዚህ ጋር ነው፡፡ግድቡን በጋራ እናስተዳድረው የሚል መደራደሪያ የቀረበው ከግብጽ ነው፡፡ግድቡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ይህንን ግድብ የማስተዳደር ሥራ የኢትዮጵያ የራሷ ነው የሚሆነው፡፡በአላስካ ግዛት ውስጥ የሚገኝን ነዳጅ ጣቢያ ሩሲያ በጋራ ከአሜሪካ ጋር እንደማታስተዳድር ሁሉ፣የሕዳሴ ግድብም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለ ግድብ በመሆኑ የማስተዳደር ሥልጣኑ የአገሪቱ ነው፡፡ግብጽ ይህንን የሉዓላዊነት መብት ወደ ጎን በማለት ለማስተዳደርም እንደራደር ብላለች፡፡ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያ እንደማይሆን ብቻ ሳይሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ለመደራደር እንደማትፈቅድ ገልፃለች፡፡

በዚህ ጎን ገብተው ነው እንግዲህ አሜሪካኖቹ ‹በግድቡ ማስተዳደር ላይም ተመካከሩ› የሚል አባታዊ ትዕዛዝ ያመጡት፡፡
የካርቱሙ የሶስትዮሽ ድርድር እንደተቋረጠም፣ ለዚህ ለዋይታውስ መግለጫ የኤል ሲሲ ቢሮ ወዲያው ነበር ምላሽ የሰጠው፡፡‹‹በድርደሩ ላይ አሜሪካ ጣልቃ ትገባ ዘንድ የግብጽ ፍላጎትና ውሳኔ ነው›› ይላል-የግብጽ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫ፡፡

ይህንን ያህል ነው አሜሪካና ግብጽ የተናበቡት፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ሌላ አካል መጥቶ ያደራድረን የሚለውን ጉዳይ እንደማትቀበለው በይፋ ገልፃለች፡፡አሁን ብቻ ሳይሆብ ከዚህ በፊትም የዓለም ባንክ የደራድረን ስትል ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች-አትዮጵያ፡፡ግብጽንም ከግትር አቋሟ ተመልሳ ወደ ድርድር እንድትመጣ ጥሪ አቅርባለች-ዛሬ፡፡ይሁን እንጂ የግብጹ ፕሬዚዳንት በነዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ላደረጓቸው ተንኳሽ (offensive) ንግግሮች ምላሽም ይሁን ማስተባበያ ከጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ አልተሰጠም፡፡

ይህ በአንድ በኩል ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ግን ግብጽ እየሄደችበት ያለውና ግድቡን ዓለማቀፋዊ ገጽታ የማላበስ ዘመቻዋ ኢትዮጵያን መጨረሻ ላይ የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከት ስለሚችል በፍጥነት ማረም ይገባል፡፡ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ወትሮም የምትተዋቅበትን የጋራ መድረኮች መጠቀም ይኖርባታል፡፡ከታይታና ከግል ዝና የተላቀቀ የውጭ ግንኙነት ሥራ መሥራት በፍጥነት ሊተኮርበት ይገባል፡፡ዓለማቀፋዊ ሁኔታውን እያነበቡ ተራማጅ በሆነና መርህ ላይ በተመሠረተ አኳኋን ንቁ የውጭ ግንኙነት ሥራ እጅጉን ያስፈልጋል፡፡

(ማሳሰቢያ፤ ይህ ጽሁፍ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከታተመችው ፍትሕ መጽሔት የተወሰዱ ሀሳቦችን አካትቷል)

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top